እርዳታ ፈልግ
እርዳታ ፈልግ
“አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል።” —መክብብ 4:12
ጠላታችን ምንም ይሁን ምን የሌሎችን እርዳታ ካገኘን ያንን ጠላት የማሸነፍ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። ስለዚህ የማጨስ ልማድህን ማሸነፍ ከፈለግህ የቤተሰቦችህንና የወዳጆችህን አሊያም በትዕግሥት ሊረዳህ ልባዊ ፍላጎት ያለው የማንኛውንም ሰው እርዳታ መሻትህ ብልህነት ነው።
የማጨስ ልማዳቸውን ያሸነፉ ሰዎች ችግርህን መረዳት ብቻ ሳይሆን የተሻለ ድጋፍ ሊሰጡህም ስለሚችሉ እንዲህ ዓይነት ግለሰቦችን ለማግኘት ጥረት አድርግ። በዴንማርክ የሚኖረው ቶርበን የተባለ አንድ ክርስቲያን “ሌሎች ያደረጉልኝ ድጋፍ በጣም ጠቅሞኛል” ብሏል። በሕንድ የሚኖረው ኤብረሃም ደግሞ “ቤተሰቦቼና ክርስቲያን ባልደረቦቼ ያሳዩኝ ልባዊ ፍቅር ማጨሴን እንዳቆም ረድቶኛል” ብሏል። ይሁን እንጂ ቤተሰቦችህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህ ድጋፍ እንኳ በቂ የማይሆንበት ጊዜ ይኖራል።
በግዋንዳስ የተባለ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ለ27 ዓመታት አጭሻለሁ፤ ይሁንና ማጨስ ለመተው የወሰንኩት መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ስለሆኑ ልማዶች ምን እንደሚል ሳውቅ ነው። የማጨሰውን ሲጋራ መጠን በመቀነስ ቀስ በቀስ ለመተው ሞክሬ ነበር። ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቆምኩ። ከባለሙያ የምክር አገልግሎት ለማግኘትም ሞከርኩ። ይህ ሁሉ ግን የፈየደልኝ ነገር አልነበረም። ይሁንና አንድ ቀን ማታ የልቤን አውጥቼ ወደ ይሖዋ አምላክ በመጸለይ ማጨሴን እንዳቆም እንዲረዳኝ ለመንኩት። በመጨረሻም ተሳካልኝ!”
ሌላው አስፈላጊ ነገር ሊያጋጥሙ ለሚችሉ መሰናክሎች ራስህን ማዘጋጀት ነው። እነዚህ መሰናክሎች ምንድን ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መድኃኒት መጠቀም ይኖርብሃል?
እንደ ኒኮቲን ፕላስተር (በውስጡ ጥቂት ኒኮቲን የያዘ ቆዳ ላይ የሚለጠፍ ነገር ነው) ያሉ ማጨስ ለማቆም ያግዛሉ የሚባሉ መድኃኒቶች ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚዛቅባቸው ሆነዋል። እንዲህ ያለውን ሕክምና ከመጀመርህ በፊት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ አስብ፦
ጥቅሞቹ ምንድን ናቸው? ብዙዎቹ መድኃኒቶች፣ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በመቀነስ ማጨስ የማቆም አጋጣሚህ ሰፊ እንዲሆን ይረዳሉ ተብሎ ይነገርላቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ መድኃኒቶች ዘላቂ ውጤት የማስገኘታቸው ጉዳይ በአንዳንዶች ዘንድ ጥርጣሬ ፈጥሯል።
አደጋዎቹ ምንድን ናቸው? አንዳንዶቹ መድኃኒቶች እንደማቅለሽለሽ፣ የመንፈስ ጭንቀትና ራስን የማጥፋት ሐሳብ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የማስከተል አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ለኒኮቲን ምትክ ተደርገው የሚሰጡ ሕክምናዎችን መውሰድ ኒኮቲኑን በሌላ መልክ ወደ ሰውነት ማስገባት መሆኑን መዘንጋት የለብህም፤ ኒኮቲኑ በምንም መልክ ይወሰድ ጉዳት ማስከተሉ ስለማይቀር አልሸሹም ዞር አሉ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን መድኃኒቶች የሚወስድ ሰው አሁንም ከሱሱ አልተላቀቀም ማለት ይቻላል።
ምን አማራጮች አሉ? በአንድ ጥናት እንደታየው ማጨስ ማቆም ከቻሉ ሰዎች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት ማጨስ ያቆሙት ያለምንም መድኃኒት እርዳታ በአንድ ጊዜ ነው።