ለልጆቻችሁ ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦችን አስተምሩ
“ቀደም ሲል የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የምከተል ሰው ስላልነበርኩ ልጆቼን ማሠልጠን ከባድ ሆኖብኝ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን እርዳታ ስላገኘሁ ይህን ማድረግ ይበልጥ ቀላል ሆኖልኛል።”—ኢሊዛቤት፣ ደቡብ አፍሪካ
ተፈታታኝ ሁኔታ፦
ልጆች በትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸው የእኩዮች ተጽዕኖ እንዲሁም እያሽቆለቆለ የሄደው የዓለም የሥነ ምግባር ደረጃ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ልጆች ይህን ጎጂ ተጽዕኖ መቋቋም እንዲችሉ ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ሊማሩ ይገባል። አለበለዚያ ሲያድጉ ኃላፊነት የሚሰማቸውና በሥነ ምግባር የታነጹ ሰዎች ሊሆኑ መቻላቸው አጠራጣሪ ይሆናል።
የመፍትሔ ሐሳቦች፦
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱትን ጨምሮ ብዙ ነጠላ ወላጆች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለውን የአምላክ ጥበብ እንደያዘ ስለሚያውቁ ከዚህ መጽሐፍ መመሪያ ለማግኘት ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ ስለሚበልጠው መሠረታዊ ሥርዓት ይኸውም እውነተኛ ፍቅር ስለማሳየት ምን እንደሚል እንመልከት።
“ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4-8
ወላጆች እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሲያሳዩ ልጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ። በፈረንሳይ የምትኖረውና ነጠላ ወላጅ የሆነችው ኮሌት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ብዙ ጊዜ ለልጆቼ እንደምወዳቸው እነግራቸዋለሁ። በተጨማሪም የአምላክ ስጦታ እንደሆኑና በዚህም ምክንያት ጥሩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እነግራቸዋለሁ። እነሱ ደግሞ በበኩላቸው ለእኔም ሆነ ለአባታቸው አክብሮት ማሳየትና ትሑቶች መሆን እንደሚጠበቅባቸው እገልጽላቸዋለሁ። ልጆቼ እነዚህን መመሪያዎች ማወቃቸው በቤታችን መተማመንና መከባበር እንዲኖር አስተዋጽኦ አድርጓል።”—መዝሙር 127:3
በፖላንድ የምትኖረው አና እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች፦ “ልጆቼ እርስ በርስ ሲጣሉ ኢየሱስ፣ ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ሁሉ እኛም ልናደርግላቸው እንደሚገባ ተናግሮ እንደነበር አስታውሳቸዋለሁ።” (ማቴዎስ 7:12) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሮቤርቶ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችሁ ሁለት ዓይነት የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ይኸውም የእናንተንና የሌላኛውን ወላጅ መሥፈርቶች ይማራሉ። ልጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርት እንዲጠብቁ በማድረጌ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እናታቸው እንደምትሻላቸው ሊያስቡ እንደሚችሉ አውቃለሁ።” ብዙ ነጠላ ወላጆች ተመሳሳይ ችግር ያጋጥማቸዋል። ሮቤርቶ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሌላኛው ወላጅ፣ ልጆቹ እሱን ይበልጥ እንዲወዱት ለማድረግ ሲል ስጦታዎች ይሰጣቸው ይሆናል። እንዲህ ያለውን አካሄድ ላለመከተል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል፤ ሆኖም ከልጆቹ ጋር በግልጽ መወያየት ጥሩ ውጤት ያስገኛል።”
በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሠረት መኖር ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም ውጤቱ የሚያስቆጭ አይደለም! በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ሣራ የተባለች አንዲት ነጠላ ወላጅ እንዲህ ትላለች፦ “ልጆቼ በይሖዋ መመሪያ በማደጋቸው ደስተኛ ነኝ። በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳጋጠሙን ባይካድም አምላክ ምንጊዜም ከጎናችን ነበር።”