በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስ ያለባቸውን ሰዎች መርዳት
በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስ ያለባቸውን ሰዎች መርዳት
“ብዙውን ጊዜ ልቤ በኃይል ይመታል፣ ላብ ያጠምቀኛል እንዲሁም ትንፋሽ ያጥረኛል። በፍርሃትና በስጋት ስሜት እዋጣለሁ፤ አእምሮዬም ይረበሻል።”—ኤዛቤላ፣ በ40ዎቹ ዕድሜ የምትገኝና ከመጠን ባለፈ የፍርሃት ስሜት * የምትሠቃይ
ጭንቀት “የፍርሃት ወይም የስጋት ስሜት” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ለምሳሌ ኃይለኛ ውሻ ሲመጣብህ ፍርሃት ተሰምቶህ ያውቃል? ውሻው ትቶህ ቢሄድስ? ፍርሃቱና ስጋቱ እንደሚለቅህ ግልጽ ነው። ይሁንና ጭንቀት የጤና እክል የሚሆነው መቼ ነው?
አንድ ሰው እንዲፈራ ያደረገው ነገር ከተወገደም በኋላ ስጋት የሚሰማውና በጣም የሚረበሽ ከሆነ ግለሰቡ በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስ (አንግዛይቲ ዲስኦርደር) አለበት ማለት ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤንነት ተቋም እንደሚገልጸው ከሆነ “በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ . . . ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ 40 ሚሊዮን አሜሪካውያን በጭንቀት ምክንያት በሚመጣ የስሜት ቀውስ ይታወካሉ።” በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችውን ኤዛቤላን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሷን የሚያጋጥማት ዓይነት ፋታ የማይሰጥ የጭንቀት ስሜት ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
ይህ ችግር በግለሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቡ አባላት ላይም ጫና ሊያሳድር ይችላል። ይሁንና እንዲህ ያሉት ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት አይደለም። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤንነት ተቋም ያሳተመው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስን ለመቋቋም የሚረዱ ውጤታማ የሆኑ ሕክምናዎች አሉ፤ ሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲህ ዓይነት ችግር ያላቸው ሰዎች በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑና እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት እንዲመሩ የሚያግዟቸውን አዳዲስ ሕክምናዎች እያስገኙ ነው።”
የቤተሰብ አባላትና ጓደኞችም እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን ሰዎች መርዳት ይችላሉ። እንዴት?
እርዳታ መስጠት የሚቻልበት መንገድ
ደግፏቸው፦ ያለ ምክንያት ከልክ በላይ የመጨነቅ ችግር ያለባትና ከአሰቃቂ ገጠመኝ በኋላ በሚከሰት ጭንቀት የምትሠቃየው ሞኒካ “አብዛኞቹ ሰዎች ያሉብኝን ስሜታዊ ችግሮች መረዳት አዳጋች ይሆንባቸዋል” በማለት የሚያጋጥማትን አስቸጋሪ ሁኔታ ገልጻለች።
በዚህም የተነሳ በጭንቀት ምክንያት በሚመጣ የስሜት ቀውስ የሚሠቃዩ ሰዎች፣ ሌሎች በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዷቸው ስለሚሰጉ ችግራቸውን ለመደበቅ ይሞክራሉ። ይህ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው በማድረግ ችግሩን ያባብሰዋል። ስለዚህ ከቤተሰባቸው አባላትና ከጓደኞቻቸው ድጋፍ ማግኘታቸው በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
ስለ ችግሩ ያላችሁን ግንዛቤ አሳድጉ፦ በተለይ ከላይ የተገለጸው ዓይነት የስሜት ቀውስ ያለባቸውን ሰዎች የሚቀርቧቸው ግለሰቦች ስለ ጉዳዩ ግንዛቤያቸውን ማስፋታቸው ተገቢ ነው። ይህም የቤተሰባቸውን አባላትና የቅርብ ጓደኞቻቸውን ይጨምራል።
እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁን ቀጥሉ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ጳውሎስ የተባለ ሚስዮናዊ በግሪክ በምትገኘው በተሰሎንቄ የነበሩ ወዳጆቹን “እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁንና እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:11) ይህንን ማድረግ የምንችለው በምንናገራቸው ቃላት ብቻ ሳይሆን በድምፃችን ቃናም ጭምር ነው። ለወዳጆቻችን በጥልቅ እንደምናስብ ማሳየት የሚያስፈልገን ሲሆን ስሜት የሚጎዳና ጥፋተኛ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ አስተያየት ከመሰንዘር መቆጠብ ያስፈልገናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን ኢዮብን ለማጽናናት የመጡትን ሦስት ወዳጆቹን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ታሪኩ እንደሚገልጸው እነዚህ ወዳጅ ተብዬዎች፣ ኢዮብ በድብቅ የሠራቸውን ኃጢአቶች እንደሸፋፈነና የደረሰበት መከራ መንስኤም ይኸው እንደሆነ በመናገር በስህተት ወነጀሉት።
ስለዚህ እናንተም የግለሰቡን ስሜት ለመረዳት ሞክሩ። ሲናገር በጥሞና አዳምጡት። ራሳችሁን በግለሰቡ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክሩ። የሚናገረውን ነገር ሳይጨርስ ቸኩላችሁ ያልሆነ መደምደሚያ ላይ ከመድረስ ተቆጠቡ። የኢዮብ ወዳጅ ነን ብለው የመጡት ሰዎች እንዲህ በማድረጋቸው ኢዮብ “የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ” ብሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች ኢዮብን ከማጽናናት ይልቅ ይባስ መጥፎ ስሜት እንዲሰማው አድርገውታል!—ኢዮብ 16:2
እንግዲያው እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በጥሞና ማዳመጥ እንዳለባችሁ አትዘንጉ። የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ዕድል ስጧቸው። ይህም ስሜታቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችላችኋል። ደግሞም እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም አስቡ! በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስ ያለባቸውን ሰዎች፣ ትርጉም ያለውና የሚያረካ ሕይወት እንዲመሩ ልትረዷቸው ትችሉ ይሆናል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በጭንቀት ምክንያት የሚመጡ የጤና እክሎች
በጭንቀት ምክንያት የሚመጡ የስሜት ቀውስ ዓይነቶችን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ በተለይም ይህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች የቤተሰባችን አባላት ወይም የቅርብ ወዳጆቻችን ከሆኑ በቂ ግንዛቤ ማግኘታችን ጠቃሚ ነው። ከእነዚህ የጤና እክሎች መካከል አምስቱ ከዚህ በታች ቀርበዋል።
ከመጠን ያለፈ የፍርሃት ስሜት (ፓኒክ ዲስኦርደር)፦ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችውን የኢዛቤላን ሁኔታ እንመልከት። ኢዛቤላን የሚረብሻት በጭንቀት ምክንያት የሚያጋጥማት የስሜት ቀውስ ብቻ አይደለም። “በተረጋጋሁበት ሰዓት እንኳ ‘ጭንቀቱ እንደገና ይነሳብኝ ይሆን?’ የሚለው ስጋት በጣም ይረብሸኛል” በማለት ትናገራለች። በዚህም የተነሳ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ከዚህ በፊት የስሜት ቀውስ ያጋጠማቸው ቦታ ዳግመኛ ድርሽ አለማለትን ይመርጣሉ። አንዳንዶቹ የትም መሄድ ስለሚፈሩ ከቤታቸው አይወጡም፤ ከወጡ ደግሞ የሚፈሩት ሁኔታ ወዳለበት ቦታ የሚሄዱት ከሚተማመኑበት ሰው ጋር ብቻ ነው። ኢዛቤላ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ብቻዬን መሆኔ በራሱ እንኳ የስሜት ቀውስ ሊፈጥርብኝ ይችላል። ከእናቴ ጋር ስሆን እረጋጋለሁ፤ እሷ አጠገቤ ከሌለች ግን በጣም እረበሻለሁ።”
ጭንቀትን ለመቀነስ ሲሉ አንድን ነገር ደጋግሞ የማድረግ አባዜ (ኦብሰሲቭ ኮምፐሊስቭ ዲስኦርደር)፦ ቆሻሻ ወይም ጀርሞች የሚያስከትሉት ጉዳት ከልክ በላይ የሚያስጨንቀው ሰው አሁንም አሁንም እጁን እንዲታጠብ የሚያስገድደው ኃይለኛ ስሜት አለው። ሬናን እንዲህ ያለውን ስሜት በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ቀደም ሲል የሠራኋቸውን ስህተቶች እየመላለስኩ ስለማውጠነጥናቸውና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ስለምሞክር አእምሮዬ ሁልጊዜ እንደተበጠበጠ ነው።” እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት ሰው የቀድሞ ስህተቶቹን ነጋ ጠባ ለሌሎች እንዲናዘዝ የሚገፋፋ አባዜ ይኖረዋል። ሬናን ዘወትር ማበረታቻ ያስፈልገዋል። መድኃኒት መውሰዱም ችግሩን ለመቋቋም ረድቶታል። *
ከአሰቃቂ ገጠመኝ በኋላ የሚከሰት ጭንቀት (ፖስት ትራውማቲክ ስትረስ ዲስኦርደር)፦ ይህ አገላለጽ፣ ሰዎች አካላዊ ጉዳት የሚያደርስ በጣም አሰቃቂ ሁኔታ ስላጋጠማቸው፣ ስለተመለከቱ አሊያም እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስላለፉ የሚፈጠሩባቸውን የተለያዩ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ያመለክታል። እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ሊደነብሩ፣ ሊነጫነጩ፣ ስሜታቸው ሊደነዝዝ፣ ይወዷቸው በነበሩ ነገሮች ላይደሰቱ እንዲሁም ለሌሎች፣ በተለይም በጣም ይቀርቧቸው ለነበሩት ሰዎች ፍቅር ለማሳየት ሊቸገሩ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ቁጡዎች አልፎ ተርፎም ጠበኞች ይሆናሉ፤ እንዲሁም የደረሰባቸውን አሰቃቂ ገጠመኝ ከሚያስታውሷቸው ሁኔታዎች መራቅን ይመርጣሉ።
ሰዎችንና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ያለ ምክንያት መፍራት (ሶሻል ፎብያ)፦ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር የሚያገናኟቸውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ሲያከናውኑ ሰዎች ምን ይሉኛል የሚለው ስሜት ከልክ በላይ ያስጨንቃቸዋል። አንዳንዶቹ፣ ሰዎች ሁልጊዜ እንደሚከታተሏቸውና እንደሚታዘቧቸው በማሰብ በስጋት ይዋጣሉ። በአንድ ዝግጅት ላይ ከመገኘታቸው በፊት ለቀናት ወይም ለሳምንታት ሲጨነቁ ሊሰነብቱ ይችላሉ። የሚሰማቸው ፍርሃት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሥራቸውን፣ ትምህርታቸውን ወይም ሌሎች የተለመዱ እንቅስቃሴዎቻቸውን ሊያስተጓጉልባቸው ይችላል፤ እንዲሁም ጓደኛ ማፍራትና በጓደኝነት መቀጠል አዳጋች ይሆንባቸዋል።
ያለ ምክንያት ከልክ በላይ መጨነቅ (ጄኔራላይዝድ አንግዛይቲ ዲስኦርደር)፦ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሞኒካ የዚህ ዓይነት ችግር አለባት። ያለ ምንም ምክንያት ወይም በጥቃቅን ነገሮች እንኳ ቀኑን ሙሉ ‘ከልክ በላይ ስትጨነቅ’ ትውላለች። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች መጥፎ ነገር ቢደርስስ ብለው ይሰጋሉ፤ እንዲሁም ስለ ጤንነታቸው፣ ስለ ገንዘብ፣ ስለ ቤተሰብ ችግሮች ወይም በሥራ ቦታ ስለሚያጋጥማቸው ችግር ከልክ በላይ ይጨነቃሉ። ‘ቀኑ እንዴት ያልፍ ይሆን?’ የሚለው ሐሳብ ብቻ እንኳ ጭንቀት ውስጥ ሊከታቸው ይችላል። *
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 በገጽ 27 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
^ አን.19 ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።
^ አን.22 ከላይ ያለው ሐሳብ የተመሠረተው በዩናይትድ ስቴትስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ክፍል ሥር ያለው ብሔራዊ የአእምሮ ጤንነት ተቋም ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁን . . . ቀጥሉ”