አራት እግር ያለው ገንዘብ
አራት እግር ያለው ገንዘብ
“በእኛ አካባቢ አሳማ እንደ ትልቅ ሀብት ስለሚቆጠር አንድ አሳማ ማሳደግ እንኳ ትልቅ ኃላፊነት ያስከትላል።” ይህን የተናገረችው በፓፑዋ ኒው ጊኒ ደጋማ አካባቢ የምትኖረው የ17 ዓመቷ ኤንመሪ ካኒ ናት። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ አንዲት የዓሳማ ግልገል እንዳሳድግ ሲጠይቀኝ በጣም ደስ ቢለኝም ኃላፊነቱ አስጨንቆኝ ነበር። ግልገሏ በጣም ትንሽ ስለነበረች የምትሞትብኝ መስሎኝ ነበር።”
ታዲያ ኤንመሪ ግልገሏን ለመንከባከብ ምን አደረገች? በፓፑዋ ኒው ጊኒ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች፣ አሳማዎች የገንዘብ ያህል በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? ኤንመሪ ከንቁ! መጽሔት ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እነሆ!
እስቲ ስለምትኖሪበት አካባቢ ትንሽ ግለጪልን።
የምኖረው ከወላጆቼ ጋር ሲሆን ሁለት ታናናሽ ወንድሞችና ሁለት ታናናሽ እህቶች አሉኝ። የሳር ክዳን ያላት ትንሿ ጎጆ ቤታችን የምትገኘው በምዕራባዊው ተራራማ አካባቢ ርቆ በሚገኝ መንደር ውስጥ ነው። በመንደራችን ውስጥ 50 የሚያህሉ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን ሁሉም ዘመዶቻችን ናቸው። ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነውን ኮረብታማ አካባቢ እያቆራረጠ የሚወርድ አንድ ትንሽ ወንዝ በቤታችን አጠገብ ይገኛል።
አብዛኞቹ የመንደራችን ነዋሪዎች የሚተዳደሩት በግብርና ነው። የእኛም ቤተሰብ ስኳር ድንች፣ ዱባ፣ ኪያር፣ ቡናና
ሌሎች ሰብሎች የሚያመርትበት እርሻ አለው። አትክልት መትከልና የጉልበት ሥራ መሥራት እወዳለሁ። ከዚህም ሌላ ቤት እንደ ማጽዳት፣ ልብስ እንደ ማጠብ ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እሠራለሁ፤ የቤተሰባችንን አሳማ መንከባከብም ሌላው ሥራዬ ነው።አሳማሽን የምትንከባከቢው እንዴት ነው?
አባዬ ከአንድ ዓመት በፊት አሳማችንን ሲገዛት በጣም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ በእቅፌ ልይዛት እችል ነበር። አሳማዬን የተፈጨ ዓሣን ከላመ ስኳር ድንች፣ ከውኃ፣ ከጨውና ከሸንኮራ ጭማቂ ጋር በመደባለቅ በየቀኑ እመግባታለሁ። ማታ ላይ አየሩ ስለሚቀዘቅዝ ቤታችን ውስጥ ካለው ምድጃ በላይ ጣሪያው ላይ በተንጠለጠለ የሩዝ ከረጢት ውስጥ ታድራለች። እኔም እዚያው አካባቢ ወለሉ ላይ እተኛለሁ። በዚህ መንገድ አሳማዋ ከቁሩ ማምለጥ ብቻ ሳይሆን በጥሩ ሁኔታ ማደግ ችላለች።
ለአሳማችን የተለየ ስም አላወጣሁላትም። የምጠራት “አሳማ” እያልኩ ስለነበር “አሳማ” ስሟ ሆኖ ቀረ። አሳማዋን የምንከባከባት ልክ እንደ ልጄ አድርጌ ነው። አበላታለሁ፤ አጥባታለሁ፤ እንዲሁም ለበርካታ ሰዓታት አጫውታታለሁ። አሳማዋ ለእኔ የተለየ ፍቅር ስላላት በምሄድበት ሁሉ ትከተለኛለች።
አሳማዋ አደግ ስትል ዛሬም ድረስ የምታደርገው አንድ ልማድ አስተማርኳት። በገመድ አስሬ እየመራሁ ከቤታችን 15 ደቂቃ ያህል ወደሚያስኬደው የአትክልት እርሻችን እወስዳታለሁ። እዚያ ስደርስ ገመዱን አንድ ዛፍ ላይ ካሰርኩ በኋላ አሳማዋ ቀኑን ሙሉ እርሻውን ስትቆፍር ትውላለች። አንገቷ ጠንካራ በመሆኑ በአፍንጫዋ ተጠቅማ በቀላሉ መሬቱን እየቆፈረች ሥራሥርና ትላትል ትለቃቅማለች፤ ይህ ደግሞ አፈሩ እንዲለሰልስና ለምነቱ እንዲጨምር ያደርጋል። አመሻሹ ላይ ወደ ቤት እመልሳታለሁ፤ ከዚያም ጥሬና
የበሰለ ስኳር ድንች ካበላኋት በኋላ ጉረኖዋ ውስጥ አሳድራታለሁ።በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች ለአሳማዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው?
በእኛ አካባቢ እንዲህ የሚል አባባል አለ፦ ገንዘብ ማለት አሳማ ነው፤ አሳማ ማለት ገንዘብ ነው። መደበኛ ገንዘብ ወደዚህ አካባቢ ከመምጣቱ ከብዙ ዓመት በፊት ሰዎች የሚገበያዩት በአሳማዎች ነበር፤ ይህ ልማድ ዛሬም ቀጥሏል። ለምሳሌ፣ አንድ የመኪና ሻጭ ኩባንያ አዲስ መኪና ለገዛ ሁሉ አንድ አሳማ ይሰጥ የነበረበት ጊዜ ነበር። የጎሳ ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ እርቅ የሚያወርዱት ገንዘብ ወይም አሳማ በመስጠት ነው። እንዲሁም ብዙ ሙሽሮች፣ ለሙሽሪት ቤተሰቦች ወይም የቅርብ ዘመዶች ጥሎሽ አድርገው ከሚሰጧቸው ነገሮች መካከል አሳማ ይገኝበታል።
አሳማ መብላት የቤተሰቡን የገንዘብ ምንጭ እንደ መብላት የሚቆጠር ይመስላል!
ልክ ነው! አሳማዎች እንደ ውድ ነገር ተደርገው ስለሚታዩ በአብዛኛው የአሳማ ሥጋ የምንበላው ለየት ባሉ ወቅቶች ማለትም በቀብር ሥነ ሥርዓትና ትልቅ ቦታ በሚሰጣቸው ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ነው። ያም ሆኖ አንዳንድ ጎሳዎች ሀብታቸውን ለማሳየት ወይም ቀደም ሲል የተደረገላቸውን ውለታ ለመክፈል ሲሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሳማዎችን በማረድ ትልቅ ድግስ ያዘጋጃሉ።
ታዲያ አሳማዎቹን ምን ታደርጓቸዋላችሁ?
“አሳማዎች” ማለትህ ትክክል ነው። ምክንያቱም አሳማዬ ብዙ ግልገሎችን ወልዳልናለች። በቅርቡ ከግልገሎቹ አንዷን በ100 ኪና (700 የኢትዮጵያ ብር ገደማ ይሆናል) ሸጥናት። ገንዘቡን በአውቶቡስ ተሳፍረን የይሖዋ ምሥክሮች በአቅራቢያችን በሚገኘው ባንዝ በተባለ ከተማ ወደሚያደርጉት ዓመታዊ የአውራጃ ስብሰባ ለመሄድ ተጠቀምንበት። ወደፊት አባዬ ሌላ ግልገል ሸጦ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን መግዛቱ አይቀርም።
ብዙ ገንዘብ እንድታገኙ ለምን ተጨማሪ አሳማዎችን አታሳድጉም?
ዓላማችን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘት እንጂ ሀብታም መሆን አይደለም። ቤተሰባችን ትኩረት ያደረገው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ነው። ይህም አምላካችንን ይሖዋን ማገልገልን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ በሚቻለን ሁሉ ሰዎችን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ መርዳትንና በቤተሰብ ሆነን አንዳንድ ነገሮችን ማከናወንን ያካትታል። አኗኗራችን ቀላል ቢሆንም እርስ በርሳችን የምንቀራረብ ደስተኛ ቤተሰብ ነን።
በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ አትክልቶችን በመትከልና አሳማ በማርባት ወጪዎቼን ለመሸፈን ጥረት ባደርግም ዋነኛ ሥራዬ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሰዎች በማካፈል ወንጌላዊ ሆኖ ማገልገል ነው። በሳምንቱ ውስጥ ያሉትን በርካታ ቀናት የማሳልፈው ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠውን ይህን ሥራ በማከናወን ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) አንድ ቀን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በሚተረጎሙበት ፖርት ሞርዝቢ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ገብቼ እንደምሠራ ተስፋ አደርጋለሁ። እዚህ ግብ ላይ መድረስ ባልችልም እንኳ ይሖዋን ማገልገልና መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም ከምንም ነገር በላይ ደስታ እንደሚያስገኙ አውቃለሁ። አራት እግር ባለው ገንዘብ ተጠቅሜ ወጪዎቼን መሸፈን በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተጨማሪ መረጃ
● በኒው ጊኒ ደሴት በትንሹ ሁለት ሚሊዮን አሳማዎች ይኖራሉ፤ በሌላ አባባል አንድ አሳማ ለሦስት ነዋሪዎች ይደርሳል ማለት ነው።
● በገጠር አካባቢ ካሉት ነዋሪዎች ከግማሽ የሚበልጡት አሳማ አላቸው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኢንዶኔዥያ
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
አውስትራሊያ
ኢንዶኔዥያ
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
ፖርት ሞርዝቢ
ምዕራባዊው ተራራማ አካባቢ
አውስትራሊያ
[በገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ እርሻ ቦታ ስንጓዝ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሳማዋን ማጠብ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሳማዋን ማጫወት