በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ጥሩ መዝናኛ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

ጥሩ መዝናኛ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

ክርስቲያን ከሆንክ በመዝናኛ ረገድ መራጭ መሆንህ አይቀርም። የምታየውን፣ የምትሰማውን እንዲሁም የምታነበውን ነገር በተመለከተ በሌሎች ምርጫ አትመራም። ለምን? ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነትን፣ ዓመፅንና መናፍስታዊ ተግባርን ያበረታታል፤ ከእነዚህ ነገሮች ደግሞ መራቅ ይኖርብሃል። ይሁንና ጥሩ መዝናኛም አለ። እንዲህ ያለውን መዝናኛ እንዴት ማግኘት እንደምትችል እስቲ እንመልከት። *

ፊልም

የምትወደው ዓይነት ፊልም ላይ ✔ አድርግ።

  • አስቂኝ

  • ድራማ

  • በድርጊት የተሞላ (Action)

  • ሳይንሳዊ ልብ ወለድ

  • ሌላ

ይህን ታውቅ ነበር? አብዛኛውን ጊዜ በሕንድ በዓመት ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ፊልሞች የሚሠሩ ሲሆን ይህ ቁጥር በሌሎች አገሮች ከሚሠሩት ፊልሞች በብዙ መቶዎች ይበልጣል።

ልትርቀው የሚገባ ነገር፦ ብዙ ፊልሞች ሥነ ምግባራዊ ይዘታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል። አንዳንዶቹ የፆታ ብልግና እንዲሁም ዓመፅ ሲፈጽም በግልጽ የሚያሳዩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን የመሳሰሉትን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ” ይላል። (ቆላስይስ 3:8) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ከመናፍስታዊነት ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ተግባር ያወግዛል።​—ዘዳግም 18:10-13

መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? “ማስታወቂያውን ሳየው ጥሩ ካልመሰለኝ ፊልሙን አላየውም።”​—ጀሪን *

“አንድ ሰው በሥነ ምግባር ረገድ የእኔ ዓይነት አመለካከት እንዳለው እርግጠኛ እስካልሆንኩ ድረስ የሚሰጠኝን አስተያየት አልቀበልም።”​—ኬትለን

“ሲኒማ ገብቼ ፊልም እያየሁ ሳለ ይዘቱ ጥሩ እንዳልሆነ ከተሰማኝ ተነስቼ ወጣለሁ።”​—ማሪና

“ስለ አንድ ፊልም ይዘት ለማወቅ በእያንዳንዱ ፊልም ውስጥ የፆታ ድርጊቶች፣ ዓመፅ ወይም መጥፎ ንግግር መኖሩ አለመኖሩን የሚገልጹ የኢንተርኔት ድረ ገጾችን እመለከታለሁ።”​—ናታሻ

ጠቃሚ ምክር፦ መጥፎ ድርጊት ሲፈጸም እንደማያሳዩ የሚታሰቡ ፊልሞችን ምረጥ። ማሳሚ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት “ዘመን በማይሽራቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ የተመሠረቱ ጥንታዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞች በጣም ያስደስቱኛል” በማለት ተናግራለች።

ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦

‘የምመለከታቸው ፊልሞች አምላክ ስለ ፆታ፣ ስለ ዓመፅና ስለ መናፍስታዊ ሥራዎች የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም ቀላል እንዲሆንልኝ ያደርጋሉ ወይስ ያከብዱብኛል?’

መጽሐፍ

የምትወደው ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ሥራ ላይ ✔ አድርግ።

  • ልብ ወለድ

  • ኢልብ ወለድ

  • ሳይንሳዊ

  • ሌላ

ይህን ታውቅ ነበር? በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየሳምንቱ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ መጻሕፍት ይታተማሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናህን ችላ ብለህ በብዙኃኑ ዘንድ አድናቆት ያተረፈውን ነገር ብታይ፣ ብታነብ ወይም ብታዳምጥ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ምንም የሚያጣው ነገር የለም፤ እንዲያውም ትርፉን ያጋብሳል።

ልትርቀው የሚገባ ነገር፦ እንደ ፊልሞች ሁሉ ብዙ መጻሕፍትም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ መልእክት ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ መጻሕፍት ስለ ፆታ ብልግና በግልጽ የሚያወሱ ወይም መናፍስታዊ ጭብጥ ያላቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ” ይላል። (ኤፌሶን 5:3) በተጨማሪም መናፍስታዊ ድርጊቶች በይሖዋ ፊት “ክፉ” እንደሆኑ ይናገራል።​—2 ነገሥት 17:17

መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? “ጥሩ መጽሐፍ መግዛት ስፈልግ የጀርባ ሽፋኑን ከማንበብ በተጨማሪ መጽሐፉን ገለጥ ገለጥ እያደረግሁ እመለከተዋለሁ። ተገቢ ያልሆነ ነገር ካገኘሁበት አልገዛውም።”​—መሪ

“እያደግሁ ስሄድና ነገሮችን ራሴ አስቤ ማድረግ ስጀምር ሕሊናዬን የማዳመጥን አስፈላጊነት እየተገነዘብኩ መጣሁ። አንድ መጽሐፍ መጥፎ እንደሆነ ከተሰማኝ ማንበቤን አቆማለሁ። እንዲህ ያለውን መጽሐፍ ማንበብ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንደማይስማማ ተገንዝቤያለሁ።”​—ከሪን

ጠቃሚ ምክር፦ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አንብብ። “ከዘመናዊ ልብ ወለዶች ይልቅ ጊዜ የማያልፍባቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይበልጥ ይማርኩኛል” በማለት የ17 ዓመቷ ላራ ትናገራለች። “የቃላቱ አሰካክ፣ ገጸ ባሕርያቱ የተቀረጹበት መንገድ፣ የታሪኩ መዋቅርና ሁሉ ነገሩ ድንቅ ነው!”

ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦

‘የማነባቸው መጻሕፍት አምላክ በሚጠላው ምግባር እንድዝናና የሚያደርጉ ናቸው?’

ሙዚቃ

የምትወደው ዓይነት የሙዚቃ ስልት ላይ ✔ አድርግ።

  • ሮክ

  • የድሮ ዘፈኖች

  • ጃዝ

  • አር ኤንድ ቢ (R&B)

  • ሂፕ ሆፕ

  • የሃገረሰብ ሙዚቃ

  • ሬጌ

  • ሌላ

ይህን ታውቅ ነበር? አራት ዋና ዋና የሙዚቃ አሳታሚዎች በአንድ ዓመት ውስጥ በድምሩ 30,000 አልበሞችን ለሕዝብ ያቀርባሉ።

ልትርቀው የሚገባ ነገር፦ እንደ ፊልሞችና መጻሕፍት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያለው አብዛኛው ሙዚቃም በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ነው። ወራዳ የሆነ ግጥም ያላቸው ዘፈኖችና ልቅ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባቸው የሙዚቃ ክሊፖች የፆታ ስሜትህን መቆጣጠር ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብህ ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) “በዛሬው ጊዜ ያለው አብዛኛው ሙዚቃ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር የሚጋጭ ድርጊትን የሚያበረታታ ነው” በማለት የ21 ዓመቷ ሊ ተናግራለች። አክላም “የሙዚቃው ምት ሰዎች እንዲደንሱ ያነሳሳል” ካለች በኋላ ዳንሱ ግን የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ እንደሆነ ገልጻለች።

መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? “‘በዕድሜ የሚበልጡኝ ክርስቲያኖች የማዳምጣቸውን ሙዚቃዎች ቢያዩአቸው ያሳፍረኛል?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። እንዲህ ማድረጌ ምን ዓይነት ሙዚቃ መምረጥ እንዳለብኝ ለማወቅ ይረዳኛል።”​—ሊአን

ጠቃሚ ምክር፦ የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶችን ለማዳመጥ ሞክር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ሮቤርቶ “አባቴ ክላሲካል ሙዚቃ [የቀድሞ ዘመን ሙዚቃዎች] ስለሚወድ ከልጅነቴ ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ሙዚቃ በብዛት እሰማ ነበር” በማለት ተናግሯል። “ስለ ክላሲካል ሙዚቃ ማወቄና ፒያኖ መማሬ የእውቀት አድማሴን አስፍቶታል።”

ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦

‘የማዳምጠው ሙዚቃ የፆታ ፍላጎቴን መቆጣጠር ቀላል እንዲሆንልኝ ያደርጋል ወይስ ያከብድብኛል?’

ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት፦

በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተሰኘውን መጽሐፍ ምዕራፍ 31 እና 32 ተመልከት።

 

^ አን.3 ንቁ! መጽሔት የትኛውንም ፊልም፣ መጽሐፍ ወይም ዘፈን ለይቶ በመጥቀስ አይደግፍም አሊያም አያወግዝም። የዚህ ርዕስ ዓላማ አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማስተዋል የሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና እንድታዳብርና በሕሊናህ እንድትመራ መርዳት ነው።​—መዝሙር 119:104፤ ሮም 12:9

^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።