ከዓለም አካባቢ
እስራኤል፣ ዮርዳኖስና ፍልስጤም
የሙት ባሕር ስፋት በየዓመቱ 1 ሜትር ያህል እየቀነሰ ነው። አንዳንድ ሰዎች፣ ሐይቁ በ2050 ሙሉ በሙሉ ሊደርቅ ይችላል ብለው ይፈራሉ። ባለሥልጣናት ለዚህ ችግር መፍትሔ እያፈላለጉ ነው። መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የቀረበው አንዱ አማራጭ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ የሚጠቀሙበትን ውኃ ከቀይ ባሕር አጣርቶ በመውሰድ ከዚህ ሂደት የተረፈውን ጨዋማ ውኃ ወደ ሙት ባሕር ማስገባት ነው። በዚህ አማራጭ የማይስማሙ ምሁራን፣ ይህ ዘዴ የሙት ባሕርን ልዩ ሥነ ምህዳር ሊጎዳ እንደሚችል ገልጸዋል።
ጀርመን
አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ባካሄደው ጥናት መሠረት በገና በዓል ዕለት በልብ በሽታ ምክንያት ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በዓመት ውስጥ ከሌላው ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሦስተኛ ይበልጣል። ሰዎቹን ለልብ ሕመም እንዲጋለጡ ላደረጋቸው ከፍተኛ ውጥረት ዋናው መንስኤ ለገና በዓል የሚሆን ስጦታ ለመግዛት ስለሚባክኑ፣ ቤተሰቦችና ጓደኞች ደግሞ ትልቅ ስጦታ ይሰጠኛል ብለው ስለሚጠብቁ እንደሆነ ኩባንያው ገልጿል።
ብሪታንያ
የብሪታንያ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ዕድሜው 405 ዓመት እንደሆነ ይታሰብ የነበረውና በአይስላንድ የተገኘው ባለ ዛጎል የባሕር ፍጥረት በ2006 ያለጊዜው በሞተበት ወቅት ትክክለኛ ዕድሜው 507 ዓመት እንደነበረ አስታወቁ። ይህም በመዝገብ ከሰፈሩት እንስሳት መካከል በጣም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ እንስሳ * እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ትንሽ የባሕር እንስሳ የሞተው ተመራማሪዎች በማቀዝቀዣ ውስጥ አድርገው ወደ ቤተ ሙከራ ሲያጓጉዙት ነው።
ላቲን አሜሪካና የካሪቢያን አገሮች
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሀቫና፣ ኩባ በተደረገ የመሪዎች ስብሰባ ላይ፣ የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን አገሮች ማኅበር አባል የሆኑ 33 ብሔራት፣ በመካከላቸው የሚፈጠረውን ግጭት የኃይል እርምጃ መውሰድ ሳያስፈልጋቸው በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስለተስማሙ አገሮቻቸው ‘የሰላም ክልል’ እንደሆኑ ገልጸዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ባን ኪሙን ይገኙበታል።
^ አን.7 እዚህ ላይ “በጣም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ እንስሳ” የሚለው መግለጫ ለብዙ ሺህ ዓመታት ኖረዋል ተብለው የሚታሰቡትን እንደ ኮራል ያሉ ፍጥረታትን አይጨምርም።