ከልብ ምት በስተጀርባ ያለው ነገር
ከልብ ምት በስተጀርባ ያለው ነገር
● ልብህ በሰውነትህ ውስጥ ላለው የደም ዝውውር ሥርዓት እምብርት ከመሆኑም ሌላ ከሚገመተው በላይ ትጉህ ሠራተኛ ነው። ትልቅ ሰው ከሆንክ ልብህ በቀን ውስጥ ከ100,000 ጊዜ በላይ ሊመታ ይችላል። እንቅስቃሴ በማታደርግበት ጊዜም እንኳ የልብህ ጡንቻዎች ጠንክረው የሚሠሩ ሲሆን እንዲያውም በፍጥነት በምትሮጥበት ጊዜ የእግርህ ጡንቻዎች ከሚሠሩት በእጥፍ የሚበልጥ ከባድ ሥራ ያከናውናሉ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ልብህ የምቱን ፍጥነት በአምስት ሴኮንድ ውስጥ እጥፍ ሊያደርገው ይችላል። በአንድ ትልቅ ሰው ሰውነት ውስጥ ያለው የደም መጠን በግምት 5 ሊትር ነው ብለን ብንወስድ ግለሰቡ እንደሚያደርገው የእንቅስቃሴ መጠን ልቡ በደቂቃ ከ5 ሊትር አንስቶ እስከ 20 ሊትር የሚደርስ ደም ሊረጭ ይችላል።
የልብ ምትህን የሚቆጣጠረው አስገራሚ ንድፍ እንዳለው የሚነገርለት የነርቭ ሥርዓት ነው። ይህ የነርቭ ሥርዓት፣ በልብ ውስጥ ያሉት ደም ሰጪ ገንዳዎች ከአንድ ሴኮንድ ላነሰ ጊዜ ሳይኮማተሩ እንዲቆዩና በዚህም የተነሳ ደም ተቀባይ ገንዳዎች ከደም ሰጪ ገንዳዎች ቀድመው እንዲኮማተሩ በማድረግ ቅደም ተከተሉን ይቆጣጠራል። በነገራችን ላይ ሐኪሞች በልብ ትርታ ማዳመጫ አማካኝነት የሚሰሙት ድም ድም የሚል ድምፅ የሚመነጨው ክፍ ክዶች (valves) በሚዘጉበት ጊዜ ነው እንጂ የልብ ጡንቻዎች ጭብጥ ዘርጋ በማለታቸው የሚፈጠር ድምፅ አይደለም።
አንድ ቢሊዮን የልብ ምቶች
አንድ እንስሳ የአካሉ መጠን ከፍ ማለቱ ከልብ ምቱ መጨመር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ እንዲያውም በተቃራኒው እንስሳው በገዘፈ መጠን የልብ ምቱ አዝጋሚ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ዝሆን የልብ ምት በአማካይ በደቂቃ 25 ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ካናሪ የምትባለው ትንሽ ወፍ የልብ ምት በደቂቃ 1,000 ያህል ከመሆኑ የተነሳ ልቧ ‘ጥዝዝ . . .’ የሚል ድምፅ የሚያወጣ ይመስላል! የሰው ልጆችን ስንመለከት ደግሞ ሲወለዱ በደቂቃ 130 ያህል የነበረው የልብ ምታቸው እየቀነሰ በመምጣት ትልቅ ሰው ሲሆኑ 70 ገደማ ይሆናል።
አብዛኞቹ አጥቢ እንስሳት የሚኖሩት የልብ ምታቸው በግምት አንድ ቢሊዮን እስኪሞላ ድረስ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም የልብ ምቷ በደቂቃ 550 የሆነ አንዲት አይጥ ሦስት ዓመት ገደማ ልትኖር ትችላለች፤ በሌላ በኩል ግን በግምት የልብ ምቱ በደቂቃ 20 የሆነ ብሉ ዌል የሚባለው አንድ ዓሣ ነባሪ ከ50 ዓመት በላይ ሊኖር ይችላል። የሰዎች ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ዕድሜያችን በልባችን ምት ብዛት ቢወሰን ኖሮ በሕይወት የምንቆየው 20 ዓመት ገደማ ሊሆን ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ የአንድ ጤነኛ ሰው የልብ ምት ብዛት ሦስት ቢሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ሊደርስ ስለሚችል ከ70 ወይም ከ80 ለሚበልጡ ዓመታት መኖር ይችላል! *
እንደዚያም ሆኖ እኛ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ጥልቅ ምኞት ስላለን ማናችንም ብንሆን የልባችን ምት ብዛት እንዲወሰንና በዚያም መሠረት ዕድሜያችን እንዲሰላ አንፈልግም። በዚያ ላይ ይህ ምኞት አምላክ በውስጣችን ያስቀመጠው በመሆኑ ተፈጥሯዊ ነው። እንዲያውም የሞት መንስኤ የሆነው ኃጢአት የሚወገድበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። (ሮም 5:12) በዚህም ምክንያት ራእይ 21:3, 4 “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” በማለት ይናገራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 እዚህ ላይ የቀረቡት አኃዞች ግምታዊ ናቸው። የእያንዳንዱ ፍጥረት የልብ ምት ብዛትም ሆነ በሕይወት የሚቆይበት ዕድሜ ከአማካዩ በእጅጉ ሊለያይ ይችላል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የልብ ሞዴል
ቀኝ ደም ተቀባይ ገንዳ
ግራ ደም ተቀባይ ገንዳ
ቀኝ ደም ሰጪ ገንዳ
ግራ ደም ሰጪ ገንዳ