በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትኩስ ምግብ ከቤት ወደ ቢሮ በሙምባይ

ትኩስ ምግብ ከቤት ወደ ቢሮ በሙምባይ

ትኩስ ምግብ ከቤት ወደ ቢሮ በሙምባይ

በየዕለቱ ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ከቤት ወጥተህ ወደ ሥራ ትሄዳለህ። የምሳ ሰዓት ሲደርስ አንተ በምትወደው መንገድ ተቀምሞ ቤት የተዘጋጀ ምግብ ብታገኝ ደስ ይልሃል። ዳባዋላዎች ምስጋና ይድረሳቸውና በሙምባይ፣ ሕንድ የሚሠሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ምግብ ማግኘት ችለዋል፤ ዳባዋላዎች ቤት የተዘጋጀ ምግብ ለሰዎች በየሥራ ቦታቸው የሚያደርሱ ግለሰቦች ናቸው። *

አጋጣሚውን መጠቀም

በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በወቅቱ ቦምቤይ ተብላ ትጠራ የነበረችው ሙምባይ በማደግ ላይ ያለች የንግድ ማዕከል የነበረች ሲሆን በዚህች ከተማ የሚሠሩ የብሪታንያም ሆነ የሕንድ ነጋዴዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ለመድረስ ረዘም ያለ ርቀት መጓዝ ነበረባቸው። መጓጓዣዎቹ ቀርፋፋ ከመሆናቸውም ሌላ በከተማዋ የሚገኙት ምግብ ቤቶች በጣም ጥቂት ነበሩ። በመሆኑም በቤት የተዘጋጀ ምሳ እጅግ ተፈላጊ ነበር፤ ለዚህም ሲባል ቤት የተዘጋጀውን ምግብ ለቢሮ ሠራተኞች የሚያደርሱ አገልጋዮች ይቀጠሩ ጀመር። በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ የሥራ መስክ መፍጠር እንደሚቻል ያስተዋለ አንድ ግለሰብ፣ ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች ከገጠር በማምጣት በየቀኑ ከቤት ወደ ቢሮ ምግብ የማመላለስ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በዚህ መንገድ በትንሹ የተጀመረው ይህ ሥራ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ተስፋፍቷል።

ቤት የተዘጋጀ ምግብ ዛሬም ቢሆን ተፈላጊነቱ አልቀነሰም። እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ቤቶች ቁጥር ጨምሯል፤ ያም ቢሆን ቤት የተዘጋጀ ምግብ ብዙ ወጪ የማያስወጣ ከመሆኑም በላይ ተወዳጅ ነው። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች የጤና ችግር ስላለባቸው ለየት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ያስፈልጋቸዋል። ሌሎች ደግሞ በሃይማኖታቸው ምክንያት አንዳንድ ምግቦችን አይበሉም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ቀይ ሽንኩርት ሌሎች ደግሞ ነጭ ሽንኩርት አይመገቡም። በምግብ ቤት በሚዘጋጁ ምግቦች ውስጥ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ነገሮች ይጨመራሉ፤ ከቤት ወደ ቢሮ ምግብ የማድረስ አገልግሎት ግን ሰዎች በሚፈልጉት መንገድ የሚዘጋጁ ምግቦችን እንዲያገኙ ያስችላል።

እጅግ አስተማማኝ አገልግሎት

ዓመታት እያለፉ ቢሄዱም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል የሆነው ይህ ምግብ የማድረስ ዘዴ እየተስፋፋ ከመሄዱ ውጭ ብዙም አልተለወጠም። በአሁኑ ጊዜ ከ5,000 በላይ ወንዶችና ጥቂት ሴቶች በዚህ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል፤ በየቀኑ ከ200,000 በላይ ምሳዎችን በየሰፈራቸው ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በመውሰድ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚርመሰመስባት ከተማ ውስጥ በየቦታው ተበታትነው ለሚገኙ የቢሮ ሠራተኞች ያደርሳሉ። ዳባዋላዎቹ ምግቦቹን የሚያደርሱት 60 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ርቀት ውስጥ ሲሆን አንዳንዶቹ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ የምሳ ዕቃዎችን በጋሪ ላይ ጭነው በእግራቸው ይጓዛሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በብስክሌቶች ወይም ከከተማ ወጣ ብለው ወደሚገኙ አካባቢዎች በሚሄዱ ባቡሮች ይጠቀማሉ። የሚጠቀሙበት መጓጓዣ ምንም ይሁን ምን ምግቡን ለተላከለት ሰው ልክ በሰዓቱ ያደርሳሉ። እንዲያውም የምሳ ዕቃውን ሲያደርሱ ስህተት የመፈጸም አጋጣሚያቸው ከ6 ሚሊዮን 1 እንደሆነ ይነገርላቸዋል! እንዲህ ዓይነት ግሩም ስም ማትረፍ የቻሉት እንዴት ነው?

በ1956 ዳባዋላዎች ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ሌሎች ባለሥልጣናትን ያቀፈ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆነው ተመዘገቡ። ሠራተኞቹ በቡድን በቡድን የሚደራጁ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን ተቆጣጣሪ ይኖረዋል፤ ቡድኖቹ ራሱን ችሎ እንደሚንቀሳቀስ ድርጅት ሆነው ይሠራሉ። ይሁንና ሁሉም የድርጅቱ አባላት ባለ ሸሪኮችና የአክሲዮን ባለቤቶች እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሲሆን አገልግሎታቸው ስኬታማ እንዲሆን ያበቃውም ይህ አደረጃጀታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ከ100 ዓመት በላይ ቢሆናቸውም ሠራተኞቹ አንድም ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ አድርገው አያውቁም።

ዳባዋላዎች መታወቂያ ካርድ የሚይዙ ሲሆን በነጭ ሸሚዛቸው፣ ሰፊ በሆነው ሱሪያቸውና በነጭ ቆባቸው በቀላሉ ተለይተው ይታወቃሉ። ቆባቸውን ሳይደፉ ቢቀሩ፣ ያለ በቂ ምክንያት ቢዘገዩ ወይም ከሥራ ቢቀሩ አሊያም በሥራ ሰዓታቸው መጠጥ ሲጠጡ ቢያዙ መቀጫ ይከፍላሉ።

የዕለት ተዕለት ውሏቸው ምን ይመስላል?

ከጠዋቱ 2:30 ላይ ደንበኛቸው ቤት ሲደርሱ ሚስቱ ወይም ሌላ ሰው ያዘጋጁት ምሳ በዕቃ ወይም በዳባ ተቋጥሮ ይጠብቃቸዋል። የተለመዱት ዳባዎች አንዱ በአንዱ ላይ የተነባበሩ በርከት ያሉ የምሳ ዕቃዎች ያሏቸው ሲሆን አንድ ላይ አስሮ የሚይዛቸው የብረት ማቀፊያ አላቸው። ዳባዋላው ከአንድ አካባቢ ብዙ የምሳ ዕቃዎችን ይሰበስብና በብስክሌቱ ወይም በጋሪው ላይ ጭኖ ከሌሎቹ የቡድኑ አባላት ጋር ወደሚገናኝበት ባቡር ጣቢያ በፍጥነት ይገሰግሳል። በዚያም የፖስታ ቤት ሠራተኞች እንደሚያደርጉት የምሳ ዕቃዎቹን በአድራሻቸው መሠረት ይከፋፍሏቸዋል።

ዳባዋላዎቹ የምሳ ዕቃው ከየት አካባቢ እንደመጣ፣ በአቅራቢያው ያለው ባቡር ጣቢያ የትኛው እንደሆነና መድረሻው የት እንደሆነ እንዲሁም ግለሰቡ ያለበትን ሕንፃ ስምና ስንተኛ ፎቅ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ እንዲችሉ እያንዳንዱ የምሳ ዕቃ ላይ በፊደላት፣ በቁጥሮችና በቀለማት በመጠቀም ምልክት ይደረግበታል። ወደ አንድ አካባቢ የሚወሰዱት የምሳ ዕቃዎች እስከ 48 የሚደርሱ ዳባዎችን በሚይዝ ከእንጨት የተሠራ ረጅም የዕቃ መያዣ ላይ ይቀመጣሉ። ባቡሩ ሲመጣ የምሳ ዕቃዎቹ ከጋቢናው ቀጥሎ በሚገኝ ልዩ ክፍል ውስጥ ይጫናሉ። ከዚያም ባቡሩ ወደ አንድ መናኸሪያ ሲደርስ ዳባዎቹ በድጋሚ በመልክ በመልኩ ይለያዩና ወደመድረሻቸው ጣቢያ ይወሰዳሉ። እዚያም እንደገና ተለያይተው በብስክሌት ወይም በእጅ በሚገፋ ጋሪ አማካኝነት ወደ ደንበኛው ይወሰዳሉ።

እነዚህ የመጓጓዣ ዘዴዎች ጊዜ ቆጣቢ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ወጪ አያስወጡም። ከዚህም ሌላ ዳባዋላው ብስክሌቱን የሚነዳው በመንገድ ዳር ወይም በመኪኖች መሃል እየተሹለከለከ በመሆኑ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት አይዘገይም። በመሆኑም ምግቡ ልክ 6:30 ላይ ደንበኛው ቢሮ ይደርሳል። ከዚያም ታታሪው ዳባዋላ የራሱን ምሳ ከበላ በኋላ ከ7:15 እስከ 8:00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ባዶዎቹን የምሳ ዕቃዎች ይሰበስባል፤ ቀጥሎም የምሳ ዕቃዎቹን በየቤታቸው ያደርሳቸውና ዕቃዎቹ ታጥበው ለቀጣዩ ቀን ዝግጁ ይሆናሉ። ጠቅላላው ሥራ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ ከዱላ ቅብብሎሽ ውድድር ጋር በሚመሳሰል መልኩ ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ይከናወናል!

ዝቅተኛ መስሎ ቢታይም ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈ አገልግሎት

ዳባዋላዎች ያተረፉት ግሩም ስም ሳይስተዋል አልቀረም። አንዳንድ ድርጅቶች እነዚህ ሰዎች ዕቃ የሚያደርሱበትን ዘዴ በማጥናት በሌሎች የንግድ ዘርፎች ላይ ሊጠቀሙበት አስበዋል። ስለ ዳባዋላዎች የሚገልጹ ጥናታዊ ፊልሞች ተሠርተዋል። እንዲሁም እንከን የለሽ ሊባል የሚችል አገልግሎት በመስጠት ረገድ ባተረፉት ስም የተነሳ ከፎርብዝ ግሎባል ማጋዚን፣ ሲክስ ሲግማ የምሥክር ወረቀት አግኝተዋል። ዳባዋላዎች ዘ ጊነስ ቡክ ኦቭ ዎርልድ ሪከርድስ ላይ የተመዘገቡ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሃርቫርድ የቢዝነስ ትምህርት ቤት በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሰዋል። ዳባዋላዎችን አንድ የብሪታንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባልን ጨምሮ ትልቅ ሥልጣን ያላቸው ሰዎችም እንኳ ጎብኝተዋቸዋል፤ የብሪታንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆነው ሰው በሥራቸው እጅግ ከመደነቁ የተነሳ አንዳንዶቹን በእንግሊዝ በተካሄደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸዋል።

በዛሬው ጊዜ ዳባዋላዎች ትእዛዝ ለመቀበልና ለሒሳብ አያያዝ በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተሮች ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ የምሳ ዕቃ የሚያደርሱበት መንገድ አሁንም አልተለወጠም። በሙምባይ የሚገኙ በርካታ የቢሮ ሠራተኞች የምሳ ሰዓት እየተቃረበ ሲሄድ ቤት የተሠራ ትኩስ ምግብ ልክ በሰዓቱ ጠረጴዛቸው ላይ እንደሚቀርብላቸው ማወቃቸው ያስደስታቸዋል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ዳባ ማለት “የምሳ ዕቃ” ማለት ሲሆን ዋላ የሚለው ቃል ደግሞ ምግቡን የሚያደርሰውን ሰው ያመለክታል። ቃሉ በተለያየ መንገድ ሊጻፍ ይችላል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ዳባዎቹን” ወደ መድረሻቸው ለማጓጓዝ ባቡር ላይ ሲጭኑ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ “ዳባ” በቀላሉ ለመያዝና ለማጓጓዝ እንዲመች አንድ ላይ የሚደራረቡ የተለያዩ የምሳ ዕቃዎችን የያዘ ነው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ የንግድ ድርጅቶች “ዳባዋላዎች” የምሳ ዕቃዎቹን ለማድረስ ከሚጠቀሙበት ጊዜ ቆጣቢ ዘዴ ትምህርት ወስደዋል