በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ”

“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ”

“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ”

ረኔ ጭንቀቱ ከአቅሟ በላይ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ባለቤቷ ማቲው ቋሚ ሥራ ካጣ ሦስት ዓመት አልፎታል። “ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ምንም አልቀረውም። ስለ ነገ ምንም ነገር አለማወቄ ተስፋ አስቆርጦኝ ነበር” በማለት ረኔ ትናገራለች። ማቲው የሚያስፈልጋቸውን እንዳላጡ በመግለጽ ሚስቱ እንዳትጨነቅ ለማረጋጋት ይጥር ነበር። እሷም “ቢሆንም ገና መቼ ሥራ አገኘህ? ገቢ ያስፈልገናል!” በማለት ትመልስለት ነበር።

ሥራ መፈናቀል ጭንቀት እንደሚያስከትል እሙን ነው። ሥራ የሌለው ሰው ‘ያለ ሥራ የምቆየው እስከ መቼ ነው? ሥራ እስካገኝ ድረስ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ማሟላት የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ማሰቡ አይቀርም።

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ማሰቡ ተገቢ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ ጭንቀትን ለማቃለል የሚያስችል ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ . . . እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።”—ማቴዎስ 6:34

የሚያስፈራችሁን ነገር ለይታችሁ እወቁ

ኢየሱስ ምንም ችግር እንዳልተከሰተ አድርገን እንድናስብ መናገሩ አልነበረም። ይሁን እንጂ ነገ ሊሆን ስለሚችለው ነገር መጨነቅ ዛሬ ያለብንን የስሜት ጫና ከማባባስ በቀር የሚፈይደው አይኖርም። እውነቱን ለመናገር ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ ነገ የሚሆነውን ነገር ለመለወጥ ያለን አቅም ውስን ነው። ይሁን እንጂ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ለመቋቋም እርምጃ መውሰድ እንችላለን።

ማድረግ የመናገርን ያህል ቀላል አይደለም ብለህ ታስብ ይሆናል። ልክ ነው! ለ12 ዓመታት ሥራ የነበረውና ይሠራበት ከነበረው ድርጅት የተፈናቀለ ባል ያላት ሬቤካ እንዲህ ብላለች፦ “ኃይለኛ ውጥረት ሲያጋጥም በትክክል ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም እንዲህ ማድረግ ነበረብን። ስለዚህ ራሴን ለመቆጣጠር ጥረት አደረኩ። በጣም የፈራኋቸው ነገሮች እንዳልተከሰቱ ስመለከት መጨነቅ ምንም ዋጋ እንደሌለው ተገነዘብኩ። አሁን ባሉብን ችግሮች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የሚያጋጥመንን ውጥረት ሁሉ ማስወገድ ችለናል።”

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘በጣም የምፈራው ነገር ምንድን ነው? የሚያስፈራኝ ሁኔታ የመከሰቱ አጋጣሚ ምን ያህል ነው? ሊደርስ ወይም ላይደርስ በሚችል ነገር ላይ መጨነቄ ኃይሌን እያሟጠጠብኝ ነው?’

ባላችሁ ነገር ረክታችሁ መኖርን ተማሩ

አመለካከታችን በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል” የሚል አመለካከት እንድንይዝ ይመክረናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ባለን ነገር ረክተን መኖር ሲባል ለምንፈልጋቸው ነገሮች ገደብ ማበጀትና ለዕለት የሚያስፈልጉን ነገሮች ሲሟሉልን በዚያ መርካት ማለት ነው። እንዲኖሯችሁ የምትመኟቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት መጣራችሁ ኑሯችሁን ቀላል እንዳታደርጉ እንቅፋት ከመሆን ውጪ የሚያስገኝላችሁ ጥቅም የለም።—ማርቆስ 4:19

ረኔ ራሷን በሐቀኝነት ከመረመረች በኋላ ባላት ነገር ረክታ መኖር ጀመረች። እንዲህ ትላለች፦ “መብራትም ሆነ ጋዝ አጥተን አናውቅም፤ መጠለያ አጥተንም ጎዳና ላይ አልወደቅንም። ዋናው ችግር እንዲህ ባለ ሁኔታ ኖረን የማናውቅ መሆናችን ሲሆን እንደ ቀደሙት ዓመታት እንድንኖር ያለኝ ፍላጎት ጭንቀቴን አባብሶብኛል።”

ረኔ ነገሮች ከአቅሟ በላይ እንደሆኑ እንዲሰማት ያደረገው ያለችበት ሁኔታ ሳይሆን አመለካከቷ እንደሆነ ወዲያውኑ ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “ስላለንበት ሁኔታ ሐቁን መቀበል ብሎም እንዲኖረን ስለምመኘው ሕይወት ማብሰልሰሌን ማቆም ነበረብኝ። አምላክ በየቀኑ በሚሰጠን ነገር ረክቼ መኖር እንዳለብኝ ከተገነዘብኩ በኋላ ይበልጥ ደስተኛ ሆኛለሁ።”

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ለዛሬ የሚያስፈልጉኝ ነገሮች ተሟልተውልኛል? ከሆነ ለነገ የሚያስፈልጉኝም ነገሮች እንደሚሟሉልኝ እርግጠኛ በመሆን ስለ ነገ መጨነቄን ትቼ ስለ ዛሬ ብቻ ማሰብ እችላለሁ?’

በአነስተኛ ገቢ መኖር ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የመጀመሪያው እርምጃ ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ነው። * ይሁን እንጂ ሥራ በማጣታችሁ ምክንያት ገቢያችሁ በሚያንስበት ጊዜ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላላችሁ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ሥራ ማግኘትና ሳይፈናቀሉ መኖር ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጥቅምት 2005 ንቁ! ከገጽ 3-11ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መንፈሰ ጠንካራ መሆን ይክሳል!

ፍሬድ ሥራ ፍለጋ ለሳምንታት ሲለፋ ከቆየ በኋላ አጋጣሚዎች ሁሉ እንደተዘጉበት ተሰምቶት ነበር። “የተሰማኝ ስሜት አውቶቡስ ተራ ቆማችሁ አንድ ሰው መጥቶ እንዲወስዳችሁ ስትጠብቁ ከቆያችሁ በኋላ ማንም ሳይመጣላችሁ ሲቀር ከሚሰማችሁ ስሜት ጋር የሚመሳሰል ነበር” በማለት ተናግሯል። ፍሬድ ከእሱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮችን ትቶ ማድረግ የሚችለውን ነገር ብቻ ለማድረግ ወሰነ። የሥራ ልምዱንና የትምህርት ደረጃውን በተመለከተ የሚገልጽ መረጃ ለብዙ ድርጅቶች ሌላው ቀርቶ የእሱ ሙያ እምብዛም የማያስፈልግበት በሚመስልበት ድርጅት እንኳ አስገባ። “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መሠረት ድርጅቶቹ የሚሰጡትን መልስ እየተከታተለ ለቃለ ምልልስ በደንብ ይዘጋጅ ነበር። (ምሳሌ 21:5) ፍሬድ ሲናገር “በአንድ ድርጅት ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ሥራ አስኪያጆች ፊት ቀርቤ ሁለት ጊዜ ቃለ ምልልስ ተደርጎልኛል” ብሏል። ይሁንና ፍሬድ መንፈሰ ጠንካራ መሆኑ ክሶታል። በመጨረሻም “ተቀጠርኩኝ!” በማለት ተናግሯል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከገቢ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር

ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ሥነ ምግባርህ ወይስ ገቢህ? ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ተመልከት።

“በአካሄዱ ነውር የሌለበት ድኻ፣ መንገዱ ጠማማ ከሆነ ባለጠጋ ይሻላል።”—ምሳሌ 28:6

“ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል።”—ምሳሌ 15:17

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንድ ሰው ገቢውን ማጣቱ ንጹሕ አቋሙን እንዳይጠብቅ አያደርገውም፤ እንዲሁም የግለሰቡን ተፈላጊነት አይቀንሰውም። በመሆኑም ረኔ ባለቤቷ ከሥራ ሲባረር ለልጆቿ እንዲህ ብላቸው ነበር፦ “ብዙ አባቶች ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ሄደዋል። የእናንተ አባት ግን አሁንም ከጎናችሁ ነው። ምን ያህል እንደሚወዳችሁና በችግሮቻችሁ ሁሉ እንደሚረዳችሁ ታውቃላችሁ። ከእሱ የተሻለ አባት ልታገኙ አትችሉም!”