እረኛ መሆን ደስ ይላል
እረኛ መሆን ደስ ይላል
አሊምቤክ ቤክማኖቭ እንደተናገረው
በግ ማገድ የጀመርኩት ገና በሦስት ዓመቴ ሲሆን ቀስ በቀስ የእረኝነቱን ሥራ እየወደድኩት መጣሁ። አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ የተዋጣልኝ እረኛ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ ስለ ሌላ ዓይነት እረኝነት ማለትም ስለ መንፈሳዊ እረኝነት ተማርኩ። መንፈሳዊ እረኛ ሆኖ ማገልገል ከበግ እረኝነት የበለጠ ደስታ ያመጣልኝ እንዴት እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።
የተወለድኩት በ1972 ነው። የኪርጊስታን ዘር ያለው ቤተሰባችን በጣም ሰፊ ሲሆን አይሲክ ከል በሚባለው ውብ ሐይቅ ዳርቻ በምትገኘው በቺርፒክቲ መንደር ውስጥ እንኖር ነበር። በሐይቁ ዙሪያ ያለው ይህ አካባቢ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ግዛት የሆነችውን ኪርጊስታንን መጎብኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ተወዳጅ የቱሪስት መስሕብ ነው። በአሁኑ ጊዜ እኔና ባለቤቴ ጉልሚራ የምንኖረው ካደግኩበት ቀዬ 200 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘውና የኪርጊስታን ዋና ከተማ በሆነችው በቢሽኬክ ነው።
እረኛና በጎች
ልጅ ሳለሁ በጸደይ ወቅት በጎቹን ተራራ ላይ ወደሚገኝ የግጦሽ ስፍራ እንወስዳቸው ነበር። ይህ ስፍራ ከ3,000 ሜትር በሚበልጥ ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ተራራውን ለመውጣት የተወሰኑ ቀናት ይወስድብን ነበር። አንዳንድ እረኞች ወደ ግጦሹ ስፍራ ቶሎ ለመድረስ ሲሉ አቋራጭ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ በእነዚህ አቋራጭ መንገዶች አካባቢ ሸለቆና ገደሎች ስለሚበዙ በጎች ጥቂት እንኳ ከመንጋው ነጠል ካሉ ጉዳት ሊያገኛቸው አልፎ ተርፎም ሊሞቱ ይችላሉ።
እንዲህ ባሉ መንገዶች ላይ ቀበሮዎች በጎችን ሲያስደነብሩና ጥቃት ሲሰነዝሩባቸው መመልከት የተለመደ ነበር፤ ቀበሮዎቹ አንዳንዶቹን በጎች ከመንጋው እንዲነጠሉ ካደረጓቸው በኋላ ይወስዷቸው ነበር። ስለዚህ አጎቴ ተጨማሪ ቀን መጓዝ ቢጠይቅበትም እንኳ ለመሄድ የሚመርጠው ቀና በሆነውና እምብዛም ለአደጋ በማያጋልጠው መንገድ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ፈጠን ፈጠን እያልኩ ስሄድ አጎቴ ረጋ እንድል ይነግረኛል። “አሊምቤክ፣ ስለ ራስህ ሳይሆን ስለ በጎቹ አስብ” ይለኝ ነበር።
ሌሊት ላይ በጎቹን ከአደጋ ለመጠበቅ ውብ በሆነው ተራራ ላይ ጊዜያዊ ጉረኖ ወይም በረት እንሠራ ነበር። አንዳንድ እረኞች በጠዋት መነሳት ስለማይወዱ በጎቹን ወደ ግጦሽ ስፍራ የሚወስዷቸው ከረፋድ በኋላ ነበር። በጎቹ ወደ ግጦሹ ስፍራ ደርሰው መጋጥ ሳይጀምሩ የፀሐዩ ትኩሳት ይበረታል።
ብዙም ሳይቆይ በጎቹ አንገታቸውን ደፍተው እያለከለኩ ተጠጋግተው ይቆማሉ። ፀሐዩን ተቋቁመው በደንብ መጋጥ ስለማይችሉ አቅመ ቢስና ከሲታ ይሆናሉ። አርፍደው ከሚነሱት እረኞች በተቃራኒ አጎቴ ጎሕ ከመቅደዱ በፊት ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ይነሳ ነበር። በጎቹን ይዞ ጥሩ ግጦሽ ወዳለበት ስፍራ የሚደርሰው ገና ፀሐይ ሳትወጣ ነው። በመሆኑም በጎቹ መንፈስን በሚያድሰው የማለዳ አየር ዘና ብለው
መጋጥ ይችላሉ። ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደሚሉት ነው፤ “በጎቹን አይቶ እረኛውን።”የበጎቹን ጤንነት ለመፈተሽና አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት አመቺ የሆነው ጊዜ በደንብ ግጠው አረፍ የሚሉበት ሰዓት ነው። በበጎች እምብርት ላይ እንቁላላቸውን የሚጥሉ ዝንቦች ለበጎቻችን ጤንነት ዋነኛ ጠንቅ ነበሩ። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት በግ እምብርቱ ያብጥና ይቀላ ነበር። ችግሩ በጊዜ ካልታወቀ በጉ ሥቃዩ በጣም ሊበረታበትና ከመንጋው በመነጠል ለሞት ሊዳረግ ይችላል። በመሆኑም እርዳታ ለመስጠት ስንል በየቀኑ ማለት ይቻላል በጎቹን እንፈትሽ ነበር። እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፤ ሆኖም በጎቻችን ጤነኞችና ደስተኞች መሆናቸውን ስንመለከት ልፋታችን መና እንዳልቀረ ይሰማናል።
በየቀኑ ማታ ማታ በጎቹ ከግጦሽ ተመልሰው ወደ ጉረኖው ሲገቡ እንቆጥራቸው ነበር። የጉረኖው መግቢያ ጠባብ በመሆኑ በአንድ ጊዜ የሚያሳልፈው ግፋ ቢል ሦስት ወይም አራት በግ ሊሆን ይችላል። በጎቻችን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቢሆኑም አቆጣጠሩን በደንብ ስለምንችልበት በ15 ወይም በ20 ደቂቃ ውስጥ እስከ 800 የሚደርሱ በጎችን መቁጠር እንችል ነበር። ይህን ማድረግ ብዙ ልምምድ ቢጠይቅም እንዴት በአጭር ጊዜ መቁጠር እንደሚቻል ተምረናል!
አንድ በግ እንደጎደለ ከተገነዘብን አጎቴ ጠመንጃና በትር በመያዝ የጠፋውን በግ ፍለጋ ይሄዳል፤ ድቅድቅ ባለ ጨለማና በዝናብ ውስጥ ሳይቀር አጎቴ ለአንድ በግ ሲል ይሄድ ነበር። ከዚያም ጮክ ባለ ድምፅ ይጣራል። ድምፁ አውሬዎች ፈርተው እንዲሸሹ ያደርግ ነበር። በጉ ግን ድምፁን ሲሰማ ምን ያህል የደኅንነት ስሜት ሊሰማው እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ።
የበጎቹን መልክ ወይም ጠባይ በማየት ለእያንዳንዳቸው ስም እናወጣላቸው ነበር። በአንድ መንጋ ውስጥ ምንጊዜም አስቸጋሪ በጎች አይጠፉም ነበር። ምክንያቱ በውል ባይታወቅም እነዚህ በጎች እረኛቸውን መታዘዝ አይፈልጉም። አንዳንድ ጊዜ ሌሎቹ በጎችም ዓመፀኛውን በግ ወደመከተል ያዘነብላሉ። ስለዚህ እረኛው አስቸጋሪ የሆነውን በግ ለማሠልጠንና ጠባዩን ለማረም ጥረት ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ ዓይነቱን በግ ጉረኖው ውስጥ ብቻውን እንዲውል ይተወዋል። ከዜ በኋላ አንዳንዶቹ በጎች እርማቱን ተቀብለው የእረኛውን መመሪያ መከተል ይጀምራሉ። በአስቸጋሪነቱ የሚቀጥል በግ ግን እራት ላይ ይቀርባል።
ለየት ያለ እረኝነት
በ1989 ማርሻል አርት የተማርኩ ሲሆን በኋላም በዚህ ስፖርት የተካንኩ ሆንኩ። በቀጣዩ ዓመት የሶቪየት ጦር ሠራዊትን እንድቀላቀል ተመለመልኩ። ሩሲያ በሚገኘው የጦር ሠራዊት ውስጥ እያገለገልኩ ሳለሁ እንደ እኔው ማርሻል አርት የተማሩ ጓደኞቼ የራሳቸውን የወሮበሎች ቡድን አደራጅተው ነበር። ወደ አገሬ ወደ ኪርጊስታን ስመለስ እነሱን ከተቀላቀልኩ የፈለግሁትን ሁሉ እንደማገኝ ነገሩኝ። ይሁን እንጂ በዚያው ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ጀምሬ ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ ‘ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ሲያስጨንቁኝ ለኖሩ ጥያቄዎች መልስ ሰጡኝ። ሞት የመጣው የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት በመሥራቱ እንደሆነ ካደረግነው ውይይት ተረዳሁ። (ሮም 5:12) በተጨማሪም እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን አዳኛችን እንዲሆን እንደላከው ብሎም በእሱና በልጁ የምናምን ከሆነ ከአዳም የወረስነው ኃጢአት እንደሚደመሰስልን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ። ወደፊት ኃጢአታችን ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስልን አምላክ ለሰው ዘር ባወጣው የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር እንችላለን።—መዝሙር 37:11, 29፤ 83:18፤ ዮሐንስ 3:16, 36፤ 17:1-5፤ ራእይ 21:3, 4
የይሖዋ ምሥክሮቹ ለጥያቄዎቼ በጣም ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግር ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ስለሰጡኝ “መሆን ያለበት እንዲህ ነው!” በማለት አድናቆቴን ለመግለጽ ተገፋፋሁ። ከዚያ በኋላ ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ወዳጅነት መቀጠል አልፈለግሁም። በተደጋጋሚ ወደ ቡድናቸው እንድመለስ ለማድረግ ሞክረው ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመማርና ተግባራዊ ለማድረግ የነበረኝ ከፍተኛ ፍላጎት ማባበያቸውን ለመቋቋምና መንፈሳዊ እረኛ ለመሆን ረድቶኛል።
በዚያ ሰሞን በአካባቢያችን ታዋቂ የሆነች ተአምራዊ ፈውስ የምታከናውን አንዲት ሴት እናቴን እየመጣች ትጠይቃት ነበር። አንድ ቀን ቤት ስደርስ ሴትዮዋ ከሙታን ጋር ለመገናኘት መናፍስታዊ ድርጊት እየፈጸመች ነበር። እሷም አንድ ልዩ ስጦታ እንዳለኝ ከገለጸችልኝ በኋላ ወደ መስጊድ ሄጄ ክታብ እንድቀበል አበረታታችኝ፤ ክታቡ እንደሚረዳኝ በእርግጠኝነት ትናገር ነበር። እሷ ያለችውን ብፈጽም የመፈወስ ስጦታ እንደምቀበል ልታሳምነኝ ተቃርባ ነበር።
በማግሥቱም መጽሐፍ ቅዱስ ወደሚያስጠኑኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሄድኩና ስለ ሴትዮዋ ነገርኳቸው። እነሱም ማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት ከአጋንንት ጋር ግንኙነት ስላለው ይሖዋ እንደሚቃወመው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዘዳግም 18:9-13) በአጋንንቱ ተጽዕኖ የተነሳ ለጥቂት ቀናት ሌሊት ሌሊት መተኛት አልቻልኩም ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ ሲያስተምሩኝ ቅዠቱ ወዲያውኑ ለቀቀኝ። እውነተኛ የሆነውን እረኛ ይሖዋን እንዳገኘሁት እርግጠኛ ሆንኩ።
አሳዩኝ። (ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙሮችን የጻፈው ዳዊትም በልጅነቱ የበግ እረኛ እንደነበረ ተማርኩ። ዳዊት ይሖዋን “እረኛዬ” በማለት የጠራው ሲሆን ለእሱ የነበረውን ስሜት የገለጸበት መንገድ በጥልቅ ነካኝ። (መዝሙር 23:1-6) “የበጎች እረኛ” ተብሎ የተጠራውን የይሖዋን ልጅ ኢየሱስን ለመምሰል ፍላጎት አደረብኝ። (ዕብራውያን 13:20) በ1993 መጀመሪያ አካባቢ በቢሽኬክ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
ወሳኝ የሆነ ስብሰባ
በርካታ ቁጥር ያላቸው ዘመዶቼና ጎረቤቶቼ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት መሰብሰብ ጀመሩ። ወደ 70 የሚጠጉ የመንደራችን ነዋሪዎች በአይሲክ ከል ሐይቅ አጠገብ ይሰበሰቡ ነበር። የአካባቢው ምክር ቤት ኃላፊ የሆነው አንድ ዘመዴ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። እሱም ስለ አዲሱ እምነታችን ማስረዳት እንድንችል አንድ ትልቅ ስብሰባ እንደሚያዘጋጅ ተናገረ። ይሁን እንጂ የአካባቢው የሃይማኖት መሪዎች ሕዝቡ የስብከት ሥራችንን እንዲቃወም መቀስቀስ ጀመሩ። ለስብሰባ በምንገናኝበት ወቅት አጋጣሚውን ተጠቅመው ሕዝቡን በእኛ ላይ ለማስነሳት አሴሩ።
በቀጠሮው ቀን በአቅራቢያው ካሉ ሦስት መንደሮች የመጡትን ጨምሮ አንድ ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ። በስብሰባው ላይ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች የተገኙ ሲሆን ከእነሱም አንዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነታችን ማስረዳት ጀመረ። አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሕዝቡ መሃል አንድ ሰው ተነስቶ ከፍ ባለ ድምፅ ጠብ የሚያነሳሱ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመረ። ከዚያም የሐሰት ውንጀላዎችና ዛቻዎች ከየአቅጣጫው መሰንዘር ቀጠሉ፤ ሁኔታው እየተባባሰ በመሄዱ ሕዝቡ ሊደበድበን ተነሳ።
በዚህ ጊዜ በቅርቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው ታላቅ ወንድሜ ለእኛ ወግኖ ተነሳ። ወንድሜ በድብድብ የታወቀ ስለሆነ በሁሉ ዘንድ የሚፈራና የሚከበር ሰው ነበር። ወንድሜ በእኛና በጠበኞቹ መሃል በድፍረት በመግባት ስለተከላከለልን ጫፋችንን ሳይነኩን መሄድ ቻልን። በዚያ ስብሰባ ከተገኙት ውስጥ ብዙዎቹ በቀጣዮቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በዛሬው ጊዜ በመንደራችን ካሉት ወደ 1,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች መካከል ከ50 በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
አንዲት የእረኛ ልጅ
ነሐሴ 1993 በሞስኮ፣ ሩሲያ ከተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ከኪርጊስታናውያን መንደር ከመጣች ጉልሚራ የምትባል የይሖዋ ምሥክር ጋር ተዋወቅሁ። የእሷ አባትም የበግ እረኛ ነበር። በ1988 በሶቪየት ኅብረት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ገና በእገዳ ሥር ሳለ የጉልሚራ እናት፣ አክሳሚ ከተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። አክሳሚ የተጠመቀችው በ1970ዎቹ ሲሆን በአካባቢው ካሉት ኪርጊስታናዊ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የመጀመሪያዋ ነች።
ብዙም ሳይቆይ ጉልሚራ፣ እናቷ ከአክሳሚ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በምታጠናበት ጊዜ አብራ መገኘት ጀመረች። በ1990 ሁለቱም ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ጉልሚራ የተማረችው ነገር ልቧን ስለነካው ወዲያውኑ አቅኚ በመሆን በስብከቱ ሥራ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ ጀመረች።
የምኖረው ጉልሚራ ካለችበት 160 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ስለነበር በስብሰባው ላይ ከተዋወቅን ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የምንተያየው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። መጋቢት 1995 ከእሷ ጋር በደንብ ለመቀራረብ ወሰንኩ፤ በመሆኑም አንድ ቀን ጠዋት እሷ ወዳለችበት ሄድኩ። ቤቷ ስደርስ፣ በማግሥቱ 5,633 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የሩሲያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለማገልገል ልትሄድ መሆኗን ስሰማ ክው ብዬ ቀረሁ!
በዚህ ጊዜ እኔም በአቅኚነት አገለግል የነበረ ከመሆኑም ባሻገር በኪርጊስታን ቋንቋ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ስላልነበሩን ሩሲያኛ መማር ጀምሬ ነበር። እኔና ጉልሚራ ለሦስት ዓመት ያህል በደብዳቤ እንገናኝ የነበረ ሲሆን በመንፈሳዊ ነገሮች ዙሪያ ሐሳብ መለዋወጥ እንድንችል ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራምም ነበረን። ይህ በእንዲህ እንዳለ በባሊክቺ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመው በኪርጊስታን ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ አገለግል ነበር።
ከጉልሚራ ጋር ይሖዋን ማገልገል
በ1998 ጉልሚራ ለእረፍት ወደ ኪርጊስታን መጣችና ተጋባን። እኔም ከእሷ ጋር በሩሲያ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ። የሩሲያን ቋንቋ መማር በመጀመሬ በጣም ተደሰትኩ! ከጊዜ በኋላ በኪርጊስታን ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በሚተረጉመው የትርጉም ቡድን ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። ጥበብና ትዕግሥት እንዲሰጠኝ ይሖዋን ለመንኩት። እርግጥ የሥራ ባልደረባዬ ጉልሚራም ከፍተኛ እርዳታ አበርክታልኛለች።
በ2004 የትርጉም ቡድናችን ወደ ቢሽኬክ ተዛወረ፤ እኔም በኪርጊስታን ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት እንዲከታተል በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ እንዳገለግል ስለተመደብኩ ወደዚያው አመራሁ። በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ በኪርጊስታን ቋንቋ የሚመሩት ጉባኤዎች ሰባት ሲሆኑ በሩሲያኛ የሚመሩ ጉባኤዎች ደግሞ ከ30 በላይ ነበሩ። አሁን ግን በኪርጊስታን ቋንቋ የሚመሩ ከ20 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎችና በርካታ ቡድኖች አሉ፤ በሌላ አባባል በኪርጊስታን ካሉት 4,800 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ውስጥ 40 በመቶ ገደማ የሚገኙት በእነዚህ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ ነው።
እኔና ጉልሚራ ለአገልግሎታችን እንዲረዳን እንግሊዝኛ ለመማር ወሰንን። ይህ ደግሞ በ2008 በዩናይትድ ስቴትስ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተጋብዘን በሄድንበት ወቅት ጠቅሞናል። እዚያም በየአገራቸው ያለውን የስብከት ሥራ በበላይነት ለሚመሩ ወንድሞች በተዘጋጀው ልዩ ትምህርት ቤት ተካፈልኩ።
አሁን እኔና ጉልሚራ በኪርጊስታን ያሉትን ሕዝቦች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የተሻለ ብቃት እንዳገኘን ይሰማናል። ያሳለፍናቸው ጊዜያት ይሖዋ በእርግጥም አፍቃሪ እረኛ እንደሆነ በገዛ ዓይናችን ለመመልከት አስችለውናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የሚከተለው መዝሙር በራሴ ሕይወት ውስጥ እንደተፈጸመ ይሰማኛል፦ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።”—መዝሙር 23:1-3
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጎቻችን በግጦሽ ስፍራ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመንጋው የጠፋ በግ እንደሌለ ለማረጋገጥ በየዕለቱ ማታ ማታ እንቆጥራቸው ነበር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ከጉልሚራ ጋር