በቆዳ ቀለምህ ደስተኛ ሁን
በቆዳ ቀለምህ ደስተኛ ሁን
● በአፍሪካ፣ በደቡባዊው እስያ፣ በካሪቢያንና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ነጣ ያለ የቆዳ ቀለምን ከብልጽግና ጋር የሚያያዙት ከመሆኑም በላይ የውበት መለኪያ አድርገው ይቆጥሩታል። በዚህም የተነሳ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ብዛት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች የቆዳ ቀለም የሚያነጡ ምርቶችን የሚጠቀሙ ሲሆን ይህም አንዳንድ ጊዜ በጤንነታቸው ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትልባቸዋል።
ቆዳን የሚያነጡ አንዳንድ ቅባቶች ሜላኒን የሚባለውን ቆዳን ከአደጋ የሚከላከል ንጥረ ነገር እንዳይመረት የሚያደርግ ሃይድሮኩዋይኖን የሚባል ኬሚካል ያላቸው ሲሆን ይህም ቆዳችን አልትራቫዮሌት የሚባለውን ጎጂ የፀሐይ ጨረር የመከላከል አቅሙ እንዲዳከም ያደርጋል። ሃይድሮኩዋይኖን ወደ ቆዳ ውስጥ ሰርጎ በመግባት እንደ ጅማትና አጥንት ባሉ አጣማሪ ሕብረ ሕዋሳት (connective tissues) ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው ያለ ዕድሜው ያረጀ እንዲመስል ያደርጋል። በተጨማሪም ይህ ኬሚካል የካንሰር በሽታ ሊያመጣ ይችላል። ሌሎች ቅባቶች ደግሞ በውስጣቸው ሜርኩሪ አላቸው፤ ይህ ንጥረ ነገርም መርዘኛ ኬሚካል ነው።
ከዚህም ሌላ እንዲህ ባሉት ምርቶች ረዘም ላለ ጊዜ መጠቀም መልክ የሚያበላሽ ሽፍታና ማዲያት በቆዳ ላይ እንዲወጣ ሊያደርግ ብሎም ቆዳው ድንገት ቢቆረጥ እንኳ መሰፋት እስከማይችል ድረስ ደካማ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም በአንዳንድ የመዋቢያ ቅባቶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ወደ ደም ሥር ውስጥ ከገቡ በጉበት፣ በኩላሊት ወይም በአንጎል ላይ ጉዳት ሊያደርሱና አልፎ ተርፎም እነዚህ የአካል ክፍሎች መሥራታቸውን እንዲያቆሙ ሊያደርጉ ይችላሉ።
የሚገርመው ነገር ጠቆር ያለ ቆዳ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ነጣ ያለ መልክ እንዲኖራቸው ሲፈልጉ ነጭ ቆዳ ያላቸው ብዙ ሰዎች ደግሞ ቆዳቸውን ለማጥቆር መከራቸውን ያያሉ። በመጠኑ ፀሐይ ላይ መሰጣት ለጤና ተስማሚ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ አይካድም፤ ለምሳሌ ሰውነታችን ቫይታሚን ዲ እንዲያመርት ሊረዳው ይችላል። ይሁን እንጂ በተለይ ፀሐይ አናት ላይ ስትሆን ለረጅም ጊዜ ለፀሐይ መጋለጥ ጎጂ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ቆዳችሁ በፀሐይ መጥቆሩ፣ የተወሰነ ጉዳት እንደደረሰበትና በአደገኛው የአልትራቫዮሌት ጨረር ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበት ራሱን ለመከላከል እየሞከረ መሆኑን የሚጠቁም ነው። ሆኖም ቆዳችን ራሱን ከጉዳት የመከላከል አቅሙ ውስን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ነጭ ቆዳ ያላቸው ሰዎች በተፈጥሮ የሚያመርቱት ቆዳን የሚያጠቁር ንጥረ ነገር ከአደገኛ ጨረሮች የመከላከል ኃይሉ (sun-protection factor) ከአራት አይበልጥም። በፀሐይ መከላከያ ቅባቶች አዘውትሮ መጠቀም ሊረዳ ቢችልም ቆዳን ሙሉ በሙሉ ከጉዳት ሊጠብቅም ሆነ ሜላኖማ የሚባለውን የቆዳ ካንሰር ጨምሮ ከአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ሊከላከል አይችልም።
በመሆኑም የዓለም የጤና ድርጅት “ሁሉም ሰው በተፈጥሮ የቆዳ ቀለሙ ደስተኛ መሆን እንዳለበት የሚገልጸውን ሐሳብ በተጠናከረ መንገድ ማሰራጨት” የተሻለ እንደሆነና ይህም “ሰዎች ራሳቸውን ከፀሐይ ጨረር ጉዳት እንዲጠብቁ ለማበረታታት የሚረዳ ወሳኝ እርምጃ” እንደሆነ ገልጿል። ብልኅ የሆኑ ሰዎች ግን ትኩረት የሚሰጡት ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ውበቱን ከሚያጣው ቆዳችን በተለየ መልኩ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እየተሻሻለ ለሚሄደውና መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰወረ የልብ ሰው” ብሎ ለሚጠራው ውስጣዊ ማንነታቸው ነው።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ምሳሌ 16:31