ከዓለም አካባቢ
ዩናይትድ ስቴትስ
በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የሎስ አንጀለስ ከተማ፣ በ1,215 ካሬ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ያሉትን ወደ 4,500 የሚጠጉ የትራፊክ መብራቶች በሙሉ እርስ በርሳቸው ተቀናጅተው የሚሠሩበትን ሥርዓት ዘርግታለች። ኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጸው ከሆነ ሎስ አንጀለስ “ይህን ለማድረግ በዓለም የመጀመሪያዋ ትልቅ ከተማ ሆናለች።”
ዓለም
በዓለም ዙሪያ ከጤና ጋር በተያያዘ የተደረገ አንድ ግምገማ እንዳሳየው ከልክ ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከ1990 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ውስጥ 82 በመቶ ጨምሯል። በቂ ምግብ አለማግኘት ዛሬም ድረስ በብዙ አገሮች ችግር ማስከተሉ እንዳለ ሆኖ፣ ከመጠን በላይ በሆነ ውፍረት ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ግን በቂ ምግብ ባለማግኘት ከሚሞቱት በሦስት እጥፍ ይበልጣል። እንደ እውነቱ ከሆነ “ከ20 ዓመት በፊት ሰዎች በቂ ምግብ የማያገኙባት የነበረችው ዓለማችን አሁን ግን ታዳጊ በሆኑ አገሮች ሳይቀር ከበቂ በላይ የሆነ ምግብ እንዲሁም ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች የሚገኝባት መሆኗ ለበሽታ ዳርጎናል” በማለት ከዋነኞቹ ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት ማጂድ ኢዛቲ ተናግረዋል።
ሚድዌይ ደሴት
“በዓለማችን ላይ ካሉ የዱር አእዋፍ መካከል በዕድሜ አንጋፋ” እንደሆነች የሚነገርላት ላይሳን አልባትሮስ የተባለችው ወፍ ተጨማሪ ጫጩት ፈልፍላለች። ለመሆኑ ዕድሜዋ ምን ያህል ይሆናል? የመከታተያ ቀለበት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገላት በ1956 ሲሆን በዚያ ጊዜ ቢያንስ አምስት ዓመት ይሆናት ነበር፤ በመሆኑም አሁን ዕድሜዋ ከ60 ዓመት አልፏል ማለት ነው። ይህች አልባትሮስ በሕይወት ዘመኗ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ኪሎ ሜትር እንደበረረች የሚገመት ሲሆን ይህ ርቀት ከምድር ወደ ጨረቃ ደርሶ መልስ ከአራት እስከ ስድስት ጊዜ ይሆናል።
ደቡብ አፍሪካ
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከደቡብ አፍሪካ ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የቆዳ ቀለማቸውን ለማንጣት ሲሉ ቆዳ የሚያነጡ ሳሙናዎችና ቅባቶች ይጠቀማሉ። እንደነዚህ ያሉት ቆዳን ለማንጣት የሚያገለግሉ ምርቶች አደገኛ በመሆናቸው በብዙ አገሮች ታግደዋል። ከሚያስከትሉት አደጋዎች መካከል የተለያዩ የካንሰር በሽታዎች፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ሽፍታና የቆዳ መበላሸት ይገኙባቸዋል።