ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ይስማማሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ ይስማማሉ?
“በተሠማራሁበት የሳይንስ መስክ አልፎ አልፎ አዲስ ነገር ሳገኝ ‘አሃ፣ አምላክ የሠራው በዚህ መንገድ ነው ማለት ነው’ ብዬ አስባለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች በሥራዬ ላይ ጉልህ ስፍራ የሚይዙ ከመሆኑም በላይ ያስደስቱኛል!”—የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሄንሪ ሼፈር
ብዙዎች፣ ገደብ የለሽ ማስተዋልና ኃይል ያለው አምላክ መኖሩን የሚጠቁመውን በተፈጥሮ ውስጥ ያለ ሕግና ሥርዓት፣ ዝንፍ የማይል ትክክለኝነት እንዲሁም ረቂቅነት በሚገባ እንዲረዱ በማስቻል ረገድ ሳይንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሳይንስ ከተፈጥሮ ጋር በተያያዘ ዝርዝር ጉዳዮችን ግልጽ በማድረግ ብቻ ሳይወሰን የአምላክንም አስተሳሰብ ለመረዳት እንደሚያስችል ያምናሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አመለካከት የሚደግፉ በርካታ ሐሳቦችን ይዟል። ሮም 1:20 እንዲህ ይላል፦ “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” በተመሳሳይም መዝሙር 19:1, 2 “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ። ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ በዙሪያችን ያለው ተፈጥሮ ብዙ ድንቅ ነገሮች ቢኖሩትም ስለፈጣሪያችን ሊገልጽልን የሚችለው በጣም ጥቂት ነገሮችን ብቻ ነው።
ሳይንስ ማስረዳት የማይችላቸው ነገሮች
ሳይንስ አምላክን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠት የማይችላቸው በርካታ እውነቶች አሉ። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ የሳይንስ ሊቅ በቸኮሌት ኬክ ውስጥ ያሉትን ሞለኪውሎች አንድ በአንድ ዘርዝሮ መግለጽ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሳይንቲስቱ ኬኩ ለምን ወይም ለማን እንደተጋገረ መናገር ይችላል? ሳይንቲስቱ ብዙ ሰዎች ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርገው ለሚመለከቷቸው እንደነዚህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኬኩን የጋገረውን ሰው መጠየቅ ያስፈልገዋል።
በተመሳሳይም ሳይንስ “በማስረጃ የተደገፉ ብዙ መረጃዎችን ያቀርባል። . . . ይሁን እንጂ ይበልጥ ልናውቃቸው የምንፈልጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም” በማለት ኦስትሪያዊው የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ኧርቪን ሽሮዲንገር ጽፈዋል። ይህም እሳቸው እንዳሉት “አምላክንና ዘላለማዊነትን” በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል፣ እንደሚከተለው ላሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው፦ አጽናፈ ዓለም የተፈጠረው ለምንድን ነው? እኛ የምንኖርባት ፕላኔት የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ጨምሮ ሕይወት ባላቸው ነገሮች የተሞላችው ለምንድን ነው? አምላክ በእርግጥ ሁሉን ቻይ ከሆነ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ከሞት በኋላ ዳግም የመኖር ተስፋ አለ?
ታዲያ አምላክ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል? አዎን፣ መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማግኘት ይቻላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ‘ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አምላክ ከራሱ ጋር ስለማይቃረን መጽሐፍ ቅዱስ በዙሪያችን ስላለው ዓለም የሚናገረው ሳይንሳዊ ሐሳብ ከሳይንሳዊ አመለካከት ጋር እንደሚስማማ ግልጽ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይስማማል? ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
ከዘመኑ እጅግ የመጠቀ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ
መጽሐፍ ቅዱስ ይጻፍ በነበረበት ዘመን፣ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ በርካታ አማልክት እንዳሉ እንዲሁም ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ የአየር ንብረትን፣ መዋለድንና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚቆጣጠሩት የተፈጥሮ ሕጎች ሳይሆኑ እነዚህ አማልክት እንደሆኑ ያምኑ ነበር። የጥንቶቹ ዕብራውያን ነቢያት ግን እንደዚህ ብለው አያምኑም ነበር። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አምላክ ተፈጥሮን በቀጥታ መቆጣጠር እንደሚችልና ይህንንም በተወሰኑ ወቅቶች እንዳደረገ ያውቁ ነበር። (ኢያሱ 10:12-14፤ ) ይሁን እንጂ እንግሊዝ በሚገኘው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሒሳብ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ሌኖክስ እንደተናገሩት የጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት “መጀመሪያውኑም በአማልክት ስለማያምኑ . . . አጽናፈ ዓለም በእነዚህ አማልክት ቁጥጥር ሥር ነው ከሚለው እምነት መላቀቅ አላስፈለጋቸውም። እንዲህ ከመሰለው አጉል እምነት ያዳናቸው የሰማይና የምድር ፈጣሪ በሆነ አንድ እውነተኛ አምላክ ላይ የነበራቸው እምነት ነው።” 2 ነገሥት 20:9-11
ይህ እምነት እነዚያን የጥንት ነቢያት ከአጉል እምነት ያዳናቸው እንዴት ነው? መጀመሪያ ነገር፣ እውነተኛው አምላክ አጽናፈ ዓለምን ዝንፍ በማይሉ ሕጎች ወይም ሥርዓቶች አማካኝነት እንደሚገዛ ስለገለጸላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከ3,500 ዓመታት በፊት ይሖዋ አምላክ አገልጋዩን ኢዮብን “የሰማያትን ሥርዐት ታውቃለህ?” በማለት ጠይቆት ነበር። (ኢዮብ 38:33) በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኤርምያስ ‘የሰማይና የምድር ሥርዐት’ በማለት ጽፎ ነበር።—ኤርምያስ 33:25
በመሆኑም በጥንት ዘመን ነቢያት በጻፏቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ያምኑ የነበሩ ሰዎች በሙሉ አጽናፈ ዓለም የሚገዛው በፈጠራ ታሪኮች ውስጥ ባሉ ግልፍተኛ አማልክት ሳይሆን የማሰብ ችሎታ ውጤት በሆኑ ሕጎች እንደሆነ ማወቅ ችለው ነበር። በዚህም የተነሳ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው እነዚህ ግለሰቦች እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃ ወይም ከዋክብት ያሉትን አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች አላመለኩም ወይም እነሱን በተመለከተ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ አመለካከት አልነበራቸውም። (ዘዳግም 4:15-19) ከዚህ ይልቅ እነዚህ ፍጥረታት የአምላክ ጥበብ፣ ኃይልና ሌሎች ባሕርያት መገለጫዎች እንደመሆናቸው መጠን ስለ እነሱ ሊያጠኑ እንደሚገባ ተረድተው ነበር።—መዝሙር 8:3-9፤ ምሳሌ 3:19, 20
በዛሬው ጊዜ እንዳሉት በርካታ ሳይንቲስቶች ሁሉ የጥንት ዕብራውያን ነቢያትም አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው ያምኑ ነበር። ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም ከ3,500 ዓመታት በፊት አምላክ ለአገልጋዩ ለኢዮብ ምድር ‘በባዶው ላይ’ ወይም በሕዋ ላይ ‘እንደተንጠለጠለች’ ገልጾለታል። (ኢዮብ 26:7) ከዚህም ሌላ ከ2,500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ምድር ክብ ወይም ሉል መሆኗን ጽፏል።—ኢሳይያስ 40:22 *
አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዙሪያችን ስላለው ተፈጥሮ የሚናገረው ሐሳብ ከሳይንሳዊ እውነቶች ጋር ይስማማል። እንዲያውም ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ መስማማት ብቻ ሳይሆን አንዱ የሌላው ማሟያ በመሆን ስለ አምላክ ይበልጥ እንድናውቅ ይረዱናል። ከሁለት አንዳቸውን ችላ ማለት ስለ አምላክ ለማወቅ የሚያስችለውን በር ከመዝጋት ተለይቶ አይታይም።—መዝሙር 119:105፤ ኢሳይያስ 40:26
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.14 ስለ አምላክ መኖርና መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ስለመሆኑ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚለውን ብሮሹርና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተሰኘውን መጽሐፍ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
ይህን አስተውለኸዋል
● ፍጥረት ስለ አምላክ ምን ይነግረናል?—ሮም 1:20
● ሳይንስ አምላክን በተመለከተ ለየትኞቹ እውነቶች ማብራሪያ ሊሰጥ አይችልም?—2 ጢሞቴዎስ 3:16
● የጥንቶቹ እውነተኛ የአምላክ ነቢያት ስለ ፍጥረት በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ አመለካከት እንዳይኖራቸው የረዳቸው ምንድን ነው?—ኤርምያስ 33:25
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አጽናፈ ዓለም የሚገዛው “የሰማይና የምድር ሥርዓት” ተብለው በተገለጹት ዝንፍ በማይሉ ሕጎች ነው።—ኤርምያስ 33:25