በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታይታኒክ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነች መርከብ”

ታይታኒክ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነች መርከብ”

ታይታኒክ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነች መርከብ”

ሚያዝያ 10 ቀን 1912፦ ታይታኒክ ከሳውዝሃምፕተን፣ እንግሊዝ በመነሳት ወደ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አቀናች።

ሚያዝያ 11፦ ታይታኒክ ከሼርቡርግ፣ ፈረንሳይና ከኩዊንስታውን (አሁን ኮቭ ይባላል)፣ አየርላንድ ተጨማሪ መንገደኞች ካሳፈረች በኋላ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ጉዞዋን ተያያዘችው።

ሚያዝያ 14፦ ከምሽቱ 5:40 አካባቢ ታይታኒክ ከበረዶ ዐለት ጋር ተላተመች።

ሚያዝያ 15፦ ከሌሊቱ 8:20 ላይ ታይታኒክ የሰመጠች ሲሆን ከተሳፋሪዎቹ መካከል 1,500 የሚያህሉ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ።

ታይታኒክ ምን ዓይነት መርከብ ነበረች? እንድትሰምጥ ያደረጋት ምንድን ነው? በሰሜን አየርላንድ ባለው በቤልፋስት አቅራቢያ የሚገኘውን የአልስተር የባሕልና የትራንስፖርት ቤተ መዘክር በመጎብኘት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይቻላል።

ታይታኒክ​ልዩ የሚያደርጋት ምንድን ነው?

የባሕልና የትራንስፖርት ቤተ መዘክሩ የቀድሞ ኃላፊ የነበሩት ማይክል መኮን እንደገለጹት ታይታኒክ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነች መርከብ” ነች። ይሁን እንጂ ታይታኒክ ተመሳሳይ የሌላት መርከብ አልነበረችም። ታይታኒክ በቤልፋስት በሚገኘው የሃርላንድና የዎልፍ መርከብ ማምረቻ ከተሠሩት ሦስት ትላልቅ መርከቦች ሁለተኛዋ ነበረች። * ታይታኒክ 269 ሜትር ርዝመትና 28 ሜትር ስፋት ስለነበራት በዘመኑ ከነበሩት ግዙፍ መርከቦች አንዷ ናት።

የእነዚህ ግዙፍ መርከቦች ባለንብረት፣ ኋይት ስታር የተባለ የመርከብ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም እጅግ አትራፊ በነበረው የሰሜን አትላንቲክ የጉዞ መስመር ላይ የበላይነት ማግኘት ነበር። ኋይት ስታር፣ ተፎካካሪው የነበረውን ኩናርድ የተባለ የመርከብ ድርጅት በፍጥነት ረገድ መወዳደር አልቻለም። በመሆኑም ኋይት ስታር፣ ታዋቂና ባለጠጋ የሆኑ ተሳፋሪዎችን ለመሳብ ሲል ግዙፍ በሆኑና ምቾት ባላቸው መርከቦች ግንባታ ላይ ትኩረት አደረገ።

ይሁን እንጂ ታይታኒክ ግዙፍ መሆኗ ሌላም ጥቅም ነበረው። የሰሜን አየርላንድ ብሔራዊ ቤተ መዘክሮች ኃላፊ የሆኑት ዊልያም ብሌር “ከ1900 እስከ 1914 ባሉት ዓመታት በየዓመቱ 900,000 የሚያህሉ ሰዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይፈልሱ ነበር” ብለዋል። አትላንቲክን የሚያቋርጡ የመርከብ ድርጅቶች፣ እነዚህን ሰዎች ከአውሮፓ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማጓጓዝ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ነበር፤ ታይታኒክም ለዚህ ዓላማ እንድታገለግል ታስቦ ነበር።

አሳዛኙ አደጋ

የታይታኒክ ካፒቴን የነበሩት ኤድዋርድ ጆን ስሚዝ፣ በሰሜናዊው አትላንቲክ በረዶ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ አሳምረው ያውቁ ነበር። እኚህ ካፒቴን በኦሎምፒክ መርከብ በዚህ መስመር ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል። ሌሎች መርከቦችም በዚህ መስመር የበረዶ ዐለቶች እንዳሉ የሚገልጹ ማስጠንቀቂያዎች አስተላልፈው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ችላ ተብለዋል፤ አሊያም ደግሞ መልእክቱ ለካፒቴኑ አልደረሰ ይሆናል።

ታይታኒክ በጉዞ ላይ እያለች ከፊት ለፊት የበረዶ ዐለት እንዳለ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በድንገት ከማማው ተሰማ፤ ይሁንና ይህ የዘገየ ማስጠንቀቂያ ነበር! ተረኛ የነበረው መኮንን መርከቧን ፊት ለፊት ከመላተም ሊያድናት ቢችልም በጎን በኩል ከበረዶው ዐለት ጋር መጋጨቷ አልቀረም። በዚህ ምክንያት በመርከቧ አካል ላይ ጉዳት በመድረሱ ውኃው ከፊት ወዳሉት የመርከቢቱ ክፍሎች ገባ። ካፒቴን ስሚዝ መርከባቸው ከመስጠም እንደማትተርፍ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። የድረሱልን መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የሕይወት አድን ጀልባዎች እንዲዘጋጁ አዘዙ።

ታይታኒክ 16 የሕይወት አድን ጀልባዎችና ሌሎች አራት በአየር የሚሞሉ ጀልባዎች ነበሯት። እነዚህ ጀልባዎች 1,170 ያህል ሰዎችን የመያዝ አቅም አላቸው። መርከቧ ላይ የነበሩት ተሳፋሪዎችና ሠራተኞች ግን 2,200 ነበሩ! ይባስ ብሎ ደግሞ ብዙዎቹ ጀልባዎች በደንብ ሳይሞሉ መሄድ ጀመሩ። በተጨማሪም በአብዛኞቹ ጀልባዎች ላይ የነበሩት ሰዎች ወደ ባሕሩ ዘለው የገቡ ሰዎችን ፈልገው ለማዳን ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም። በመሆኑም የተረፉት 705 ሰዎች ብቻ ናቸው!

ከአደጋው በኋላ

ታይታኒክ አደጋ ከደረሰባት በኋላ የባሕር ጉዞ ባለሥልጣናት የመርከብ ተጓዦችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ ደንቦችን አውጥተዋል። ከእነዚህ ደንቦች አንዱ በባሕር ላይ በሚደረጉ ጉዞዎች በሙሉ ለሁሉም ተሳፋሪዎች የሚበቃ ሕይወት አድን ጀልባ እንዲኖር ያስገድዳል።

ለበርካታ ዓመታት ሰዎች፣ ታይታኒክ በፍጥነት የሰመጠችው ከበረዶው ዐለት ጋር ስትጋጭ በሰፊው ስለተሸነቆረች እንደሆነ ያምኑ ነበር። በ1985 ታይታኒክ በውቅያኖሱ ወለል ላይ ከተገኘች በኋላ ግን መርማሪዎች ከዚህ የተለየ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፤ የውኃው ቅዝቃዜ የመርከቧን ብረቶች ስለጎዳቸው መሰባበርና መሰነጣጠቅ ጀምረው ነበር። መርከቧ ከበረዶው ዐለት ጋር ከተጋጨች ሦስት ሰዓት እንኳ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለት ተከፈለችና ሰመጠች፤ ይህ አደጋ በባሕር ጉዞ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ ከሚባሉት አንዱ ነው። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ከታይታኒክ በፊት ኦሎምፒክ የተሰኘች መርከብ የተሠራች ሲሆን ከታይታኒክ በኋላ ደግሞ ብሪታኒክ የተባለች መርከብ ተሠርታለች።

^ አን.17 በታይታኒክ ላይ ከደረሰው አደጋ የተረፈ ሰው የተናገረውን ታሪክ በጥቅምት 22, 1981 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-8 ላይ ማግኘት ይቻላል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሳውዝሃምፕተን

ሼርቡርግ

ኩዊንስታውን (ኮቭ)

ታይታኒክ የተጋጨችበት ቦታ

ኒው ዮርክ

አትላንቲክ ውቅያኖስ

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ታይታኒክ” በግንባታ ላይ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የታይታኒክ” አክናፊዎች

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሠራተኞች ቤልፋስት፣ አየርላንድ ከሚገኘው የሃርላንድና የዎልፍ መርከብ ማምረቻ ሲወጡ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የታይታኒክ” ካፒቴን ኤድዋርድ ጆን ስሚዝ (በቀኝ በኩል) እና የመርከቧ ተቆጣጣሪ የሆኑት ኸርበርት ማክኤልሮይ

[የሥዕል ምንጭ]

© Courtesy CSU Archive/age fotostock

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pages 12 and 13: Leaving Southampton, under construction, and shipyard: © National Museums Northern Ireland; propellers: © The Bridgeman Art Library

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

© SZ Photo/Knorr & Hirth/Bridgeman Art Library