የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?
ተስፋ አለ
“ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:11
ሕይወት “በመከራ የተሞላ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በዛሬው ጊዜ አሳዛኝ ሁኔታ የማያጋጥመው ሰው የለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ዓይነት የተስፋ ጭላንጭል አይታያቸውም፤ ወይም የተሻለ ነገር ይመጣል ብለው አያስቡም። አንተስ የሚሰማህ እንዲህ ነው? ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለአንተ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የሚሰጠው እውነተኛ ተስፋ አለ። ለምሳሌ ያህል፦
የይሖዋ አምላክ ዓላማ አሁን ካለው በጣም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:28
ይሖዋ አምላክ ምድራችንን ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:21-25
ይሖዋ የገባው ይህ ቃል እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል፦
“የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
ይህ ተስፋ የሕልም እንጀራ አይደለም። ይሖዋ አምላክ ይህን ተስፋ እውን እንደሚያደርገው ምን አያጠያይቅም፤ ደግሞም ይህን ለማድረግ ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ አስተማማኝ ነው፤ እንዲሁም “መኖር ምን ዋጋ አለው?” ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
ይህን አስታውስ፦ ስሜትህ በሚናወጥ ባሕር ላይ እንዳለ ጀልባ እየወጣና እየወረደ ቢያስቸግርህም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደ መልሕቅ ሆኖ ሊያረጋጋህ ይችላል።
ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን እውነተኛ ተስፋ መመርመር ጀምር። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም jw.org/am * በተባለው ድረ ገጻቸው ላይ ጠቃሚ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።
^ አን.11 ለጥቆማ ያህል፦ jw.org/amን ክፈት፤ ከዚያም “የሕትመት ውጤቶች” በሚለው ሥር የሚገኘውን “የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት” ክፈት። ቤተ መጻሕፍቱን ከከፈትክ በኋላ “የመንፈስ ጭንቀት” ወይም “ራስን መግደል” እንደሚሉት ያሉ ለፍለጋ የሚረዱ ቁልፍ ቃላትን ተጠቅመህ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።