መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም
ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት ነው?
“የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱ ይኸውም ከዝሙት እንድትርቁ [ነው]።”—1 ተሰሎንቄ 4:3
ሰዎች ምን ይላሉ?
በአንዳንድ ባሕሎች፣ ትዳር ያልመሠረቱ ሁለት ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሰዎች በፈቃዳቸው የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምንም ችግር የለውም። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ወሲባዊ ድርጊቶችን ቢፈጽሙ ምንም ችግር እንደሌለው ተደርጎ ይታያል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸሙ አንዳንድ ወሲባዊ ድርጊቶችን ለመግለጽ “ዝሙት” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። አምላክ ሕዝቦቹ ‘ከዝሙት እንዲርቁ’ ይጠብቅባቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ዝሙት ልክ እንደ ምንዝር፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ስካር፣ ጣዖት አምልኮ፣ ነፍስ ግድያና ስርቆት ከባድ ኃጢአት ተደርጎ ተጠቅሷል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8
ጉዳዩ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?
አንደኛው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ በአመንዝሮች ላይ እንደሚፈርድ’ ስለሚያስጠነቅቅ ነው። (ዕብራውያን 13:4) ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላክ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሰጠውን ሕግ መታዘዛችን ለይሖዋ አምላክ ፍቅር እንዳለን ያረጋግጣል። (1 ዮሐንስ 5:3) እሱም በምላሹ ትእዛዛቱን የሚጠብቁ ሰዎችን ይባርካል።—ኢሳይያስ 48:18
ያልተጋቡ ሰዎች የፆታ ግንኙነት እስካልፈጸሙ ድረስ በማንኛውም ወሲባዊ ድርጊት ቢካፈሉ ስህተት ነው?
“ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።”—ኤፌሶን 5:3
ሰዎች ምን ይላሉ?
ያልተጋቡ ጓደኛሞች የፆታ ግንኙነት እስካልፈጸሙ ድረስ ሌሎች ወሲባዊ ድርጊቶችን ቢፈጽሙ ምንም ስህተት እንደሌለው የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ከሥነ ምግባር ውጪ ስለሆኑ ወሲባዊ ድርጊቶች ሲገልጽ የሚጠቅሰው ዝሙትን ብቻ ሳይሆን ከፆታ ጋር የተያያዘ “ርኩሰት” እና “ብልግና” መፈጸምን ጭምር ነው። (2 ቆሮንቶስ 12:21) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የፆታ ግንኙነት ባይፈጸምም እንኳ አምላክ የማይደሰትባቸው ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸሙ የተለያዩ ወሲባዊ ድርጊቶች አሉ።
ፆታን በሚመለከት የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልእክት ግልጽ ነው፤ ይኸውም ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን መፈጸም የሚችሉት የተጋቡ ወንድና ሴት ብቻ ናቸው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለፍትወተ ሥጋ መጎምጀትን’ ያወግዛል። (1 ተሰሎንቄ 4:5) ይህ ምን ማለት ነው? ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በእኩል ደረጃ ሊሠራ የሚችል አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንዲት ሴት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የፆታ ግንኙነት ላለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ይሆናል። ያም ሆኖ ሌሎች ወሲባዊ ድርጊቶችን ከጓደኛዋ ጋር ትፈጽማለች። እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማድረጋቸው የእነሱ ያልሆነን ነገር እየጎመጁ ነው። በመሆኑም “ለፍትወተ ሥጋ በመጎምጀት” ምክንያት በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናሉ። ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ እንዲህ ዓይነት ስግብግብነት ማሳየት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘ ነው።—ኤፌሶን 5:3-5
ከፆታ ብልግና መራቅ የምትችለው እንዴት ነው?
“ከዝሙት ሽሹ።”—1 ቆሮንቶስ 6:18
ጉዳዩ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።—ቆላስይስ 3:5, 6
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ‘ከዝሙት እንዲሸሹ’ ይመክራል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህ ማለት አንድ ሰው የፆታ ብልግና እንዲፈጽም ከሚመራው ማንኛውም ነገር በተቻለ መጠን መራቅ ይኖርበታል። (ምሳሌ 22:3) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለገ አምላክ ከፆታ ጋር በተያያዘ ያወጣቸውን መመሪያዎች ችላ ከሚሉ ሰዎች ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
በሌላ በኩል ደግሞ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ሐሳቦችን ወደ አእምሮ ማስገባት የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። (ሮም 8:5, 6) ስለዚህ ወሲባዊ ድርጊትን ከሚያሳይ ወይም አምላክን የሚያሳዝን ፆታዊ ድርጊት መፈጸምን ከሚያበረታታ ሙዚቃ፣ ቪዲዮ፣ ጽሑፍ ወይም ሌላ ማንኛውም ነገር መራቅ ብልህነት ነው።—መዝሙር 101:3