ጭፍን ጥላቻና መድሎ—መንስኤያቸውን ለይቶ ማወቅ
ጭፍን ጥላቻና መድሎ—መንስኤያቸውን ለይቶ ማወቅ
“ሰዎች ሁሉ ነፃ፣ እኩል ክብር እንዲሁም መብት ያላቸው ሆነው ተወልደዋል። የሚያስብ አእምሮና ሕሊና ያላቸው ስለሆኑ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል።”—ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 1
እንደዚህ የመሰሉ በጥሩ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ጭፍን ጥላቻና መድሎ በሰው ልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። ይህ አሳዛኝ ሐቅ በምን ዓይነት ዘመን ውስጥ እንዳለን የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን የሰዎችን አለፍጽምና ጭምር የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 51:5) ይሁን እንጂ ሁኔታው ምንም ተስፋ የሌለው አይደለም። እርግጥ ነው፣ በዙሪያችን የምናየውን መድሎ ማስወገድ አንችልም፤ ይሁንና በውስጣችን ሊኖር የሚችለውን ጭፍን ጥላቻ ከሥሩ ነቅለን ለማውጣት መጣር እንችላለን።
ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያው እርምጃ፣ ማናችንም ብንሆን ጭፍን ጥላቻ ሊጠናወተን እንደሚችል አምነን መቀበል ነው። አንደርስታንዲንግ ፕሬጁዲስ ኤንድ ዲስክሪሚኔሽን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ስለ ጭፍን ጥላቻ ባደረግነው ምርምር ከደረስንባቸው ድምዳሜዎች መካከል ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡት የሚከተሉት ሳይሆኑ አይቀሩም፦ (1) ማሰብና መናገር የሚችል ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ከጭፍን ጥላቻ ነፃ አይደለም፤ (2) ጭፍን ጥላቻን ለመቀነስ ብዙውን ጊዜ የታሰበበት ጥረት ማድረግና ስለ ሁኔታው ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋል፤ እንዲሁም (3) ጥሩ የልብ ተነሳሽነት ካለ ይህን ማድረግ ይቻላል።”
ትምህርት፣ ጭፍን ጥላቻን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት “ከሁሉ የበለጠ ኃይል ያለው መሣሪያ” እንደሆነ ተገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ ትክክለኛ ትምህርት ማግኘት የጭፍን ጥላቻን መንስኤ ለማወቅ የሚያስችል ሲሆን አመለካከታችንን በሐቀኝነት እንድንመረምርና የጭፍን ጥላቻ ዒላማ በምንሆንበት ጊዜ ደግሞ ጉዳዩን በጥበብ እንድንይዝ ሊረዳን ይችላል።
መንስኤውን ለይቶ ማወቅ
ጭፍን ጥላቻ፣ ሰዎች ከራሳቸው አመለካከት ጋር የሚጋጩ እውነታዎችን አጣመው ወይም በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱ አልፎ ተርፎም በቸልታ እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። የጭፍን ጥላቻ መነሻ ከቤተሰብ የተወረሱ ምንም ክፋት የሌላቸው የሚመስሉ ሆኖም የተሳሳቱ የሥነ ምግባር እሴቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ የጭፍን ጥላቻ ዘር የተዘራው ሌላ ብሔር ወይም ባሕል ስላላቸው ሰዎች ሆን ብለው የተዛቡ አመለካከቶችን በሚያስፋፉ ወገኖች ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ጭፍን ጥላቻ በብሔራዊ ስሜትና በተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች አማካኝነት ሊስፋፋ ይችላል። እንዲሁም ጭፍን ጥላቻ ተገቢ ያልሆነ ኩራት ውጤት ሊሆን ይችላል። ቀጥሎ በተዘረዘሩት ነጥቦችና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በማሰላሰል በአስተሳሰብህ ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልግህ እንደሆነ ለምን ራስህን አትመረምርም?
ምሳሌ 18:1) ይሁን እንጂ ባልንጀሮቻችን በእኛ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ አብረናቸው የምንውላቸውን ሰዎች በጥበብ መምረጥ ይኖርብናል። በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች የልጆቻቸውን ጓደኞች ለማወቅ ከልባቸው ጥረት ያደርጋሉ። ጥናቶች እንዳመለከቱት የሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች እንኳ ከእነሱ የተለየ ዘር ስላላቸው ሰዎች የተዛባ አመለካከት ሊያዳብሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት የሚወስዱት ከሌሎች ሰዎች ዝንባሌ፣ አነጋገርና የሰውነት እንቅስቃሴ ነው። እርግጥ ነው፣ የአንድን ልጅ አመለካከት በመቅረጽ ረገድ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ወላጆች በመሆናቸው ወላጆች ራሳቸው በልጆቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር የቻሉትን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ባልንጀሮች። ሰዎች ከሌሎች ጋር ተግባብቶ የመኖር ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን ይህም ጥሩ ነገር ነው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል”፤ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተግባራዊ የሆነውን ጥበብ ወደኋላ ገሸሽ ያደርጋል። (▪ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።” (ምሳሌ 22:6) “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) ወላጅ ከሆንክ ራስህን እንዲህ በማለት መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘ልጆቼ በአምላክ ዓይን እውነትና ትክክል የሆነውን መንገድ እንዲከተሉ እየመራኋቸው ነው? ጓደኝነት የምመሠርተው በእኔ ላይ ጤናማ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰዎች ጋር ነው? በሌሎች ላይ ጥሩ ተጽዕኖ የማሳድር ሰው ነኝ?’—ምሳሌ 2:1-9
ብሔራዊ ስሜት። አንድ መዝገበ ቃላት ብሔራዊ ስሜት የሚለውን ሐሳብ ሲፈታው “አንድን ብሔር ከሌሎች ሁሉ በላይ ከፍ አድርጎ መመልከትን እንዲሁም ከሌሎች ብሔራት ይልቅ በዋነኝነት ለአንድ ብሔር ባሕልና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን የሚያበረታታ አስተሳሰብ” እንደሆነ ይገልጻል። ኢቮ ዱካቼክ የሚባሉ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር፣ ኮንፍሊክት ኤንድ ኮኦፐሬሽን አመንግ ኔሽንስ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፦ “ብሔራዊ ስሜት የሰው ዘርን በመከፋፈል እርስ በርስ መቻቻል እንዳይሰፍን አድርጓል። በዚህም የተነሳ ሰዎች መጀመሪያ የሚያስቡት አሜሪካዊ፣ ሩሲያዊ፣ ቻይናዊ፣ የፔሩ ተወላጅ ወይም ግብፃዊ መሆናቸውን ነው፤ ሰብዓዊ ፍጡራን መሆናቸውን የሚያስቡት (ያውም ካሰቡ) ከዚያ በኋላ ነው።” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ዛሬ ለሚያጋጥሙን ለአብዛኞቹ ችግሮች መንስኤው የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው፤ አሊያም የእንደነዚህ ዓይነቶቹ አመለካከቶች ውጤት ነው። ሰዎች እንደዚህ ካሉት አመለካከቶች አንዳንዶቹን ያዳበሯቸው ሳያስቡት ነው። ከእነዚህ መካከል ‘ትክክልም ይሁን ስህተት አገሬ የምትወስደውን እርምጃ እደግፋለሁ’ የሚለው ጠባብ ብሔረተኝነት የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይገኝበታል።”
▪ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምላክ ዓለምን [መላውን የሰው ዘር] እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘አምላክ ለማንም ሳያዳላ እኔን ጨምሮ ከሁሉም ብሔራት የመጡ ሰዎችን የሚወድ ከሆነ እኔስ (በተለይ ለእሱ ልዩ ክብር እሰጣለሁ የምል ከሆነ) እሱን ለመምሰል መጣር የለብኝም?’
ዘረኝነት። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ዘረኛ የሆኑ ሰዎች “የዘር ልዩነት በሰዎች ጠባይ ወይም ችሎታ ላይ ልዩነት እንደሚያመጣና አንዱ ዘር ከሌሎቹ እንደሚበልጥ” ያምናሉ። ሆኖም ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ በተገለጸው መሠረት ተመራማሪዎች “[አንዱ ዘር ከሌላው] ይበልጣል የሚለውን አባባል የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ አላገኙም።” ዘረኝነት የሚያስፋፋቸው ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች (ለምሳሌ ሆን ብሎ የሌሎች ሰዎችን መብት
መንፈግ) ዘረኝነት በሐሰትና በተሳሳቱ አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚጠቁሙ አሳዛኝ ማስረጃዎች ናቸው።▪ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል።’ (ዮሐንስ 8:32) “[አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:26) “እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘ሁሉንም ሰዎች አምላክ እንደሚያያቸው አድርጌ ለማየት እጥራለሁ? ሌሎች፣ ምናልባትም የተለየ ዘር ወይም ባሕል ያላቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ ለማወቅ አንዳንዶችን በግለሰብ ደረጃ ለመቅረብ እጥራለሁ?’ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ስናውቃቸው ስለ እነሱ ያለን አመለካከት የተዛባ መሆኑን በቀላሉ እንገነዘባለን።
ሃይማኖት። ዘ ኔቸር ኦቭ ፕሬጁዲስ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሰበብ በማድረግ [የግል ጥቅማቸውን] እና የዘራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚጥሩበት ጊዜ ጥላቻ መፈጠሩ የማይቀር ነው። ሃይማኖትና ጭፍን ጥላቻ የሚዋሃዱት በዚህ ጊዜ ነው።” ይኸው መጽሐፍ እንደገለጸው ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ሃይማኖተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች በቀላሉ “ጭፍን ጥላቻን የሚያዳብሩ መሆኑ” ነው። ይህን አባባል የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ለማግኘት በዘር የተከፋፈሉ አብያተ ክርስቲያናትን፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ያለውን ጥላቻና ዓመፅ እንዲሁም በሃይማኖት አነሳሽነት የሚፈጸሙ የሽብር ድርጊቶችን መመልከቱ ይበቃል።
▪ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከላይ [ከአምላክ] የሆነው ጥበብ . . . ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ . . . በአድልዎ ሰዎችን የማይለያይ” ነው። (ያዕቆብ 3:17) “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና [በሃይማኖታዊ] እውነት [ያመልኩታል]።” (ዮሐንስ 4:23) “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ።” (ማቴዎስ 5:44) ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘ሃይማኖቴ ለሁሉም ሰዎች፣ ሊጎዱኝ ለሚፈልጉትም ጭምር እውነተኛ ፍቅር ማሳየትን ያበረታታል? ዜግነታቸው፣ የቆዳ ቀለማቸው፣ ጾታቸው፣ የገቢ መጠናቸው ወይም ማኅበራዊ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ያለሁበት ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይቀበላል?’
ኩራት። ለራስ ከልክ ያለፈ ግምት መስጠት ወይም ኩራት አንድ ሰው ጭፍን ጥላቻ እንዲያዳብር ሊያደርገው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኩራት አንድ ሰው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ወይም በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሃ የሆኑ ሰዎችን እንዲንቅ አሊያም እንዲህ ካሉት ሰዎች እንደሚበልጥ እንዲሰማው ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም ግለሰቡ የራሱን ብሔር ወይም ጎሳ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳን እንዲያምን ሊያደርገው ይችላል። የናዚ ፓርቲ መሪ እንደነበረው እንደ አዶልፍ ሂትለር የመሳሰሉ ዘዴኛ ሰዎች የብዙኃኑን ድጋፍ ለማሰባሰብና የተለዩ ወይም የማይፈለጉ እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ወገኖችን እንዲጠሉ ለማድረግ ሲሉ ሆን ብለው የብሔርና የዘር ኩራትን የሚያበረታታ ፕሮፓጋንዳ ነዝተዋል።
▪ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እግዚአብሔር በልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል።” (ምሳሌ 16:5) “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጋችሁ በትሕትና አስቡ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።” (ፊልጵስዩስ 2:3) ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘የእኔን ዘር ወይም ጎሳ የሚያሞግሱ ሌሎችን ግን የሚያዋርዱ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ በውስጤ እደሰታለሁ? እኔ የሌለኝ ችሎታ ባላቸው ሰዎች እቀናለሁ ወይስ በችሎታቸው ከልብ እደሰታለሁ?’
አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” በማለት ማስጠንቀቁ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 4:23) ስለዚህ ልብህን እንደ ውድ ሀብት አድርገህ ተመልከተው፤ ደግሞም ምንም ነገር እንዲበክለው አትፍቀድ! ልብህ አምላካዊ በሆነ ጥበብ እንዲሞላ አድርግ። ‘የመለየት ችሎታና ማስተዋል የሚጠብቅህ እንዲሁም ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎችና ከክፉዎች መንገድ የሚያድንህ’ እንዲህ ካደረግህ ብቻ ነው።—ምሳሌ 2:10-12
ይሁንና ጭፍን ጥላቻ ወይም መድሎ በአንተ ላይ ቢደርስብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ይመረምራል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ስናውቃቸው ስለ እነሱ ያለን አመለካከት የተዛባ መሆኑን በቀላሉ እንገነዘባለን