ከዓለም አካባቢ
ዩናይትድ ስቴትስ
የዩናይትድ ስቴትስ የአገር ደህንነት መሥሪያ ቤት ሪፖርት እንደሚያሳየው ባለፉት አሥር ዓመታት የአውሮፕላን ማረፊያ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች 50 ሚሊዮን የሚያህሉ የተከለከሉ ዕቃዎችን ወርሰዋል። የደህንነት ተቆጣጣሪዎች በ2011 ብቻ ባካሄዱት ፍተሻ ተሳፋሪዎች ወደ አውሮፕላን ይዘዋቸው ሊገቡ የነበሩ 1,200 የሚያህሉ የጦር መሣሪያዎችን ይዘዋል። አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች የጦር መሣሪያ መያዛቸውን እንደዘነጉ ተናግረዋል።
ብራዚል
የትምህርት ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች ሳያስፈቅዱ ከክፍል እንዳይቀሩ ለመቆጣጠር ሲሉ በትምህርት ቤት ዩኒፎርም ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ ቺፖችን ማስገባት ጀምረዋል። ልጁ ትምህርት ቤት ሲደርስ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያው ለወላጁ አንድ የጽሑፍ መልእክት የሚልክ ሲሆን ልጁ ከ20 ደቂቃ በላይ ከዘገየ ደግሞ ሌላ ዓይነት የጽሑፍ መልእክት ይልካል።
ኖርዌይ
የሉተራን ቤተ ክርስቲያን የኖርዌይ የመንግሥት ሃይማኖት መሆኑ ቀርቷል። የኖርዌይ ፓርላማ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ቁርኝት መላላት አለበት በሚል ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፀ ውሳኔ አስተላልፏል።
ቼክ ሪፑብሊክ
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከቼክ ሠራተኞች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በሥራ ገበታቸው ላይ በማይሆኑበት ጊዜ ከሥራቸው ጋር ለተያያዙ የስልክ ጥሪዎች፣ ኢ-ሜይሎችና የጽሑፍ መልእክቶች መልስ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ሆኖ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወዲያውኑ መልስ አለመስጠት ጨዋነት የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ሕንድ
ባለፉት 20 ዓመታት የእህል ምርት 50 በመቶ የጨመረ እንዲሁም የስንዴና የሩዝ ክምችት ከ71 ሚሊዮን ቶን በላይ የደረሰ ቢሆንም ሕንድ ዛሬም ሕዝቦቿን በሙሉ መመገብ አልቻለችም። ከተከማቸው እህል መካከል ለሕንዳውያን የሚደርሰው 40 በመቶ ገደማ የሚሆነው ብቻ ነው። ለዚህ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ሙስናና ብክነት ይጠቀሳሉ።