ፍጥረት ቀድሟቸዋል
ፍጥረት ቀድሟቸዋል
“እስቲ . . . የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤ . . . የእግዚአብሔር እጅ ይህን [አድርጓል]።”—ኢዮብ 12:7-9
ወፎች ሁለንተናቸው ለበረራ እንዲመች ሆኖ የተፈጠረ ነው። ለምሳሌ ክንፉ ላይ ያሉትን ላባዎች የሚይዘው ዘንግ ወፉ በሚበርበት ጊዜ ክብደቱን በአጠቃላይ ሊሸከም የሚያስችል ጥንካሬ ሊኖረው ይገባል። ታዲያ ክንፎቹ በጣም ቀላል ሆኖም እጅግ ጠንካራ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? የላባውን ዘንግ መሃል ለመሃል ብትቆርጠው ምክንያቱን መረዳት ትችላለህ። መሐንዲሶች የስፖንጅ ንብብር አውታር የሚሉት ዓይነት አሠራር አለው። ውስጠኛው ክፍል ለስላሳ ሲሆን ውጭያዊው ክፍል ደግሞ ሸካራ ነው። መሐንዲሶች የላባ ዘንግን አሠራር ካጠኑ በኋላ አውሮፕላን ሲሠሩ የስፖንጅ ንብብር አውታር ተጠቅመዋል።
የአእዋፍ አጥንት አሠራርም ቢሆን በጣም የሚያስደንቅ ነው። አብዛኞቹ ውስጣቸው እንደ ሸምበቆ ባዶ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ መሐንዲሶች የዋረን ምሰሶ በሚባል ዘዴ በተገናኙ ውስጣዊ ቅስቶች የተጠናከሩ ናቸው። የሚገርመው ነገር፣ የጠፈር መንኮራኩሮችም በተመሳሳይ ንድፍ የተሠራ ክንፍ አላቸው።
አብራሪዎች ዘመናዊ አውሮፕላኖች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲበሩ የሚያደርጉት በአውሮፕላን ክንፎችና ጅራት ላይ ያሉ ጥቂት መቅዘፊያዎችን በማስተካከል ነው። አንድ ወፍ ግን የክንፎቹንና የእያንዳንዱን ላባ አቀማመጥ እንዲሁም እንቅስቃሴ በሴኮንድ ውስጥ ብዙ ጊዜ ለመለዋወጥ 48 የሚያክሉ የክንፍና የትከሻ ጡንቻዎችን ይጠቀማል። አውሮፕላን ሠሪዎች አእዋፍ ባላቸው የበረራና የመገለባበጥ ችሎታ መቅናታቸው ምንም አያስደንቅም!
በረራ በተለይ ደግሞ ከመሬት አኮብኩቦ መነሳት ብዙ ኃይል ይጠይቃል። በመሆኑም ወፎች በጣም ከፍተኛ ጉልበት ያለውና በፍጥነት የሚቀጣጠል “ሞተር” ያስፈልጋቸዋል። የወፍ ልብ ተመሳሳይ መጠን ካላቸው አጥቢ እንስሳት በበለጠ ፍጥነት የሚመታ ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ መጠኑ ትልቅ ነው፤ ከፍተኛ አቅምም አለው። በተጨማሪም የወፍ ሳንባ በአሠራሩ ለየት ያለ የአንድ አቅጣጫ ፍሰት ያለው ሲሆን ከአጥቢ እንስሳት ሳንባ በተሻለ ሁኔታ ይሠራል።
የወፍ “ሞተር” ምን ያህል አቅም አለው? የአንድ አውሮፕላን አቅም የሚለካው በቂ ነዳጅ ጭኖ ከመሬት ማኮብኮብ በመቻሉ ነው። አንድ ቦይንግ 747 አውሮፕላን አሥር ሰዓት የሚፈጅ በረራ ለማድረግ በሚያኮበኩብበት ጊዜ የክብደቱን ሲሶ የሚያክል ነዳጅ ይጭናል። በተመሳሳይም ከአንድ የምድር ክፍል ወደ ሌላው የምትሰደድ ትንሽ ወፍ አሥር ሰዓት የሚፈጅ በረራ ካደረገች በኋላ የክብደቷን ግማሽ ታጣለች። ይሁን እንጂ ባርቴይልድ ጎድዊት የምትባለው ወፍ ወደ ኒውዚላንድ ለመጓዝ ከአላስካ በምትነሳበት ጊዜ ከመላ የሰውነቷ ክብደት ከግማሽ የሚበልጠው ስብ ነው። የሚገርመው ነገር ወፏ ለአፍታ እንኳን ሳትቆም 190 ሰዓት (ስምንት ቀን) አለማቋረጥ ትበራለች። ይህን ያህል መብረር የሚችል አንድም የንግድ አውሮፕላን የለም።