የታሪክ መስኮት
አህጉራትን የከፋፈሉ አዋጆች
ክሪስቶፈር ኮሎምበስ ወደ አሜሪካ አህጉራት ለመጀመሪያ ጊዜ ካደረገው ጉዞ በ1493 ከተመለሰ በኋላ በስፔንና በፖርቱጋል ነገሥታት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፤ ይህም የሆነው አዲስ ከተገኙት አገሮች ጋር በተያያዘ የሚካሄደውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው እንዲሁም በቅኝ ግዛት የሚያስተዳድራቸው ማን እንደሆነ መስማማት ስላልቻሉ ነው። ስፔን ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አሌክሳንደር ስድስተኛ ዞር አለች።
ነገሥታትና ጳጳሳት አህጉራቱን ተቀራመቷቸው
ስፔን፣ ፖርቱጋልና ጳጳሳቱ አዲስ የሚገኙትን አገሮች የራሳቸው ለማድረግ ቀድሞውንም ቢሆን አስበው ነበር። በ1455 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኒኮላስ አምስተኛ፣ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ባለው የአፍሪካ ዳርቻ ላይ የሚገኙትን አገራትና ደሴቶች የማሰስ እንዲሁም ያገኙትን ሁሉ የግላቸው የማድረግ ሙሉ መብትን ለፖርቱጋሎች ሰጥተው ነበር። በ1479 የፖርቱጋሉ ንጉሥ አፎንሶ አምስተኛና ልጃቸው ልዑል ጆን፣ በአልካሱቨሽ ውል ላይ የካነሪ ደሴቶችን አስተዳደር ለስፔናውያኑ ፈርዲናንድና ኢዛቤላ አሳልፈው ሰጡ። በምላሹም ስፔን፣ ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ የመቆጣጠር እንዲሁም የማዴይራ፣ የኤዞርዝ እና የኬፕ ቨርዴ ደሴቶችን የማስተዳደር ሙሉ መብት ያላት ፖርቱጋል እንደሆነች እውቅና ሰጠች። ከሁለት ዓመት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲክስተስ አራተኛ፣ ከካነሪ ደሴቶች በስተ ደቡብና በስተ ምሥራቅ አዲስ የሚገኙ አገሮች በሙሉ የፖርቱጋል እንደሚሆኑ በመጥቀስ ይህንን ውል አጸደቁ።
ይሁንና የፖርቱጋሉ ንጉሥ ጆን (በዚህ ወቅት ዳግማዊ ጆን ተብለዋል)፣ ኮሎምበስ ያገኛቸው አገሮች የፖርቱጋል መሆን እንዳለባቸው ገለጹ። የስፔን ነገሥታት ይህ ሊዋጥላቸው አልቻለም፤ በመሆኑም ኮሎምበስ ያገኛቸውን አገሮች ወደ ክርስትና እምነት የመለወጥና በቅኝ ግዛት የማስተዳደር ሥልጣን ለስፔን እንዲሰጥ ለአዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ይኸውም ለአሌክሳንደር ስድስተኛ አቤቱታ አቀረቡ።
አሌክሳንደር ስድስተኛ በፊርማቸው ብቻ አህጉራቱን ለሁለት ከፈሏቸው
አሌክሳንደርም በምላሹ ሦስት አዋጆች እንዲወጡ አደረጉ። በመጀመሪያው አዋጅ ላይ አሌክሳንደር “ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ” በተሰጣቸው
ሥልጣን መሠረት የአዳዲሶቹን ግዛቶች ብቸኛ የባለቤትነት መብት ለስፔን ለዘላለም እንደሰጡ ገልጸዋል። በሁለተኛው አዋጅ ላይ ደግሞ ከኬፕ ቨርዴ ደሴቶች በስተ ምዕራብ 560 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ከሰሜን ወደ ደቡብ መስመር በማስመር የድንበር ወሰንን ለማወቅ የሚያስችል ምልክት እንዲኖር አድርገዋል። አሌክሳንደር፣ ከዚህ መስመር በስተ ምዕራብ የተገኘ ወይም የሚገኝ አገር ሁሉ የስፔን ግዛት እንደሚሆን ደነገጉ። በዚህ መንገድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በፊርማቸው ብቻ አህጉራቱን ለሁለት ከፈሏቸው! ሦስተኛው አዋጃቸው፣ የስፔንን ግዛት በማስፋት በስተ ምሥራቅ እስከ ሕንድ ድረስ ያለውን አካባቢ እንድትቆጣጠር የሚያደርግ ይመስላል። ይህ ደግሞ ንጉሥ ጆንን አስቆጣቸው፤ ምክንያቱም ዜጎቻቸው የአፍሪካን ጫፍ ዞረው የፖርቱጋልን ግዛት እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ካሰፉ ብዙም አልቆዩም ነበር።በካርታ ላይ አዲስ መስመር ማስመር
ጆን፣ በአሌክሳንደር * ሁኔታ በመሰላቸታቸው ከፈርዲናንድና ከኢዛቤላ ጋር በቀጥታ መደራደር ጀመሩ። ዊልያም በርንስታይን የተባሉ ጸሐፊ “የስፔን ነገሥታት፣ ጨካኝ የሆኑትን ፖርቱጋሎች ስለፈሩና አዲሱን ዓለም [የአሜሪካን አህጉራት] ለመቆጣጠር እየተጣደፉ ስለነበር ለመደራደር ፈቃደኞች ነበሩ” ብለዋል። በመሆኑም በ1494 ስምምነቱ በተካሄደበት የስፔን ከተማ ይኸውም በቶርደሲላስ የተሰየመ ውል ተፈረመ።
የቶርደሲላስ ውል፣ አሌክሳንደር ከሰሜን ወደ ደቡብ ያሰመሩትን መስመር ሳይነካ ምልክቱ ያለበት ቦታ በ1,480 ኪሎ ሜትር ወደ ምዕራብ እንዲጠጋ አደረገ። በዚህ መሠረት ፖርቱጋል፣ መላው አፍሪካና እስያ የእሷ “ንብረት” እንደሚሆን አስባ ነበር፤ አዲሱ ዓለም ደግሞ የስፔን ይሆናል። ይህ መስመር ወደ ምዕራብ እንዲንፏቀቅ መደረጉ ግን በወቅቱ ያልታወቀውና በኋላ ብራዚል የተባለው አገር አብዛኛው ክፍል በፖርቱጋል ሥር እንዲሆን አድርጓል።
ስፔንና ፖርቱጋል ያገኟቸውን አዳዲስ አገሮች በቁጥጥራቸው ሥር እንዲያደርጉና ግዛታቸውን እንዲያስከብሩ ሥልጣን የሰጧቸው አዋጆች ብዙ ደም መፋሰስ አስከትለዋል። እነዚህ ውሳኔዎች በአገሮቹ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች መብት ከጉዳይ ሳይቆጥሩ ለጭቆናና ለብዝበዛ የዳረጓቸው ከመሆኑም ሌላ ብሔራት በሥልጣን ሽኩቻ እንዲሁም የባሕር መስመሮችን በነፃነት ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ለብዙ ዘመናት እንዲዋጉ ምክንያት ሆነዋል።
^ አን.9 ምግባረ ብልሹ የሆኑትን እኚህን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-29 ላይ የወጣውን “አሌክሳንደር ስድስተኛ ሮም ፈጽሞ የማትረሳው ጳጳስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።