“አንድ መዝሙር ብቻ እንኳ ሊሆን ይችላል”
“አንድ መዝሙር ብቻ እንኳ ሊሆን ይችላል”
● ጁሊያና የምትባል በፊሊፒንስ የምትኖር የመርሳት በሽታ የያዛት አንዲት ውድ አረጋዊት ክርስቲያን ነበረች። የገዛ ልጆቿን እንኳ ማስታወስ አትችልም ነበር። ያም ቢሆን እሷ ወደምትኖርበት አካባቢ በሄድኩ ቁጥር ጎራ እያልኩ እጠይቃት ነበር።
ጁሊያና የአልጋ ቁራኛ የነበረች ሲሆን በመስኮት በኩል ወደ ውጪ ከማማተር በስተቀር የምታደርገው ነገር አልነበራትም። እንደማታስታውሰኝ ስለማውቅ ከእሷ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ቀላል አልነበረም። ፍጥጥ ብላ ብታየኝም እንዳስታወሰችኝ የሚያሳይ ምንም ነገር ፊቷ ላይ አይነበብም ነበር። እኔም “አሁንም ስለ ይሖዋ ታስቢያለሽ?” ብዬ ጠየቅኳት። ተሞክሮ ከነገርኳት በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ብጠይቃትም እንደገባት የሚያመለክት ምንም ፍንጭ አልነበረም። በኋላም አንድ መዝሙር መዘመር ጀመርኩ። ቀጥሎ የሆነው ነገር ልብ የሚነካ ነበር!
ጁሊያና ፊቷን አዙራ ካየችኝ በኋላ አብራኝ መዘመር ጀመረች! ሙሉውን መዝሙር በዚህ አካባቢ በሚነገረው በተጋሎግ ቋንቋ በቃሌ ስለማልችለው ብዙም ሳይቆይ መዘመሬን አቆምኩ። ጁሊያና ግን መዘመሯን ቀጠለች። ሁሉንም ስንኞች አስታወሰቻቸው። እኔም ቶሎ ብዬ በአቅራቢያው ከምትገኝ አንዲት የይሖዋ ምሥክር የመዝሙር መጽሐፍ ተውሳ እንድታመጣልኝ አብራኝ የነበረችውን ሴት ጠየቅኳት። እሷም በፍጥነት መጽሐፉን ይዛ መጣች። የመዝሙሩን ቁጥር ባላስታውሰውም እንዳጋጣሚ መጽሐፉን ስከፍተው መዝሙሩ ያለበትን ገጽ አወጣሁ። በዚህ ጊዜ ሙሉውን መዝሙር አብረን ዘመርን! ጁሊያናን ሌላ መዝሙር ታስታውስ እንደሆነ ስጠይቃት ፊሊፒኖች የሚጫወቱትን አንድ የድሮ የፍቅር ዘፈን መዝፈን ጀመረች።
እኔም “ጁሊያና እሱን አይደለም፤ ከሬዲዮ የሰማሽውን ሳይሆን በመንግሥት አዳራሽ * የሚዘመረውን መዝሙር ዘምሪልኝ” አልኳት። ከዚያም ከመዝሙር መጽሐፋችን ላይ አንድ ሌላ መዝሙር አውጥቼ መዘመር ስጀምር እሷም አብራኝ ትዘምር ጀመር። በዚህ ጊዜ ዓይኖቿ በደስታ ያበሩ ነበር። ምንም ስሜት የማይነበብባት የነበረችው ጁሊያና ፊቷ በብሩህ ፈገግታ ተሞላ።
በዚህ ጊዜ የመዝሙሩ ድምፅ የመጣው ከየት እንደሆነ ለማወቅ በጎረቤት ያሉት ሰዎች ግልብጥ ብለው ወጡ። ከዚያም በመስኮት በኩል ቆመው እያዩን መዝሙራችንን ያዳምጡ ጀመር። ሙዚቃው የጁሊያናን ስሜት ሲቀሰቅሰው ማየት እንዴት የሚያስደስት ነበር! ሙዚቃው የመዝሙሩን ቃላት እንድታስታውስ አድርጓታል።
በአብዛኛው ሁኔታዎችን መረዳት ወይም ሐሳባቸውን መግለጽ የማይችሉ ሰዎችን ልብ ዘልቆ ስሜታቸውን የሚቀሰቅሰው ምን እንደሆነ ማወቅ ስለማይቻል ሳይሰለቹ መሞከሩ የተሻለ እንደሆነ ከዚህ ተሞክሮ ተገንዝቤያለሁ። ምናልባትም አንድ መዝሙር ብቻ እንኳ ሊሆን ይችላል።
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጁሊያና በሞት አንቀላፋች። የይሖዋ ምሥክሮች በ2009 ያዘጋጁትን ልብ የሚነካ አዲስ መዝሙር ሳዳምጥ ከጁሊያና ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ ትዝ አለኝ። አንተም በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች በመጠየቅ እነዚህን ልብ የሚነኩ ጣዕመ ዜማዎች ማግኘት ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ የሚያካሂዱበት ቦታ የሚጠራበት ስም ነው።