የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
የተሻለ ሕይወት ፍለጋ
የተሻለ ሕይወት ፍለጋ
ጆርጅ በጣም ጨንቆታል። ምክንያቱም ለቤተሰቡ የሚበቃ ምግብ ማቅረብ አልቻለም። በዚህ ላይ ደግሞ ጎረቤቶቹ የታመሙ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ በረሃብ ክፉኛ ተጠቅተዋል። ጆርጅ ከሚኖርበት አገር በስተ ደቡብ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አንድ የበለጸ አገር ይገኛል። በመሆኑም ጆርጅ ወደዚያ አገር ሄዶ ለመሥራት በኋላም ቤተሰቡን እሱ ጋር ለማምጣት አሰበ።
ፓትሪሻም ወደ ሌላ አገር ሄዶ ጥሩ ሕይወት የመምራት ሕልም ነበራት። በአገሯ ሥራ የሌላት ከመሆኑም በላይ ሥራ የማግኘት አጋጣሚዋም በጣም ጠባብ ነበር። ፓትሪሻ ከናይጄሪያ ተነስታ በአልጄሪያ በኩል አድርጋ ወደ ስፔን ለመግባት ወሰነች፤ ሆኖም የሰሃራን በረሃ ማቋረጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አልተገነዘበችም። ፓትሪሻ እንዲህ ብላለች፦ “በዚያን ወቅት ነፍሰ ጡር የነበርኩ ሲሆን ልጄ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራት ቆርጬ ነበር።”
ሬቸል ወደ አውሮፓ በመሄድ ጥሩ ኑሮ ለመጀመር ፈልጋለች። በፊሊፒንስ የነበራትን ሥራ አጥታ የነበረ ሲሆን ዘመዶቿ ውጭ አገር ብትሄድ የቤት ሠራተኛ ሆና የመቀጠር ሰፊ አጋጣሚ እንዳላት ይነግሯት ነበር። በመሆኑም ለአውሮፕላን መሳፈሪያ የሚሆን ገንዘብ ከተበደረች በኋላ ባልዋንና ሴት ልጇን ተሰናብታ ወደ አውሮፓ አቀናች። ቤተሰቧን ስትሰናበት ግን መጨረሻ ላይ “አይዟችሁ የምንለያየው ለትንሽ ጊዜ ነው” ብላቸው ነበር።
ባለፉት አሥርተ ዓመታት እንደ ጆርጅ፣ ፓትሪሻና ሬቸል ያሉ ከ200 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ትውልድ አገራቸውን ትተው ወደ ሌላ አገር እንደተሰደዱ ይገመታል። አንዳንዶቹ ከትውልድ አገራቸው የወጡት በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋና በደረሰባቸው ግፍ ምክንያት ቢሆንም አብዛኞቹ የወጡት ግን በኢኮኖሚ ምክንያት ነው። ከአገራቸው የወጡ ሰዎች በሚሄዱበት አገር ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል? ሁሉም ያለሙትን የተሻለ ሕይወት አግኝተዋል? አንድ ወላጅ የተሻለ ገቢ ፍለጋ ቤተሰቡን ትቶ ወደ ሌላ አገር ሲሄድ ልጆች ምን ያጋጥማቸዋል? ለእነዚህ ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች ተመልከት።
ጉዞውና አዲስ ሕይወት መጀመር
ብዙ ጊዜ፣ ወደ ሌላ አገር ሲኬድ የሚያጋጥመው የመጀመሪያ ፈተና ጉዞው ራሱ ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ጆርጅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘው በጥቂት ምግብ ብቻ ነው። “ጉዞውን ሳስብ አሁን ድረስ ይዘገንነኛል” ብሏል። የሚገርመው ብዙዎቹ ስደተኞች ያሰቡት አገር ሳይደርሱ መንገድ ላይ ይቀራሉ።
የፓትሪሻ ግብ ስፔን መድረስ ነበር። ወደ ስፔን ለመሄድ ክፍት በሆነ የጭነት መኪና የሰሃራን በረሃ ማቋረጥ አስፈልጓታል። እንዲህ ብላለች፦ “ከናይጄሪያ 25 የምንሆን ሰዎች በአንድ የጭነት መኪና ታጭቀን ወደ አልጄሪያ የተጓዝን ሲሆን መንገዱም አንድ ሳምንት ፈጅቶብናል። መንገድ ላይ በርካታ ሬሳዎችንና ሊሞቱ የሚያጣጥሩ ሰዎችን አይተናል። እነዚህ ሰዎች ርኅራኄ የሌላቸው የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች በየመንገዱ ጥለዋቸው የሄዱ ሳይሆኑ አይቀሩም።”
የቤት ሠራተኛ ለመሆን ያሰበችው ሬቸል ከጆርጅና ከፓትሪሻ በተለየ ወደ አውሮፓ የተጓዘችው በአውሮፕላን ነበር። ይሁንና የሁለት ዓመት ልጇ ናፍቆት ያን ያህል የሚጠናባት አልመሰላትም ነበር። ሁኔታውን አስመልክታ ስትናገር “ትንሽ ልጅ የያዘች እናት ባየሁ ቁጥር ያመኝ ነበር” ብላለች።
ጆርጅ የሄደበትን አገር ለመልመድ ብርቱ ትግል ጠይቆበታል። ወደ ቤተሰቡ ገንዘብ ሳይልክ የተወሰኑ ወራት አልፈዋል። “በብቸኝነትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳለቅስ የማድርባቸው ብዙ ሌሊቶች ነበሩ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።
ፓትሪሻ በአልጄሪያ በርካታ ወራት ከቆየች በኋላ ሞሮኮ ድንበር ደረሰች። እንዲህ ብላለች፦ “ሞሮኮ ድንበር ላይ ሴት ልጅ ተገላገልኩ። እዚያም ስደተኛ ሴቶችን ጠልፈው በዝሙት አዳሪነት እንዲሠሩ ከሚያስገድዱ ሰዎች መደበቅ ነበረብኝ። በመጨረሻ ወደ ስፔን የሚያሻግረውን አደገኛ የባሕር ጉዞ ለመጀመር በቂ ገንዘብ አገኘሁ። የተሳፈርንበት ጀልባ ያረጀ ከመሆኑም በላይ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተሳፋሪዎች ለማጓጓዝ የሚያስችል አልነበረም። ወደ ጀልባው የሚገባውን ውኃ በጫማዎቻችን እየቀዳን ወደ ውጪ መድፋት ነበረብን! ስፔን ስንደርስ በጣም ደክሜ ስለነበር ቆሞ መሄድ እንኳ አልቻልኩም።”
እርግጥ ነው፣ ወደ ሌላ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርባቸው በጉዞ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር ብቻ አይደለም። በሚሄዱበት አገር ውስጥ በቋንቋና በባሕል ረገድ የሚያጋጥማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲሁም በአገሩ የዜግነት ወይም የነዋሪነት መብት ለማግኘት የሚጠይቀውን ወጪና ውጣ ውረድ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች ጥሩ ሥራ፣ የተሻለ መኖሪያ፣ ትምህርትና ሕክምና ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። በተጨማሪም የመንጃ ፈቃድ ማግኘት ወይም የባንክ ሒሳብ መክፈት ሊያስቸግራቸው ይችላል። ብዙ ጊዜ ደግሞ ሕጋዊ መኖሪያ የሌላቸው ስደተኞች በአነስተኛ ገንዘብ ስለሚቀጠሩ ጉልበታቸው ይበዘበዛል።
ሌላው ከግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ገንዘብ ነው። በእርግጥ ገንዘብ ልንታመንበት የሚገባ ነገር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ግሩም ምክር ይሰጠናል፦ “ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤ . . . በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፤ ወዲያው ይጠፋል፤ ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በእርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል።” (ምሳሌ 23:4, 5) በተጨማሪም እንደ ፍቅር፣ የስሜት መረጋጋትና የቤተሰብ አንድነት ያሉት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በገንዘብ ሊገዙ እንደማይችሉ አስታውስ። ወላጆች ለገንዘብ ያላቸው ፍቅር አንዳቸው ለሌላው ወይም ለልጆቻቸው ካላቸው “ተፈጥሯዊ ፍቅር” እንዲበልጥ መፍቀዳቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው!—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም መንፈሳዊ ፍላጎት አለን። (ማቴዎስ 5:3) በመሆኑም ኃላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች፣ ከአምላክ የተቀበሉትን ስለ አምላክ ዓላማና ስለ መመሪያዎቹ ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት ለመወጣት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ።—ኤፌሶን 6:4
አብሮ መኖር—ከገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር
ከአገራቸው የወጡ ሰዎች ያሳለፉት ታሪክ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ ከተጠቀሱት ከጆርጅ፣ ከፓትሪሻና ከሬቸል ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች የሚመሳሰሉባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አንድ ወላጅ ከልጆቹ ተለያይቶ ሌላ አገር ሲኖር ወይም አንድ ባለትዳር ከትዳር ጓደኛው ተነጥሎ ወደ ውጭ አገር ሲሄድ ቤተሰቡ ይሠቃያል፤ ቤተሰቡ በድጋሚ አብሮ መኖር እስኪጀምር ድረስም በርካታ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ። ለምሳሌ የጆርጅ ቤተሰብ እንደገና አብሮ ለመኖር አራት ዓመት ፈጅቶበታል።
ሬቸል ወደ ፊሊፒንስ ተመልሳ ልጇን የወሰደቻት ከተለያዩ ከአምስት ዓመታት ገደማ በኋላ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ፓትሪሻ ስፔን የደረሰችው መንገድ ላይ የወለደቻትን ልጇን እንደታቀፈች ነበር። “ያለችኝ ቤተሰብ እሷ ብቻ ስለሆነች እሷን ለመንከባከብ የተቻለኝን ያህል ጥረት እያደረግኩ ነው” ብላለች።
ከአገራቸው የወጡ ብዙ ስደተኞች የብቸኝነት ስሜት፣ የኢኮኖሚ ችግር እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ከቤተሰብ ርቆ መኖር የመሳሰሉ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም የሄዱበትን አገር መልቀቅ አይፈልጉም። አብዛኞቹ ስደተኞች ከአገራቸው ወጥተው ወደሚፈልጉበት አገር ለመድረስ የከፈሉት መሥዋዕትነት በጣም ከፍተኛ ነው፤ በመሆኑም ሁሉ ነገር እንዳሰቡት በማይሆንበት ጊዜ የሚደርስባቸውን ኀፍረትና ውርደት ተቋቁመው ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ድፍረት ያሳዩት በጣም ጥቂቶች ናቸው።
እንዲህ ዓይነት ድፍረት ካሳዩ ሰዎች መካከል አንዱ በፊሊፒንስ ይኖር የነበረው አለን ነው። በስፔን ጥሩ ሥራ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ግን ወደ አገሩ ተመለሰ። እንዲህ ብሏል፦ “የባለቤቴንና የልጄን ናፍቆት መቋቋም አልቻልኩም። ሁላችንም አብረን መሄድ ካልቻልን በስተቀር ሁለተኛ ከአገሬ ወጥቼ ላለመሥራት ወሰንኩ። ያደረግነውም ይህንኑ ነበር። ምክንያቱም ቤተሰብ ከገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።”
ፓትሪሻ እንደተገነዘበችው ከገንዘብ የሚበልጥ ሌላ ነገር አለ። ወደ ስፔን የሄደችው “አዲስ ኪዳን” ወይም የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ ይዛ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፉ ከክፉ ነገር እንደሚጠብቀኝ አድርጌ እመለከተው ነበር። አንድ ቀን፣ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ሴት ጋር ተገናኘሁ። ከዚያ በፊት የዚህን ሃይማኖት ተከታዮች ለማነጋገር ፍላጎት አልነበረኝም። በመሆኑም ይህች ሴት እምነቷ ስህተት መሆኑን ለማጋለጥ ብዙ ጥያቄዎች ጠየቅኳት። እሷ ግን ስለ እምነቷ በትክክል ማስረዳት የቻለች ከመሆኑም በላይ ለጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ሰጠችኝ፤ እንዲህ ማድረግ ትችላለች ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም ነበር።”
ፓትሪሻ ዘላቂ ደስታና አስተማማኝ ተስፋ ማግኘታችን የተመካው በገንዘብ ወይም በምንኖርበት አገር ሳይሆን ስለ አምላክና እሱ ለእኛ ስላለው ዓላማ በማወቅ ላይ እንደሆነ ከተማረችው ነገር መገንዘብ ችላለች። (ዮሐንስ 17:3) ፓትሪሻ በርካታ ነገሮች የተማረች ሲሆን ከእነዚህ መካከል እውነተኛው አምላክ ስም እንዳለውና ስሙም ይሖዋ መሆኑን ማወቋ ይገኝበታል። (መዝሙር 83:18 NW) በተጨማሪም አምላክ በቅርቡ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት ድህነትን በሙሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አነበበች። (ዳንኤል 7:13, 14) መዝሙር 72:12, 14 “[ኢየሱስ] ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል” ይላል።
አንተም ጊዜ ወስደህ መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር እናበረታታሃለን። መለኮታዊ ጥበብ ያለው ይህ መጽሐፍ፣ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይተህ እንድታውቅ፣ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ እንድታደርግና የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ፈተና በደስታና በተስፋ እንድትወጣ ይረዳሃል።—ምሳሌ 2:6-9, 20, 21