ንድፍ አውጪ አለው?
“የማየት ችሎታ” ያላቸው የብሪትል ስታር አጥንቶች
በውቅያኖስ ሥር በሚገኙ ቋጥኞች ላይ የሚኖረው ብሪትል ስታር የተባለው የባሕር ፍጥረት በሰውነቱ ውጨኛ ክፍል ላይ ራሱን ለመከላከል የሚጠቀምበት አስደናቂ መሣሪያ አለው። በሰውነቱ ውጨኛ ክፍል ላይ የሚገኙት እነዚህ አጥንቶች ጥቃቅን በሆኑ ሌንሶች የተሞሉ ናቸው፤ በመሆኑም ራሱን ለመከላከል የሚጠቀምበት ይህ የሰውነቱ ክፍል እንደ ዓይንም ሆኖ ያገለግለዋል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሔት፣ የሳይንስ ሊቃውንት የብሪትል ስታርን የአጥንት ሽፋን በሚመረምሩበት ጊዜ “እያንዳንዳቸው ከሰው ፀጉር የሚቀጥኑና በጣም የተጠጋጉ እንደ መስተዋት የጠሩ ጉብ ጉብ ያሉ ነገሮችን” እንደተመለከቱ ይገልጻል። እነዚህ እንደ መስተዋት ያሉ ጉብ ጉብ ያሉ ነገሮች ከካልሲየም ካርቦኔት (ካልሳይት) የተሠሩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ጥቃቅን ሌንሶች ናቸው፤ እነዚህ ሌንሶች ከአጥንቱ በታች ላሉ ብርሃን የመለየት ችሎታ እንዳላቸው ለሚታሰቡ ነርቮች ብርሃን አስተካክለው ያስተላልፋሉ። ከዚህም በላይ የሌንሶቹ ቅርጽ ትክክለኛ ምስል እንዲፈጠር የሚያስችል ነው።
ጆአና አይዘንበርግ የተባሉ የኬሚስትሪ ባለሙያ እንዳሉት ከሆነ ሁለት የተለያዩ ተግባራት ማከናወን የሚችለው የብሪትል ስታር አጥንት “በባዮሎጂ መስክ አንድ ነገር አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ በላይ ተግባራትን እንደሚያከናውን የሚገልጸውን አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ሐቅ የሚያሳይ ነው።”
ተመራማሪዎች ስለ ብሪትል ስታር በማጥናት ባገኙት እውቀት በመጠቀም ከካልሲየም ካርቦኔት የተሠሩ ጥቃቅን ሌንሶችን በአነስተኛ ወጪና ቀላል በሆነ ዘዴ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ ደርሰውበታል። እነዚህ ጥቃቅን ሌንሶች በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ፣ በብርሃን አማካኝነት የሚተላለፉ መረጃዎችን በኦፕቲክ ፋይበር ለማስተላለፍና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? “የማየት ችሎታ” ያለው የብሪትል ስታር አጥንት በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?