በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ቁጣህን የመቆጣጠር ችግር የሚያጋጥምህ በየስንት ጊዜው ነው?

□ ጨርሶ

□ በወር አንዴ

□ በሳምንት አንዴ

□ በየቀኑ

አብዛኛውን ጊዜ በቁጣ እንድትገነፍል የሚያደርግህ ማን ነው?

□ ማንም

□ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች

□ ወላጆቼ

□ ወንድሞቼና እህቶቼ

□ ሌላ

አብዛኛውን ጊዜ የሚያበሳጭህን ሁኔታ ከዚህ በታች አስፍር።

□ ․․․․․․

ሣጥኑ ውስጥ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስትሰጥ “ጨርሶ” እና “ማንም” በሚሉት ላይ ምልክት አድርገህ የመጨረሻውን ጥያቄ ባዶ ትተኸዋል? ከሆነ እንኳን ደስ ያለህ! ቁጣህን መቆጣጠር ትችላለህ ማለት ነው!

እያንዳንዱ ሰው የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሚወስደው እርምጃ የተለያየ ነው፤ እንዲሁም ሁሉም ሰው በሆነ መንገድ ድክመት ይኖረዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 3:2) አንተም ቁጣህን በመቆጣጠር ረገድ እንደ 17 ዓመቷ ሴሪና * ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብላለች፦ “ቁጣዬን በውስጤ አምቄው እቆያለሁ፤ ከዚያም ብዙውን ጊዜ ሌላ ሰው ወይም ነገር ሲያበሳጨኝ ንዴቴን እወጣበታለሁ። ይህን የማደርገው በወላጆቼ፣ በእህቴ ሌላው ቀርቶ በውሻዬ ላይ ሊሆን ይችላል!”

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ከእውነታው መለየት

ስትቆጣ ለስሜትህ ልጓም ማበጀት ያስቸግርሃል? ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። እስቲ በመጀመሪያ ግን ልታስወግዳቸው የሚገቡ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንመርምር።

የተሳሳተ አመለካከት፦ “ቁጣዬን መቆጣጠር አልችልም፤ ያደግኩት በቀላሉ ቱግ በሚል ቤተሰብ ውስጥ ነው!”

እውነታው፦ ቤተሰብህ፣ ያደግህበት አካባቢ ወይም ሌሎች ነገሮች ተጽዕኖ ስላሳደሩብህ “ግልፍተኛ” ወይም በቶሎ የምትቆጣ ሰው ልትሆን ትችላለህ። ያም ቢሆን ስትቆጣ የምትወስደውን እርምጃ መቆጣጠር ትችላለህ። (ምሳሌ 29:22) እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ከቁጣ ጋር በተያያዘ ማድረግ የምትፈልገው ምንድን ነው? የሚል ይሆናል። መኪናውን መቆጣጠር እንደሚችለው በአሽከርካሪው ቦታ ላይ እንዳለው ሰው መሆን ትፈልጋለህ? ወይስ ምንም ማድረግ እንደማይችለው በተሳፋሪው ቦታ ላይ እንደተቀመጠው ሰው? ብዙ ሰዎች ቁጣቸውን መቆጣጠር ተምረዋል፤ አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ!—ቆላስይስ 3:8-10

ቁልፍ ጥቅስ፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31

የተሳሳተ አመለካከት፦ “አንድ ነገር ካበሳጨኝ በውስጤ ይዤው ከምብገነገን ይልቅ ተናግሬ ቢወጣልኝ ይሻላል።”

እውነታው፦ ንዴትህን በውስጥህ አምቀህ መያዝም ሆነ በቁጣ መገንፈል ሁለቱም ለጤንነትህ ጎጂ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ያስጨነቀህን ጉዳይ ‘መልቀቅ’ ወይም አውጥተህ መናገር ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። (ኢዮብ 10:1) ይህ ሲባል ግን ለመፈንዳት ትንሽ ነገር እንደሚበቃው ድማሚት በቀላሉ በቁጣ ትገነፍላለህ ማለት አይደለም። ቱግ ማለት ሳያስፈልግህ ስሜትህን መግለጽ የምትችልበትን መንገድ መማር ትችላለህ።

ቁልፍ ጥቅስ፦ “የጌታ ባሪያ ግን ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [እንዲሁም] . . . ክፉ ነገር ሲደርስበት በትዕግሥት የሚያሳልፍ ሊሆን ይገባዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:24

የተሳሳተ አመለካከት፦ “‘ለሰው ሁሉ ገርነትን’ ላሳይ ካልኩ ሁሉም ሰው መረማመጃ ያደርገኛል።”

እውነታው፦ ራስን መግዛት ጥንካሬ የሚጠይቅ ነገር እንደሆነ ሰዎች ማስተዋል ይችላሉ፤ እንዲህ በማድረግህም የበለጠ ያከብሩሃል።

ቁልፍ ጥቅስ፦ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18

ለቁጣህ ልጓም ማበጀት

በቀላሉ የምትቆጣ ሰው ከሆንክ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንድታሳይ ምክንያት የሆኑህ ሌሎች ሰዎች እንደሆኑ ትናገር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ “እሷ ባትቆሰቁሰኝ እንዲህ አላደርግም ነበር” ወይም “በንዴት እንድገነፍል ያደረገኝ እሱ ነው” ብለህ ታውቃለህ? ከሆነ የስሜትህን ልጓም የያዙት ሌሎች እንጂ አንተ እንዳልሆንክ አነጋገርህ ይጠቁማል። ታዲያ ስሜትህን ራስህ መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

ለድርጊትህ ኃላፊነቱን ውሰድ። በመጀመሪያ፣ አንድ ሁኔታ ሲያጋጥምህ መቆጣት አለመቆጣትህ የተመካው በአንተ ላይ እንደሆነ መቀበል ያስፈልግሃል። ስለዚህ ጣትህን በሌሎች ላይ መቀሰርህን አቁም። “እሷ ባትቆሰቁሰኝ እንዲህ አላደርግም ነበር” ከማለት ይልቅ ‘ቁጣዬን መቆጣጠር ነበረብኝ’ በማለት ለድርጊትህ ኃላፊነቱን ውሰድ። ወይም ደግሞ “በንዴት እንድገነፍል ያደረገኝ እሱ ነው” ከማለት ይልቅ ‘በቁጣ ገንፍዬ ከቁጥጥር ውጭ መሆን አልነበረብኝም’ በማለት ጥፋትህን ልታምን ይገባል። ለድርጊትህ ኃላፊነቱን መውሰድህ ችግሩን ለማስተካከል የሚያስችል አቋም ላይ እንድትገኝ ይረዳሃል።—ገላትያ 6:5

ችግሮች የሚፈጠሩት መቼ እንደሆነ አስተውል። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልኅ ሰው መከራ ሲመጣ አይቶ ይሸሻል፤ ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ ከገባ በኋላ እንደገና ይጸጸታል” ይላል። (ምሳሌ 22:3 የ1980 ትርጉም) እንግዲያው ቁልፍ የሆነው ነገር ችግሩ የሚፈጠረው መቼ እንደሆነ ማስተዋል ነው። ‘ብዙውን ጊዜ በንዴት ቱግ የምለው ምን ጊዜ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለምሳሌ ያህል፣ ሜጋን የተባለችው ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የምሠራው በሌሊት ሽፍት ነው፤ ሥራዬን አጠናቅቄ ስወጣ በጣም ይደክመኛል። በዚህ ወቅት በትንሹም በትልቁም እበሳጫለሁ።”

ጥያቄ፦ ብዙውን ጊዜ በንዴት ቱግ የምትለው ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስትሆን ነው?

․․․․․․

ሁኔታውን በተሻለ መንገድ ለመያዝ ጥረት አድርግ። የሚያስቆጣህ ነገር ሲያጋጥምህ በረጅሙ በመተንፈስ ራስህን ካረጋጋህ በኋላ ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በእርጋታ ተናገር። ያስቆጣህን ሰው ከመውቀስ (ለምሳሌ “ሌባ ነህ! ሹራቤን ሳታስፈቅድ ትወስዳለህ?” ከማለት) ይልቅ ድርጊቱ ስሜትህን እንዴት እንደጎዳው ለመግለጽ ሞክር። (“ሹራቤን ልለብሰው ስፈልግ አንተ እንደወሰድከው አወቅሁ፤ ሳታስፈቅደኝ ልብሴን ‘መዋስህ’ በጣም አበሳጭቶኛል” ማለት ትችላለህ።)

መልመጃ፦ በቅርብ ጊዜ በቁጣ ገንፍለህ የተናገርህበትን ሁኔታ ለማስታወስ ሞክር።

1. እንድትቆጣ ያደረገህ ምን ነበር?

․․․․․․

2. ምን አደረግህ ወይም ምን ተናገርክ?

․․․․․․

3. ምን ብታደርግ የተሻለ ይሆን ነበር?

․․․․․․

በቁጣ መገንፈልህ ምን እንደሚያስከትል አስብ። ይህን ለማድረግ የሚረዱህ በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፦

ምሳሌ 12:18፦ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል።” ቃላት የሌሎችን ስሜት ሊጎዱ ይችላሉ፤ በቁጣ ገንፍለህ በምትናገርበት ጊዜ ደግሞ በኋላ ላይ የምትጸጸትበት ነገር መናገርህ አይቀርም።

ምሳሌ 29:11“ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል።” በቁጣ ሲንጨረጨሩ መዋል አንተው ራስህ ተላላ ወይም ሞኝ እንድትመስል ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።

ምሳሌ 14:30፦ “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል።” ግልፍተኛ መሆን ለጤንነትህ ጎጂ ነው! አኒታ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰባችን ውስጥ ብዙዎቹ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት አለባቸው፤ እኔም በቀላሉ የምጨነቅ ሰው ስለሆንኩ በቁጣ ከመገንፈሌ በፊት ቆም ብዬ አስባለሁ።”

ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? አነጋገርህና ተግባርህ ምን እንደሚያስከትል አስብ። የ18 ዓመቷ ሄተር እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ፦ ‘ይህን ሰው በንዴት ገንፍዬ ብናገረው ስለ እኔ ምን ያስባል? እንዲህ ማድረጌ እርስ በርስ ያለንን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው? አንድ ሰው በእኔ ላይ ተመሳሳይ ነገር ቢያደርግ ምን ይሰማኛል?’” አንተም ተቆጥተህ ከመናገርህ ወይም ደብዳቤ፣ የስልክ መልእክት አሊያም ኢሜል ከመላክህ በፊት ከላይ ያሉትን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅ ትችላለህ።

ጥያቄ፦ አንድ ሰው ቢያበሳጭህና አንተም የቁጣ ምላሽ ብትልክ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

․․․․․․

እርዳታ ጠይቅ። ምሳሌ 27:17 “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም እርስ በርሱ አንዱ ከሌላው ይማራል” ይላል። (የ1980 ትርጉም) ወላጆችህን ወይም አንድ የጎለመሰ ጓደኛህን ቁጣቸውን የሚቆጣጠሩት እንዴት እንደሆነ ለምን አትጠይቃቸውም?

ያደረግኸውን ለውጥ ተከታተል። ያደረግኸውን ለውጥ በማስታወሻ ደብተር ላይ አስፍር። በንዴት ገንፍለህ በምትናገርበት ጊዜ ሁሉ (1) ምን ዓይነት ሁኔታ እንደተከሰተ፣ (2) ምን ምላሽ እንደሰጠህ እንዲሁም (3) ምን ብታደርግ ይሻል እንደነበረ በማስታወሻህ ላይ ጻፍ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ የተሻለ ያልከውን እርምጃ መጀመሪያ ላይ መውሰድን ትማራለህ!

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

በቁጣ ይገነፍላሉ ብለን የማናስባቸው ሰዎችም እንኳ ለአጭር ጊዜም ቢሆን እንዲህ ያደረጉባቸው ጊዜያት አሉ። ከሚከተሉት ምሳሌዎች ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

▪ ሙሴ—ዘኍልቍ 20:1-12፤ መዝሙር 106:32, 33

▪ ጳውሎስና በርናባስ—ሐዋርያት ሥራ 15:36-40

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“የተሰማኝን ነገር በማስታወሻዬ ላይ ማስፈሬ ወይም ለእማዬ መናገሬ እንድረጋጋ ይረዳኛል።”—አሌክሲስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ውጥረት ውስጥ ስገባ በእግሬ ቶሎ ቶሎ በመሄድ በውስጤ የታመቀውን ስሜት አወጣዋለሁ፤ ውጪ መውጣቴ አእምሮዬ እንዲረጋጋ ይረዳኛል።”—ኤሊዛቤት፣ አየርላንድ

“በሐሳቤ ራሴን ከሁኔታው አወጣና ‘በዚህ ወቅት ተቆጥቼ ባንባርቅ ምን ይከሰታል?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ይህን ማድረግ ምንም እንደማይጠቅም ብዙ ጊዜ ማስተዋል ችያለሁ።”—ግሬም፣ አውስትራሊያ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይህን ታውቅ ነበር?

አምላክ ራሱ የሚቆጣባቸው ጊዜያት አሉ። ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን ቁጣው ምክንያታዊና ትክክል ነው፤ እንዲሁም ቁጣውን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠረዋል። ሁልጊዜም ቢሆን ቁጣው ከተከሰተው ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን ነው።—ዘፀአት 34:6ን፤ ዘዳግም 32:4ን እና ኢሳይያስ 48:9ን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁጣህ ከቁጥጥርህ ውጪ ሆኖ እንዳይገነፍል መቆጣጠሩ በአንተ ላይ የተመካ ነው