ሌላኛውን ጉንጭ ማዞር ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሌላኛውን ጉንጭ ማዞር ሲባል ምን ማለት ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ “ክፉ ለሚያደርግባችሁ ሰው አጸፋ አትመልሱ፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 5:39
ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ክርስቲያኖች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ራሳቸውን ከጉዳት ለመከላከል ምንም ነገር ማድረግ እንደሌለባቸው መናገሩ ነበር? ክርስቲያኖች ሲበደሉ ዝም ብለው መመልከትም ሆነ ሕጋዊ ጥበቃ ከማግኘት ወደኋላ ማለት ይገባቸዋል?
ኢየሱስ ይህን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብና የአድማጮቹን ማንነት ከግምት ማስገባት አለብን። ኢየሱስ ይህን ምክር ከመስጠቱ በፊት አድማጮቹ ቀድሞውንም ያውቁት የነበረውን አንድ ሐሳብ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ጠቅሶ ነበር። “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል” ብሏቸው ነበር።—ማቴዎስ 5:38
ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ሐሳብ የሚገኘው በዘፀአት 21:24 እና በዘሌዋውያን 24:20 ላይ ነው። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሰው “ዓይን ስለ ዓይን” የሚለው ቅጣት ከአምላክ ሕግ ጋር በሚስማማ መልኩ ተፈጻሚነት አግኝቷል የሚባለው በዳዩ፣ ሁኔታውንና ድርጊቱን ሆነ ብሎ መፈጸም አለመፈጸሙን በሚያረጋግጡት ካህናትና ዳኞች ፊት ለፍርድ ከቀረበ በኋላ እንደነበረ ልብ ሊባል ይገባዋል።—ዘዳግም 19:15-21
ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን የዚህን ሕግ አፈጻጸም አዛቡት። በ19ኛው መቶ ዘመን በአዳም ክላርክ የተዘጋጀው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል፦ “አይሁድ ይህን [ይኸውም ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ የሚለውን] ሕግ የግል ቅራኔዎቻቸውንና በቂም በቀል መንፈስ ተነሳስተው የሚፈጽሟቸውን የተለያዩ የግፍ ተግባሮች ተገቢ አስመስለው ለማቅረብ እንደ ምክንያት አድርገው ሳይጠቀሙበት አልቀሩም። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከልክ ያለፈ የበቀል ድርጊት ይፈጽሙ የነበረ ሲሆን ተበቃዩ በእሱ ላይ ከደረሰበት እጅግ የከፋ ነገር በበደለው ሰው ላይ ይፈጽም ነበር።” ቅዱሳን
መጻሕፍት ግን በቂም በቀል ተነሳስቶ በሌላው ላይ ጉዳት ማድረስን ያወግዛሉ።ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ‘ሌላኛውን ጉንጭ ስለ ማዞር’ ያስተማረው ትምህርት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን ሕግ ትክክለኛ መንፈስ ያንጸባርቃል። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ጉንጫቸውን በጥፊ ሲመቱ ፊታቸውን መልሰው ሌላኛውን ጉንጫቸውን ለጥፊ ማቅረብ አለባቸው ማለቱ አልነበረም። በዛሬው ጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ በጥንት ዘመንም ጥፊ የሚሰነዘረው በአንድ ሰው ላይ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ ሳይሆን ግለሰቡን ለማዋረድና ጠብ ለመጫር ታስቦ ነው።
ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ አንድ ሰው ሌላውን ሰው በጥፊ በመምታት ወይም በአሽሙር በመውጋት ጠብ ለመጫር ቢፈልግ ተመቺው አጸፋውን ከመመለስ መቆጠብ እንዳለበት ለመግለጽ ነው። እንዲያውም ይህ ሰው ክፉን በክፉ የመመለስ እሽክርክሪት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገውን ድርጊት ላለመፈጸም መጣር ይኖርበታል።—ሮም 12:17
ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ “‘በእኔ ላይ እንደሠራብኝ እሠራለታለሁ፤ ስለ አድራጎቱም የጁን እመልስለታለሁ’ አትበል” ከሚለው የንጉሥ ሰለሞን አባባል ጋር በጣም ይመሳሰላል። (ምሳሌ 24:29) የኢየሱስ ተከታይ የሆነ አንድ ሰው ሌላኛውን ጉንጩን የሚያዞረው፣ ሌሎች እሱን ‘ጥል’ ውስጥ ለመክተት በሚያደርጉት ግፊት ባለመሸነፍ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:24
ራስን ስለ መከላከልስ ምን ሊባል ይችላል?
አንድ ክርስቲያን ሌላኛውን ጉንጩን ያዞራል ሲባል የኃይል ጥቃት ሲሰነዘርበት ራሱን አይከላከልም ማለት አይደለም። ኢየሱስ ራሳችንን መከላከል እንደሌለብን መናገሩ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በሌሎች ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዲሁም ሌሎች ለብቀላ እንድንነሳሳ እንዲያደርጉን መፍቀድ እንደሌለብን መግለጹ ነበር። በተቻለ መጠን ከጠብ ለመራቅ ስንል መሸሽ ብልህነት ሲሆን የወንጀል ድርጊት ሲፈጸምብን ራሳችንን ለመከላከልም ሆነ የፖሊስን እርዳታ ለመሻት እርምጃ መውሰዳችን ተገቢ ነው።
የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሕጋዊ መብታቸውን ማስከበር ተገቢ እንደሆነ በተሰማቸው ጊዜ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ አውለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሰብኩ የሰጣቸውን ተልእኮ ለመፈጸም እንዲችል መብቱን ለማስከበር በዘመኑ በነበረው ሕግ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ጳውሎስና ሚስዮናዊ ጓደኛው የነበረው ሲላስ በፊልጵስዩስ ከተማ ስብከታቸውን ሲያከናውኑ ሕግ ጥሳችኋል ተብለው በአካባቢው ባለሥልጣናት ታስረው ነበር።
በዚህ ጊዜ ሁለቱም በሕዝብ ፊት ከተገረፉ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወደ ወህኒ ተጣሉ። ጳውሎስ አጋጣሚውን ባገኘ ጊዜ ሮማዊ ዜግነቱ በሚያስገኝለት መብት ተጠቅሟል። ባለሥልጣናቱም ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነት እንዳለው ሲያውቁ፣ ሊከተል የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ከተማቸውን በሰላም ለቀውላቸው እንዲሄዱ ጳውሎስና ሲላስን ለመኗቸው። ስለዚህ ጳውሎስ ‘ለምሥራቹ በመሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን በማድረግ’ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—የሐዋርያት ሥራ 16:19-24, 35-40፤ ፊልጵስዩስ 1:7
ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማስከበር ሲሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመሟገት ተገደዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ለማድረግ የተገደዱት የዜጎቻቸውን ሃይማኖታዊ ነፃነት እንደሚያስከብሩ በሚናገሩ አገሮች ጭምር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ከወንጀልና ከራሳቸው ደኅንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድም ሌላኛውን ጉንጫቸውን እንዲያዞሩ ማለትም በደል ሲፈጸምባቸው እጃቸውን አጣጥፈው እንዲመለከቱ አይጠበቅባቸውም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችሏቸውን ሕጋዊ እርምጃዎች ይወስዳሉ።
በመሆኑም ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች፣ አንዳንድ ሕጋዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳሉ፤ ያም ሆኖ ውጤቱ አብዛኛውን ጊዜ ውስን እንደሚሆን ይገነዘባሉ። ስለሆነም እነሱም ልክ እንደ ኢየሱስ፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥማቸው አምላክ ሁሉንም ነገር በማመዛዘን እርምጃ እንደሚወስድና እሱ የሚያስፈጽመው ማንኛውም የበቀል እርምጃ ፍጹም ፍትሕ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ ይተዉታል። (ማቴዎስ 26:51-53፤ ይሁዳ 9) እውነተኛ ክርስቲያኖች በቀል የይሖዋ እንደሆነ ያስታውሳሉ።—ሮም 12:17-19
ይህን አስተውለኸዋል?
● ክርስቲያኖች የትኞቹን ድርጊቶች ከመፈጸም መራቅ አለባቸው?—ሮም 12:17
● መጽሐፍ ቅዱስ ራስን ለመከላከል በሕግ መጠቀምን ይከለክላል?—ፊልጵስዩስ 1:7
● ኢየሱስ በአባቱ ምን ይህል ይተማመን ነበር?—ማቴዎስ 26:51-53