በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት መመታት

በታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት መመታት

በታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት መመታት

ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ኦንላይን በቅርቡ በዓለማችን ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ ውድቀት “ባለፉት ትውልዶች በሙሉ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ቀውስ” በማለት ጠርቶታል። በዩናይትድ ስቴትስ ከ2007 ጀምሮ የደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ እጅግ ከባድና በብዙ አገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ‘ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት’ የሚል ልዩ ስያሜ ተሰጥቶታል።

የኢኮኖሚ ውድቀቱ መንስኤ ምንድን ነው? ኒውስዊክ መጽሔት “[ሰዎች] ኃላፊነት በጎደለው ስሜት የመበደር አባዜ የተጠናወታቸው መሆኑ ነው” በማለት በአጭር አነጋገር መልሱን ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነን ነገር ለመግዛት የመበደር አባዜ የተጠናወታቸው ለምንድን ነው?

ለዚህ ምክንያቱ ስግብግብነትን የሚያበረታታው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። ሥርዓቱ የሚያስተላልፈው መልእክት የመክፈል አቅም ኖረህም አልኖረህ “ግዛ! ግዛ! ግዛ!” ብቻ የሚል ነው። ክሪስ ፋረል የተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዘ ኒው ፍሩጋሊቲ በተባለው መጽሐፋቸው “ትውልዱ ብዙ መበደር የሚያስከትለውን መዘዝ ከደረሰበት መከራ ተምሯል” በማለት ገልጸዋል።

ብዙ አገሮች በታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት በመመታታቸው የተነሳ ክፉኛ ተጎድተዋል። ሰንዴይ ታይምስ የተባለ በደቡብ አፍሪካ የሚታተም ጋዜጣ ባለፈው ዓመት ባወጣው እትሙ የፊት ገጽ ላይ “ኢኮኖሚው እያንሰራራ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም . . . ሸማቾች የዕለት ጉርስ ማግኘት ተስኗቸዋል” ብሏል። ጋዜጣው በመቀጠል እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “[በደቡብ አፍሪካ] 3 000 000 የሚያክሉ ሸማቾች ከሦስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ ወርኃዊ ወጪያቸውን ባለመክፈላቸው ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ እንዲሁም 250 000 የሚያክሉ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሥራ ተባርረዋል።”

የሥራ አጦች ብዛት በመጨመሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሥራ አጦች ቁጥር በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሆኗል። በዩናይትድ ስቴትስ እየታየ ነው ስለሚባለው የኢኮኖሚ ማንሰራራት በተመለከተ ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ “ከሰኔ 2009 ወዲህ የታየው የኢኮኖሚ ማንሰራራት ‘ታላቁ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ’ ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል” በፌዝ መልክ ተናግሯል። ጋዜጣው በመቀጠል “በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ሰዎች ዕዳቸውን መክፈል የሚጠበቅባቸው መሆኑ ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት ፍጆታ እንዳይጨምር ስለሚያደርግ እድገት እንደማይኖር ይሰማቸዋል” በማለት ዘግቧል።

ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት በአንተም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ከሆነ ዴቪድ በርት የተባሉት ደራሲ በመጣጥፋቸው ላይ እንዲህ በማለት በተናገሩት ሐሳብ ሳትስማማ አትቀርም፦ “በዓለም ላይ ስለተከሰተው የገንዘብ ቀውስ ብዙ ውይይት የሚደረግ ቢሆንም ችግሩን በተመለከተ የሚቀርብ የመፍትሔ ሐሳብ የለም።”

የሚቀጥሉት ርዕሶች ከዕዳ ነፃ ለመሆን እየታገሉ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ሲሆኑ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይዳስሳሉ፦ ቁጠባ ምን ጥቅም አለው? ዕዳ ካለብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ገንዘብህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለውስ እንዴት ነው?