ብቸኝነት የመገናኛ ዘዴዎች በሞሉበት ዓለም
ብቸኝነት የመገናኛ ዘዴዎች በሞሉበት ዓለም
ሞባይል ስልክ፣ ኢሜይል፣ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትባቸው ድረ ገጾች፣ ቻት ሩምና ወዘተ እያልን ብንዘረዝራቸው የአሁኑን ያህል የመገናኛ ዘዴዎች የበዙበትና በቀላሉ የሚገኙበት ዘመን ኖሮ አያውቅም። ሆኖም የመገናኛ ዘዴዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ ወጣት አረጋዊ ሳይል ብዙ ሰዎች በከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ይዋጣሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
ጆን ካቾፖ እና ዊሊያም ፓትሪክ የተባሉ ተመራማሪዎች ሎንሊነስ—ሂዩማን ኔቸር ኤንድ ዘ ኒድ ፎር ሶሻል ኮኔክሽን በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ብቸኝነትን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ጽፈዋል። እነዚህ ሰዎች የጠቀሱት አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው “እየጨመረ የመጣው በኢንተርኔት የመጠቀም ልማድ ከሰዎች ጋር በቀጥታ መነጋገርን እንዲተካ ሲደረግ ከኅብረተሰቡ የመራቅና በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት አጋጣሚ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።”
በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚታየው ጥድፊያ የበዛበት ሕይወት ከሰዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት መመሥረትን አስቸጋሪ ያደርገዋል። በሰዎች ገጽታ ላይ የሚነበበው ፈገግታና የመውደድ ስሜት ብዙውን ጊዜ በስልክ ወይም በኮምፒውተር በሚላክ መልእክት አማካኝነት ሊተላለፍ አይችልም።
ከላይ ያለው ሐሳብ በሥራ ቦታ የሚታይ ቢሆንም በቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ሁኔታ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል። በብዙ ቤቶች ውስጥ የቤተሰብ አባላት በየፊናቸው ስለሚሯሯጡ አብረው በመመገብ ወይም በመጨዋወት ጊዜ አያሳልፉም። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ልጆች የየራሳቸው ኮምፒውተር ስላላቸው ከተቀሩት የቤተሰባቸው አባላት ተነጥለው የሚኖሩ ያህል ነው። የሚገርመው ግን ብዙ ወጣቶች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ቢኖሯቸውም ብቸኝነት ያጠቃቸዋል።
ዛሬ ዛሬ የብቸኝነት ስሜት የጋብቻን ትስስርም እንኳ ሳይቀር ስጋት ላይ ጥሎታል። በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሐሳብ ልውውጥ አለመኖሩ ሁለቱ ሰዎች አብረው እየኖሩም የየራሳቸውን ሕይወት የሚመሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረገ ነው። ከሁሉ የከፋው የብቸኝነት ስሜት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛ እያለውም ብቸኝነት ሲያጠቃው ነው።
በተለይ ነጠላ ወላጆች ደግሞ ከብቸኝነት ስሜት ጋር ይታገሉ ይሆናል። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ የመገናኛ ዘዴዎች መብዛታቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዳይቀራረቡ ሊያደርግ ስለሚችል የብቸኝነት ስሜታቸው እንዲባባስ ያደርጋል። በተጨማሪም ብዙ ያላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ቢናፍቁም ስሜታዊ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ይቀራል።
ብቸኝነት፣ ለአልኮልና ለዕፅ ሱሰኝነት እንዲሁም ከልክ በላይ ለመብላት ልማድና ለሴሰኝነት የሚዳርግ አልፎ ተርፎም ራስን ወደ መግደል የሚመራ ማኅበራዊ መቅሰፍት ሆኗል። እንግዲያው ለብቸኝነት መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይህም ብቸኝነትን በመቋቋም ረገድ ስኬታማ ለመሆን የመጀመሪያው እርምጃ ነው።