መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ይታይልኝ ባይ መሆን ተገቢ ነው?
“በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች፣ ታዋቂ የሆነ ዲዛይነር ስም ያለበት ጂንስ መልበሳቸው ወይም ሌላ ዕቃ መጠቀማቸው የበታችነት ስሜታቸውን ለማሸነፍና ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል፤ ‘እኔ እኮ ተራ ሰው አይደለሁም፤ ካላመናችሁኝ የለበስኩትን ልብስ ተመልከቱ!’ የሚሉ ያህል ነው።”—ቼተር ሜሰን፣ የሥነ ልቦና ምሁር
አንዳንድ ሰዎች የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ ሲሉ ታዋቂ የሆነ ዲዛይነር ስም ያለባቸውን ዕቃዎቻቸውን ወይም ሌላ ምርጥ ንብረታቸውን ለማሳየት ይጣጣራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ዋሽንግተን ፖስት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደገለጸው በአንድ የእስያ አገር “በቅርቡ ሀብታም የሆኑ ሰዎች የቅንጦት ዕቃዎችን ይኸውም የፈረንሳይ ቦርሳዎችን፣ ውድ የጣሊያን መኪኖችንና የመሳሰሉትን የሚወዱ ሲሆን [ሀብታቸውን] ማሳየት ያስደስታቸዋል።”
እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ለፍቶ ባገኘው ሀብቱ ቢደሰት ምንም ስህተት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው” ይላል። (መክብብ 3:13) ይሁን እንጂ ይታይልኝ ማለት ጥበብ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
‘ባለጠጎች ብዙ ወዳጆች አሏቸው’
የይታይልኝ መንፈስ የሚያንጸባርቁ ሀብታሞች ወይም ሀብታም መስለው መታየት የሚፈልጉ ሰዎች የሚኖሯቸው ምን ዓይነት ወዳጆች ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ድኾችን ወዳጆቻቸው እንኳ ይጠሏቸዋል፤ ባለጠጎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው” በማለት በዚህ ረገድ በብዙዎች ዘንድ የሚታየውን ዝንባሌ ይጠቁመናል።—ምሳሌ 14:20
በሌላ አባባል፣ ባለጠጎች ያሏቸው “ብዙ ወዳጆች” ጓደኝነታቸው ከሰዎቹ ጋር ሳይሆን ከንብረታቸው ጋር ነው ማለት ነው። እነዚህ ወዳጅ ተብዬዎች ከባለጠጎቹ ጋር ጓደኝነት የሚመሠርቱትም ሆነ የሚያሞካሿቸው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ወዳጅ ተብዬዎች የሚናገሩት የሙገሳ ንግግር ‘መጎምጀትን ለመሸፈን የሚቀርብ ሰበብ’ እንደሆነ ይገልጻል።—1 ተሰሎንቄ 2:5
ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምፈልገው ምን ዓይነት ወዳጆችን ነው? ለንብረቴ ሲሉ የሚጠጉኝ ዓይነት ሰዎችን ነው? ወይስ እኔን በማንነቴ የሚወዱኝን እውነተኛ ጓደኞች?’ ጥሩ ጓደኞች ማግኘት አለማግኘታችን የተመካው በባሕርያችን ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።
‘በትሑት ዘንድ ጥበብ ትገኛለች’
ይታይልኝ ማለት የሚያስከትለውን ሌላውን ችግር ደግሞ በጥንቷ ኢየሩሳሌም ይኖር ከነበረው ከንጉሥ ሕዝቅያስ ታሪክ ማየት ይቻላል። በአንድ ወቅት ሕዝቅያስ ከባቢሎን ተልከው ለመጡ ባለሥልጣናት ‘በግምጃ ቤቱ ያለውን በሙሉ አሳያቸው።’ የሕዝቅያስ ታላቅ ሀብት ጎብኚዎቹን ሳያስደንቃቸው አልቀረም። በሌላ በኩል ደግሞ ንብረቱን ለመውሰድ እንዲመኙ አድርጓቸውም ሊሆን ይችላል። እነሱ ከሄዱ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ለሕዝቅያስ ሀብቱ በሙሉ “ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በእርግጥ [እንደሚመጣና] አንዳች የሚቀር ነገር” እንደማይኖር በድፍረት ነገረው። ደግሞም እነዚህ ቃላት ተፈጽመዋል! ከዓመታት በኋላ ባቢሎናውያን ተመልሰው በመምጣት የሕዝቅያስ ቤተሰብን ሀብት በሙሉ ማርከው ወሰዱ።—2 ነገሥት 20:12-17፤ 24:12, 13
ዛሬም በተመሳሳይ ‘ሀብቴ ይታይልኝ’ የሚሉ ሰዎች ሀብታቸውን በሙሉ አሊያም የተወሰነውን ሊያጡ ይችላሉ። በሜክሲኮ ስለ ወንጀልና ደህንነት የወጣ አንድ ዘገባ እንደሚከተለው ይላል፦ “በሜክሲኮ ሲቲ ሌሎችን ለማስደመም ሲሉ ሀብታቸው እንዲታይላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሌቦችን ይስባሉ። ውድ ጌጣጌጦችንና ሰዓቶችን ማድረግ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደያዙ ማሳየት አላስፈላጊ ትኩረት ይስባል።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሀብት እንዳንመካ’ የሚሰጠንን ኤርምያስ 9:23) በተጨማሪም ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል።
ምክር መከተል ምንኛ የተሻለ ነው! (በሌሎች መልካም ባሕርያት ላይ ትኩረት አድርጉ
ልኩን የሚያውቅና ትሑት የሆነ ሰው ‘ኑሮዬ ይታይልኝ’ የሚል ራስን ከፍ የማድረግ መንፈስ ከማንጸባረቅ ይልቅ በሌሎች መልካም ባሕርያትና በጠንካራ ጎናቸው ላይ ያተኩራል። ፊልጵስዩስ 2:3 “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጋችሁ በትሕትና አስቡ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ” በማለት ይናገራል። በገላትያ 5:26 ላይም “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ” የሚል ሐሳብ እናገኛለን።
እንዲኖሩህ የምትፈልገው ለንብረትህ ሲሉ የሚጠጉህ ጓደኞች ነው? ወይስ በማንነትህ የሚወዱህ ጓደኞች?
የአምላክን ቃል በማጥናት ጥበብ የሚያዳብሩ ሰዎች፣ የእውነተኛ ወዳጅነት መሠረቱ ራስ ወዳድ አለመሆንና እርስ በርስ መከባበር እንደሆነ እንዲሁም ሀብት ቢጠፋ እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ወዳጅነት እንደሚዘልቅ ያውቃሉ። እንዲያውም እውነተኛ ወዳጅነት ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ምሳሌ 17:17 እውነተኛ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው” ይላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጠቢብ የሆነ ሰው የሚጥረው አምላክን ለማስደሰት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው፣ አምላክ በውጫዊ ነገሮች እንደማይደለል ከዚህ ይልቅ “የተሰወረ የልብ ሰው” የተባለውን ውስጣዊ ማንነታችንን እንደሚመለከት ያውቃል። (1 ጴጥሮስ 3:4) በመሆኑም ግሩም የሆኑ ባሕርያትን በማዳበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ይጥራል። (ኤፌሶን 4:24) ከእነዚህ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ በሚክያስ 6:8 ላይ ተጠቅሰዋል፤ ጥቅሱ “እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” ይላል።
እውነት ነው፣ በዛሬው ዓለም ውስጥ ትሕትና ወይም ልክን ማወቅ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ባሕርይ አይደለም፤ ለነገሩ ይህ ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን አያስገርማቸውም። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “መጨረሻዎቹ ቀኖች” ሲናገር አብዛኞቹ ሰዎች “ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . [እንዲሁም] በኩራት የተወጠሩ” እንደሚሆኑ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ያለኝ ነገር ይታይልኝ የሚሉ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በቀላሉ ተቀባይነት እንደሚያገኙ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የእነሱ ባሕርይ ሊጋባብን ስለሚችል አምላክ “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” የሚል ምክር ሰጥቶናል።