ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
“ኮምፒውተሮች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት፣ አዳዲስ ዝርያዎችን ለመመዝገብ ሁሉንም መዛግብት ማገላበጥ [ለሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች] የማይታሰብ ነገር ነበር፤ በመሆኑም ብዙ ተደጋጋሚ ስሞች ነበሩ።” ከተመዘገቡት አንድ ሚሊዮን የሚያህሉ ስሞች መካከል ቢያንስ 477,601 የሚያህሉት ተመሳሳይ መሆናቸው በአሁኑ ጊዜ ተደርሶበታል።—ሳይንስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“ከቻይና ሕዝብ መካከል ደስተኛ እንደሆኑ የሚሰማቸው 6 በመቶ የሚያህሉት ብቻ” እንደሆኑ አንድ ጥናት ያሳያል። በጥናቱ ከተካፈሉት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት “ሀብት” ማግኘት “ለደስታ ወሳኝ ነገር” እንደሆነ ይሰማቸዋል።—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና
“በሩሲያ ከወንጀል ጋር በተያያዙ አኃዛዊ መረጃዎች ላይ የተደረገ ምርመራ በመላው አገሪቱ የወጣው አኃዛዊ መረጃ ‘የተጭበረበረ’ እንደሆነ ያሳያል።” መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅቶች “ከወንጀል ጋር በተያያዘ እውነታውን ለመሸፋፈን” በመሞከራቸውና ለበርካታ ወንጀል ነክ ጉዳዮች እልባት እንደሰጡ የሚገልጹ የተጋነኑ አኃዛዊ መረጃዎችን በማቅረባቸው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።—ሪያ ኖቮስቲ፣ ሩሲያ
“በጀርመን ዋና ከተማ [በበርሊን] ከሚኖሩ ሦስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንዱ፣ ለትምህርት የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ሲል በዝሙት አዳሪነት ለመሠማራት [የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ ዳንስ መደነስንም ይጨምራል] ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።”—ሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ጀርመን
ቄንጠኞቹ ወላዶች
የመገናኛ ብዙኃን እናቶች ልጅ መውለዳቸውን በሚያሳውቁበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት እናቶች መውለዳቸውን ለማሳወቅ ቴሌግራም ይልኩ እንደነበረ ሁሉ “የዛሬዎቹ እናቶች ደግሞ የምሥራቹን የሚያበስሩት በኢንተርኔት ነው” በማለት ኤቢሲ የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ እናቶች እንደወለዱ ከልጃቸው ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ የኢንተርኔት ድረ ገጽ ላይ ያስቀምጣሉ። በመሆኑም የመልካቸው ነገር የሚያሳስባቸው የዘመኑ እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ወደ ውበት ሳሎን በመሄድ ፊታቸውን፣ እጃቸውን እንዲሁም እግራቸውን ለማስዋብ ጥረት ያደርጋሉ። ዘገባው በመቀጠል “እንዲያውም አንዳንዶች ሆስፒታል ድረስ አብሯቸው የሚሄድ ፀጉር ሠሪ ይቀጥራሉ” ይላል። ለምን? እንዲህ የሚያደርጉት አምረውና ተዉበው ለመውለድ ስለሚፈልጉ እንደሆነ በቦስተን ቤተ እስራኤል የእርግዝናና የወሊድ የጤና ማዕከል ተቆጣጣሪ የሆኑት ዶክተር ቶኒ ጎለን ይናገራሉ።
ተንቀሳቀስ፣ ጤናማ ትሆናለህ
በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት አሊያም ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ለረጅም ሰዓታት መቀመጥ ለከባድ በሽታ እንደሚያጋልጥ ተመራማሪዎች ገልጸዋል። “ስትቀመጡ፣ ጡንቻዎች ከደም ውስጥ ቅባትን እንዲያወጡና እንዲያቃጥሉ የሚያደርገው ኤንዛይም መጠን በእጅጉ ይቀንሳል” በማለት ቫንኩቨር ሳን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ጋዜጣው አክሎም ጤናማ ለመሆን “ልባችን በኃይል እንዲመታ የሚያደርግና ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ እንቅስቃሴ በቂ አይደለም” ብሏል። ሰውነታችን ጤናማ ሆኖ እንዲሠራ “አዘውትረን፣ ቀለል ያለ ወይም መካከለኛ መጠን ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልገናል።”