ከሁሉ ወደሚበልጠው የሩጫ ውድድር ውስጥ ገባሁ
ከሁሉ ወደሚበልጠው የሩጫ ውድድር ውስጥ ገባሁ
ካርል ኤሪክ በርግመን እንደተናገረው
በፍጥነት ስሮጥ በውስጤ ልዩ ስሜት ይሰማኝ ነበር። በተፈጥሮዬ ፈጣን ሯጭ ስለነበርኩ የአጭር ርቀት ሩጫ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ ያዘ።
በ1972 አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ በአንድ የስፖርት ክለብ ውስጥ ገባሁ። ታዋቂ ሯጭ ለመሆን ከፈለግሁ ከፊት ለፊቴ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀኝ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። በአጭር ርቀት ሩጫ ሻምፒዮን ለመሆን የተፈጥሮ ችሎታ ብቻውን በቂ አይደለም። ያም ቢሆን ጠንክሬ ለመሥራት ዝግጁ ነበርኩ።
በ22 ዓመቴ የፊንላንድ ብሔራዊ ቡድን አባል ሆንኩ። በቀጣዩ ዓመት በፊንላንድ ውስጥ ካሉ የ100 ሜትር ሯጮች የተሻለ አማካይ ሰዓት አስመዘገብኩ። ይሁንና ተረከዜ አካባቢ ባለው ጅማትና በቋንጃዬ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ችሎታዬን ሙሉ በሙሉ እንዳልጠቀም እንቅፋት ሆነብኝ። ይሁን እንጂ ለሩጫ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ ተሰጥኦ ያላቸውን አትሌቶች ወደማሠልጠኑ ሥራ ዞርኩ። በ1982 ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመማርና ምቹ የአየር ጠባይ ባለው በዚህ አካባቢ በስፖርት ሙያ ዘርፍ ለመሠማራት በማሰብ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ እቅድ አወጣሁ። የአውሮፕላን ቲኬት ሳይቀር ቆርጬ ነበር።
ሕይወቴን የለወጠው ነገር
ወደ ካሊፎርኒያ ለመሄድ ካሰብኩበት ቀን ጥቂት ቀደም ብሎ አንድ ምሽት ላይ የበሬ ደወል ተደወለ። በሩን ስከፍት ያገኘሁት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮችን ነበር። ሳያቸው የተረጋጉና ሥርዓታማ መሆናቸውን አስተዋልኩ፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ከአንድ ሯጭ የሚጠበቁ ናቸው። ወደ ቤት እንዲገቡ ከጋበዝኳቸው በኋላ ቁጭ ብለን መነጋገር ጀመርን። እውቀት የሚጨምር ውይይት ካደረግን በኋላ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ * የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ትተውልኝ ሄዱ። እኔም መጽሐፉን ማንበብ ጀመርኩ። መጽሐፉን ወደማጋመስ ስደርስ ያነበብኩት ነገር እውነት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ሴቶቹ ተመልሰው ሲመጡ የይሖዋ ምሥክር መሆን የምችለው እንዴት እንደሆነ ጠየቅኋቸው። እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚያስፈልገኝ ነገሩኝ።
መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ከመቀበል ባሻገር በምኖርባት በቫንታ ከተማ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መካፈል ጀመርኩ። በአዳራሹ የሚሰጠው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተገነዘብኩ። እንዲያውም የተማርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለምሰጠው ነገር ያለኝን አመለካከት ቀስ በቀስ እየለወጠው መጣ። ስለዚህ ወደ ጉዞ ወኪሉ ሄጄ ቲኬት የገዛሁበትን ገንዘብ አስመለስኩ። ከፊሉን ገንዘብ ለስብሰባ የሚሆነኝን ሙሉ ልብስ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሴንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቼን የምይዝበት ቦርሳ ገዛሁበት። ከዚያም በ1983 በሄልሲንኪ
በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።ሌሎች አትሌቶችም ከጎኔ ተሰለፉ
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየተማርኩ ስሄድ ያወቅኩትን ነገር ለጓደኞቼ በጉጉት መንገር ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ የምነግራቸው ነገር እውነት መሆኑን መቀበል ከበዳቸው። እንዲያውም አብዷል የሚል ወሬ ብዙም ሳይቆይ መናፈስ ጀመረ። ከዚያም ጓደኞቼ አንድ በአንድ እየራቁኝ ሄዱ። ከተጠመቅሁ በኋላም ለጤንነት ስል ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አደርግ ስለነበር ከአንዳንዶቹ አትሌቶች ጋር በሩጫ መወዳደሪያ ቦታ ላይ እንገናኝ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ለመወያየት አጋጣሚ ማግኘታችን በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ባደርግም አለማበዴን እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል።
ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ አትሌቶች መካከል በርካቶቹ የነገርኳቸው ነገር ምክንያታዊና በቁም ነገር ሊመረመር የሚገባው መሆኑን እየተገነዘቡ መጡ። ጸያፍ ቃላት መናገሬንም ሆነ የግልፍተኝነት ባሕርዬን እርግፍ አድርጌ እንደተውኩ አስተዋሉ። ከእነሱ መካከል የተወሰኑት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ፈቃደኞች ሆኑ። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖችን ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር እንደሚያመሳስለው ለሰዎች መንገር ያስደስተኝ ነበር። እኛ ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ገብተናል።—2 ጢሞቴዎስ 2:5፤ 4:7, 8
እንደ እውነቱ ከሆነ ሕይወታችን ትርጉም ያለውና በደስታ የተሞላ መሆኑ የተመካው በአትሌቲክስ ውድድሮች በማሸነፋችን ላይ ሳይሆን ፈጣሪያችንን የሚያስደስተውን ነገር በማድረጋችን ላይ ነው። ከአንዳንዶቹ አትሌቶች ጋር ያደርግኩት ውይይት ግባቸውን እንደገና እንዲመረምሩ ያነሳሳቸው ሲሆን ከእነሱም በርካቶቹ የእኔን ሕይወት የለወጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተቀበሉ። ደስ የሚለው ነገር፣ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ አምላክን በሚያገለግሉበት ጊዜ ለአትሌቲክስ ስፖርት የነበራቸውን ዓይነት ቅንዓት አሳይተዋል።
ከእነዚህም አንዷ የሆነችው ይቮኔ በሩጫ ልዩ ተሰጥኦ የነበራት የ800 ሜትር ርቀት ሯጭ ነበረች። በስካንዲኔቪያ አገሮች ካሉት የ800 ሜትር ርቀት ሴት ሯጮች መካከል በፍጥነት የሚወዳደራት አልነበረም፤ ከዚህም በላይ የፊንላንድን ብሔራዊ ክብረ ወሰን ይዛ ነበር። በአውሮፓውያን የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ፊንላንድን ወክላ በተሳካ ሁኔታ ሮጣለች። ካደረግነው ውይይት ይቮኔ በዚህ ዓለም ውስጥ ዝና ለማግኘት መጣጣር ከንቱ መሆኑን ማስተዋል ጀመረች። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ይህ ዓለም እንደሚያልፍና አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም እንደሚተካ ተገነዘበች።—1 ዮሐንስ 2:17
ብዙም ሳይቆይ ይቮኔ መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። በወቅቱ የፊንላንድ የሩጫ ብሔራዊ ቡድን አባል ከነበረው ጃውኮ ከተባለ ጎበዝ ሯጭ ጋር ለጋብቻ እየተጠናኑ ነበር። እሱም በአውሮፓና በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ፊንላንድን ወክሎ ተወዳድሯል። ከጊዜ በኋላ ይቮኔና ጃውኮ በአትሌቲክስ ስፖርት ለመቀጠል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተዛወሩ።
እዚያ እያሉም ይቮኔ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን የቀጠለች ሲሆን ጃውኮም አብሯት ማጥናት ጀመረ። ማጥናት የፈለገው ግን ይቮኔ ከምትማረው ነገር ላይ ስህተት ለማግኘትና አስተሳሰቧን ለማስተካከል ነበር። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልቡን ነካው። ይቮኔና ጃውኮ የተጋቡ ሲሆን በኋላ ላይ በመጠመቅ ሕይወታቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን አሳዩ። በዛሬው ጊዜ ሁለቱም አቅኚ (ሙሉ ጊዜያቸውን በስብከቱ ሥራ የሚያሳልፉ የይሖዋ ምሥክሮች) ሆነዋል።
በሴቶች የ400 ሜትር ርቀት ሩጫ ውድድር ሻምፒዮና የነበረችውን ባርብሮ የተባለች ፊንላዳዊትም መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችዬ ነበር። እሷም በአውሮፓ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ፊንላንድን ወክላ ተወዳድራ ነበር። ባርብሮና የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ የነበረው ባለቤቷ ጃርሞ ወደ ስዊድን ተዛወሩ። እዚያም ባርብሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን የቀጠለች ሲሆን ጃርሞም አብሯት ማጥናት ጀመረ። ሁለቱም የሕይወትን ዓላማ በመፈለግ ላይ ስለነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማሩ በኋላ በስዊድን ሳሉ ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ ጃርሞ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ የሆነ ሲሆን ሁለቱም በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እያገለገሉ ነው። በተጨማሪም ጃርሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።
የመሠከርኩላት ሌላዋ ሴት ደግሞ ሄዲ ትባላለች፤ በዚያን ወቅት በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ ትገኝ የነበረ ሲሆን እሷም የሩጫ ተሰጥኦ ነበራት። አሠልጣኟ ስለነበርኩ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንደነበራት አስተዋልኩ። በመሆኑም አንድ ቀን የአምላክን መንግሥትና ይህ መንግሥት በምድር ላይ የሚያመጣቸውን በረከቶች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ነገርኳት። “ቃል የተገቡልንን እነዚህን በረከቶች ልናገኛቸው እንደምንችል ታምኚያለሽ?” ብዬ ጠየቅኋት።—መዝሙር 37:11, 29፤ ማቴዎስ 6:9, 10
“አዎን” ብላ መለሰች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ትፈልግ ስለነበር አንዲት እህት እንድታስጠናት ዝግጅት አደረግሁላት። ሄዲም ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመጠመቅ ሕይወቷን ለአምላክ መወሰኗን አሳየች። ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲሄድ በመንፈሳዊ የጎለመሰች ውብ ሴት ሆነች፤ ከጊዜ በኋላም ከሄዲ ጋር ተጋባን። ሄዲ አሁንም ድረስ አምላክን ለማገልገል ቆራጥ
አቋም ያላት ግሩም አጋር ሆናልኛለች፤ በስፖርቱ ዓለም ቀጥላ ቢሆን ኖሮ ይህ ቆራጥነቷ ዝነኛ ሯጭ ያደርጋት ነበር።ስፖርተኛ የነበረው ታናሽ ወንድሜ ፒተር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርኩ ሰሞን ተቃውሞኝ ነበር። ከዚያም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ሰጠሁት። በኋላም ወደ እኔ መጥቶ “መጽሐፉን ማንበብ ጀምሬ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉንም ነገር መረዳት አልቻልኩም። ልትረዳኝ ትችላለህ?” አለኝ። አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲያስጠናው ዝግጅት አደረግሁለት፤ ለአራት ወራት ካጠና በኋላም ተጠመቀ። ከጊዜ በኋላ ትዳር የመሠረተ ሲሆን ሚስቱ አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው።
ሩጫዬን አላቆምኩም
ከመጠመቄ በፊትም እንኳን ሚስዮናዊ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ከተጠመቅሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ከገባሁ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባኝ ተረድቼ ነበር። እኔና ባለቤቴ ሄዲ ጊልያድ ማለትም ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ለመግባት አመልክተን የነበረ ሲሆን በ1994 ተጠራን። ከትምህርት ቤቱ ከተመረቅን በኋላ የሩሲያ ቋንቋ በብዛት በሚነገርባት በላትቪያ እንድናገለግል ተመደብን።
ከሶቪየት ኅብረት መፈራረስ ጋር በተያያዘ ሰዎች ሁሉም ነገር እንደጠበቁት ስላልሆነ አዝነውና ተበሳጭተው ነበር። ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የማይሰጠው የነበረ ከመሆኑም በላይ በሰዎች እጅ እንዳይገባ ታግዶ ነበር፤ እኛ በሄድንበት ጊዜ ብዙዎች መጽሐፉ የሚናገረውን ለማወቅ ፍላጎት እንዳላቸው አስተዋልን። ሩሲያኛ መማር ከገጠሙኝ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሁሉ ከባዱ ነበር። ይሁን እንጂ በላትቪያ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ስድስት ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች እንድጎበኝና እንዳበረታታ ተሾምኩ። ከታማኟ ሚስቴ ጋር በመሆን አሁንም ድረስ ይህን ሥራ እያከናወንኩ ነው።
ባለፉት ዓመታት፣ ለሕይወት ማለትም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚገኘው “እውነተኛ ሕይወት” በሚደረገው የሩጫ ውድድር ውስጥ የሚካፈሉ ብዙዎችን እድገት እንዲያደርጉ ለማሠልጠን ችያለሁ። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) አትሌቶች ሙሉ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ በሚያስችላቸው መንገድ ማሠልጠን ስሜታቸውን መረዳት ይጠይቃል። አሠልጣኙ፣ አትሌቶቹ ጠንካራ ጎናቸውን እንዲያጎለብቱና ድክመቶታቸውን እንዲቀርፉ ሊረዳቸው ይገባል። በጥረታቸው ወደፊት እንዲገፉና ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት ሞራላቸውን ማነሳሳት ያስፈልገዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ጎላ አድርጎ እንደገለጸው አንድን ክርስቲያን ከሯጭ ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር መኖሩ በጣም ያስገርመኛል። አንድ ሯጭ ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ትኩረቱን በልምምዱ ላይ ማድረግ ይኖርበታል እንጂ ስለማሸነፍ ብቻ ማለም የለበትም። ለራሱ ምክንያታዊ የሆኑ ግቦችን ያወጣል፤ እንዲሁም ባወጣው እቅድ መሠረት ግቦቹ ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጋል። ግቡ ላይ ካላነጣጠረና ከግቡ ለመድረስ መጣጣሩን ከተወ ቀደም ሲል የለፋው ልፋት ሁሉ መና ይቀራል። አንድ እውነተኛ ክርስቲያንም በተመሳሳይ ትኩረቱ ግቡ ላይ እንዲያነጣጥር ማድረግ አለበት።
በተጨማሪም አንድ አትሌት ስኬታማ እንዲሆን የወጣለትን የአመጋገብ ሥርዓት በጥብቅ መከተል አለበት። ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን መጥፎ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባቸው ትምህርቶችን አይመገብም ወይም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው “ከአጋንንት ማዕድ” አይካፈልም። በዚህ ፈንታ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያቀረበለትን ገንቢ መንፈሳዊ ምግቦች ይመገባል። (1 ቆሮንቶስ 10:21) ከዚህም በላይ አንድ ስኬታማ ሯጭ ችግሮች ሲያጋጥሙት አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ይቀጥላል። ስህተቶቹን አምኖ በመቀበል ማስተካከያ ያደርጋል። ጳውሎስ “እኔ መድረሻውን እንደማያውቅ ሰው አልሮጥም” ሲል ጽፏል። ከዚህ ይልቅ ከውድድሩ ውጪ እንዳይሆን ‘ሰውነቱን እንደሚጎስም’ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:24-27
እኔና ባለቤቴ ጤንነታችንን ለመጠበቅ ስንል አሁንም ድረስ የጂምናስቲክ ስፖርት መሥራት ያስደስተናል። እጅግ ድንቅ አድርጎ የፈጠረንን ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግደን ግን አንፈቅድለትም። (መዝሙር 139:14) የሁለታችንም ትኩረት ያረፈው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ወደፊት’ የሚመጣውን ‘የእውነተኛ ሕይወት’ ሽልማት በማግኘት ላይ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
ሐዋርያው ጳውሎስ በቅድመ ክርስትና ዘመን ስለኖሩት “የምሥክሮች ደመና” ከገለጸ በኋላ “እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ” በማለት አሳስቧል። (ዕብራውያን 12:1) በዚህ ሩጫ ከመካፈል የበለጠ ጊዜና ጉልበት ቢጠፋለት የማያስቆጭ ነገር የለም። ምክንያቱም ይህን ሩጫ በተሳካ ሁኔታ የሚያጠናቅቁ ሯጮች በሙሉ ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን መታተም አቁሟል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ እኔና ሄዲ፤ ከላይ ይቮኔ ከታች ደግሞ ጃውኮ ሴት ልጃቸውን ይዞ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ከሄዲ ጋር ስናገለግል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ2009 በሄልሲንኪ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ። በስተግራችን ይቮኔና ጃውኮ እንዲሁም በስተቀኛችን ጃርሞና ባርብሮ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Published in Aamulehti 8/21/1979