የማከዴሚያው ለውዝ—የአውስትራሊያ ተወዳጅ ፍሬ
የማከዴሚያው ለውዝ—የአውስትራሊያ ተወዳጅ ፍሬ
የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ የሆኑት ዎልተር ሂል ረዳታቸው የነበረውን አንድ ወጣት በድንጋጤ ይመለከቱት ጀመር። ልጁ በደቡብ ምሥራቅ ኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ በሚገኝ አንድ ደን ውስጥ የሚበቅል አዲስ የተገኘ የዛፍ ዝርያ ፍሬ እየበላ ነው። ሂል የዚህ ዛፍ ፍሬ መርዛማ እንደሆነ ሰምተው ነበር። ልጁ ግን መሞት ይቅርና የሕመም ምልክት እንኳ አልታየበትም። እንዲያውም ልጁ ፍሬው ጥሩ ጣዕም እንዳለው አወቀ። በመሆኑም ሂል ራሳቸው አንድ ፍሬ ወስደው በመቅመስ ፍሬው ጣፋጭ መሆኑን አረጋገጡ። ወዲያው የማከዴሚያን ችግኞች በመላው ዓለም ለሚኖሩ ወዳጆቻቸውና የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪዎች መላክ ጀመሩ። *
ከ150 ዓመታት በኋላም በዛሬው ጊዜ የማከዴሚያ ለውዝ በመላው ዓለም ታዋቂና ተወዳጅ ነው። ክሮኒካ ሆርቲካልቱሬ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “ማከዴሚያ ልዩ ጣዕምና የሚያምር ዳለቻ ቀለም ያለው የሚቆረጠም ፍሬ መሆኑ በመላው ዓለም በጣም ተፈላጊ ከሆኑት የለውዝ ዝርያዎች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።” በመሆኑም የማከዴሚያ ለውዝ በአውስትራሊያ በጣም ተፈላጊ ከሆኑት ፍሬዎች መካከል የሚመደብ መሆኑ ምንም አያስደንቅም!
በቀላሉ የማይሰበር ቅርፊት
ከዓመት እስከ ዓመት ልምላሜውን የማያጣው የማከዴሚያ ዛፍ በአውስትራሊያ ምሥራቃዊ ዳርቻ በሚገኘው ከፊል ሐሩር አካባቢ ይበቅላል። ከዘጠኙ የማከዴሚያ ዝርያዎች መካከል ሁለቱ ዝርያዎች ቃጫ የሚመስል ነገር ያለው ሽፋን፣ ጥቁር ቡኒ ቀለም ያለው ክብ ቅርፊትና ብይ የሚያክል ዳለቻ ቀለም ያለው ሊበላ የሚችል ፍሬ ያፈራሉ።
ይሁን እንጂ የማከዴሚያ ለውዝን ቅርፊት መስበር በጣም አስቸጋሪ ነው። * አቦሪጂኖች በድንጋይ ይፈነክቱት ነበር። ከአካባቢው አትክልተኞች አንዱ የነበሩት ጆን ዎልፍረን መዶሻና የብረት መቀጥቀጫ ይጠቀሙ ነበር። እንዲያውም እኚህ ሰው በእነዚህ መሣሪያዎች በመጠቀም በ50 ዓመት ውስጥ ስምንት ሚሊዮን የሚያክሉ ፍሬዎችን መፈልቀቅ ችለዋል። ይህን ሥራ በማሽን መሥራት ይቻል ይሆን? የቀድሞዎቹ ማሽኖች የውስጠኛውን ፍሬ ይሰባብሩት ስለነበረ ተቀባይነት አላገኙም። ከጊዜ በኋላ ግን የተሻሉ ማሽኖች ተፈልስፈዋል።
ሌላው ችግር የዛፉን ችግኝ ማራባት ነበር። ከጥሩ ዛፍ ተወስደው የሚተከሉ ፍሬዎች አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ዘር አያፈሩም። እንዲሁም ዛፎቹን ለማዳቀል የተደረገው ጥረትም አልተሳካም። የሐዋይ ተመራማሪዎች ለችግሩ መፍትሔ እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ዛፉን በብዛት ለማልማት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ተመራማሪዎቹ ይህን ከፍተኛ ግኝት በማግኘታቸው ሐዋይ ብዙም ሳትቆይ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው የማከዴሚያ ምርት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን ማቅረብ ችላ ነበር። የማከዴሚያ ፍሬ የሐዋይ ለውዝ ተብሎ እስከመጠራት መድረሱ የሚያስደንቅ አይደለም።
ከዚያም በ1960ዎቹ ዓመታት የአውስትራሊያ ገበሬዎች በሐዋይ የተገኘውን ዘዴ በመጠቀም “ማከዴሚያን ለንግድ ለማቅረብ በሰፊው ማምረት ጀመሩ።” በመሆኑም የማከዴሚያ ኢንዱስትሪ በአውስትራሊያ እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ምርት 50 በመቶ የሚሆነውን ማምረት ችላለች። በተጨማሪም የማከዴሚያ ፍሬ በአፍሪካ፣ በእስያና በማዕከላዊ አሜሪካ ይበቅላል።
በአንድ የአውስትራሊያ እርሻ ላይ የተደረገ ጉብኝት
የንቁ! መጽሔት በኒው ሳውዝ ዌልስ በምትገኘው ሊዝሞር የተባለች ከተማ አቅራቢያ የማከዴሚያ እርሻ ካለው ከአንድሩ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “ጥቂት መደዳዎችን እያለፍን የተለያዩ የማከዴሚያ ዝርያዎችን አሰባጥረን እንተክላለን። ይህን የምናደርገው የተለያዩ ዝርያዎች እርስ በርሳቸው እንዲዳቀሉ ነው።” የንቁ! መጽሔት መገንዘብ እንደቻለው በአውስትራሊያ ከተተከሉት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በሐዋይ አዳቃዮች ዘንድ እውቅና የተሰጣቸው ዝርያዎች ናቸው። ይሁን
እንጂ በአሁኑ ጊዜ የአውስትራሊያ አዳቃዮች የተሻሉ ዝርያዎችን ለማስገኘት ዛፎቹን ከዱር ማከዴሚያዎች ጋር በማዳቀል ላይ ናቸው።ዛፎቹን ቀና ብለን ስንመለከት ጥቅጥቅ ካሉት ቅጠሎች መሃል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍሬዎች እንደ ኳስ ተንጠልጥለው ተመለከትን። ፍሬዎቹ ከስድስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ ዛፉ ላይ እንዳሉ ከጎመሩ በኋላ መሬት ላይ ይወድቃሉ። ከወደቁት ፍሬዎች መካከል አንዳንዶቹ የተበሳሱ እንደሆኑ ተመለከትን። አንድሩ “አይጦች በስምንት ሴኮንድ ውስጥ ቅርፊቱን ሊበሱት ይችላሉ። የዱር አሳሞችም የማከዴሚያ ፍሬዎችን ይወዳሉ” አለን። ጥቂት ረድፎችን ካለፍን በኋላ አንድሩ ቆም ብሎ ግማሽ ለግማሽ አፈር ውስጥ የተቀበረ ፍሬ በእግሩ ፈንቆሎ አወጣ። ሳቅ እያለም “ሦስት ሳንቲም አተረፍኩ ማለት ነው” አለ። ብዙ ገበሬዎች እንደ ቅርጫት ያለ መያዣና አጫጭር የፕላስቲክ ጣቶች ያሉት ማሽን በመጠቀም የወደቁ ፍሬዎችን ይሰበስባሉ። ከዚያም ፍሬዎቹ እዚያው እርሻ ላይ ተፈትገው ከተበጠሩ በኋላ ወደ ፋብሪካ የሚወሰዱ ሲሆን በዚያም ቅርፊታቸው ይፈነከታል። በመጨረሻም፣ ደረጃ ወጥቶላቸው ለሽያጭ በየቦታው ይላካሉ።
ጣፋጭና ለጤና ተስማሚ!
ጉብኝታችንን ከጨረስን በኋላ በእጃችን የያዝነውን የማከዴሚያ ለውዝ መብላት ጀመርን። ፍሬው ክሬም ክሬም የሚል እጅ የሚያስቆረጥም ጣዕም አለው። ይሁንና ለጤንነትስ ተስማሚ ነው? ስለ ማከዴሚያ ለውዝ የወጣ አንድ መንግሥታዊ መረጃ እንደገለጸው ከሆነ ፍሬው የሚይዘው የዘይት መጠን “በአብዛኛው ከ72 በመቶ የሚበልጥ ሲሆን በዚህ ረገድ ከየትኛውም የቅባት ለውዝ ይበልጣል”፤ የዚህ ፍሬ ዘይት አብዛኛው ክፍል ሞኖአንሳቹሬትድ የሚባለው ለጤና ተስማሚ የሆነው ዘይት ነው። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የማከዴሚያን ለውዝ በመጠኑ መመገብ ሰውነት ውስጥ ያለውን ጎጂ ኮሌስትሮልና ትራይግሊሰራይድ የተባለውን የስብ ዓይነት ለመቀነስ ከማስቻሉም በላይ የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳል።
ሰዎች ማከዴሚያ የተጨመረበትን የቸኮላት ከረሜላ፣ ውድ የሆነ ብስኩትና ምርጥ አይስክሬም መብላት ያስደስታቸዋል። ሌሎች ደግሞ ተቆልቶና ጨው ተጨምሮበት አሊያም ቅርፊቱን እየሰበሩ መብላት ይመርጣሉ። ምርጫቸው ምንም ሆነ ምን አንዴ የቀመሱት ሁሉ ለመድገም መፈለጋቸው አይቀርም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 ከዓመታት በፊት ካኒንግሃም (1828) እና ላይክሃርት (1843) የተባሉ አሳሾች የማከዴሚያ ፍሬዎችን የሰበሰቡ ቢሆንም እነሱ የሰበሰቧቸው ናሙናዎች ምንም ዓይነት መግለጫ ሳይጻፍባቸው በመጋዘን እንደተቀመጡ ቀርተዋል። በ1857 የሂል የሥራ ባልደረባ የነበሩት የሜልቦርኑ የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ ፈርዲናንድ ፎን ሙለር፣ ይህን የዛፍ ዝርያ የቅርብ ወዳጃቸው በነበሩት በዶክተር ጆን መካደም ስም ማከዴሚያ ብለው ሰየሙት።
^ አን.6 የደቀቀው የማከዴሚያ ቅርፊት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በፋብሪካ ውስጥ ሸካራ የሆኑ ነገሮችን ለማለስለስ ያገለግላል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቅርፊቱ ኃይል ለማመንጨት ያገለግላል
እጅግ ጠጣር የሆኑት የማከዴሚያ ቅርፊቶች ከቡኒ የድንጋይ ከሰል ጋር የማይተናነስ ሙቀት ወይም ኃይል መስጠት ይችላሉ። በመሆኑም አንድ የአውስትራሊያ ኃይል አቅራቢ ድርጅት በተረፈ ምርትነት የተጣሉ ቅርፊቶችን በመጠቀም ለማከዴሚያ ፍሬዎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ለሕዝብ ፍጆታ የሚውል ኤሌክትሪክ በማምረት ላይ ነው። ይህ የኤሌክትሪክ ማመንጫ በአውስትራሊያ ተረፈ ምርቶችን ወደ ኃይል ምንጭነት የቀየረ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ሲሆን ገበሬዎች ብዙ ቅርፊት ባቀረቡ ቁጥር የሚመነጨውም ኃይል እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአውስትራሊያ ገበሬዎች በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዛፎችን ይተክላሉ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
All photos pages 22 and 23: Australian Macadamia Society