በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት

ሄሮዶተስ

ሄሮዶተስ

ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሕይወት ምን ይመስል ነበር? ሰዎች ምን ዓይነት ባሕል ነበራቸው? አርኪኦሎጂ ይህን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ መልስ ሊሰጠን ቢችልም ጥያቄዎቻችንን በሙሉ ግን አይመልስልንም። በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎችን አስተሳሰብ ለመረዳት በዘመኑ የነበረውን ዓለም ታሪክ ያጠና የነበረ ሰው የጻፋቸውን ጽሑፎች ማየት ይረዳናል። እንዲህ ያደረገ ከ2,400 ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ሄሮዶተስ የሚባል ሲሆን በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረ ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ ነው። ለመሆኑ የጽሑፍ ሥራው መጠሪያ ምንድን ነው? ዘ ሂስቶሪስ ይባላል።

ሄሮዶተስ በወቅቱ የተከናወኑትን ማለትም ግሪኮች ያካሄዷቸውን ጦርነቶች መንስኤ፣ በተለይ ደግሞ እሱ ልጅ እያለ በ490 እና በ480 ዓ.ዓ. ፋርሳውያን ያካሄዷቸውን ወረራዎች መንስኤ በጽሑፍ ማስፈር ጀምሮ ነበር። ዋናውን ጭብጡን ሳይለቅ፣ ፋርሳውያን ግዛታቸውን ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ ስለተነኩት ብሔራት ሁሉ ያገኘውን መረጃ ምንም ሳያስቀር በማስፈር ሰፋ ያለ ሐተታ አካቷል።

ከታሪክም በላይ

ሄሮዶተስ ጥሩ ተሰጥኦ ያለው ታሪክ ዘጋቢ ነው። የሚጽፈውን ታሪክ ያሟላል ብሎ የሚያስበውን ጥቃቅን ጉዳይ ጭምር በመጥቀስ ዝርዝር መረጃዎችን ሳይቀር መጻፍ ይወድ ነበር። ሄሮዶተስ በነበረበት ዘመን የነገሥታት ታሪክ በተሟላ መንገድ የሰፈረባቸው መዛግብት ካለመኖራቸው አንጻር እሱ ያዘጋጀው የጽሑፍ ሥራ በጣም የሚደነቅ ነው፤ ምክንያቱም በወቅቱ እንዲህ ያሉ ሰነዶች አልነበሩም ቢባል ይቀላል።

በዚያ ዘመን፣ ሰዎች የሠሯቸውን ጀብዱዎች ሐውልት ላይ በማስቀረጽ ጉራቸውን ለመንዛት ካልሆነ በስተቀር ታሪክ መዝግቦ የማስቀመጥ ጉዳይ የሚያሳስባቸው እምብዛም አልነበሩም። ሄሮዶተስ ስለሚጽፈው ነገር መረጃ ያገኝ የነበረው ከሚያስተውላቸው ነገሮች፣ ከአፈ ታሪኮችና ሌሎች ከሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ብቻ ነበር። ሄሮዶተስ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዟል። ያደገው የግሪክ ቅኝ ግዛት በሆነችው በኸሊከርኔሰስ (በደቡባዊ ቱርክ የምትገኘው የአሁኗ ቦድሩም) ሲሆን አብዛኛውን የግሪክ ክፍልም አዳርሷል።

ሄሮዶተስ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዟል

በስተ ሰሜን ወደ ጥቁር ባሕርና በአሁኗ ዩክሬን ወደምትገኘው ወደ ሲቲያ፣ በስተ ደቡብ ደግሞ ወደ ፍልስጤምና ወደ ላይኛው ግብፅ በድፍረት ተጉዟል። በስተ ምሥራቅ በኩል እስከ ባቢሎን ድረስ እንደሄደ የሚገመት ሲሆን ቀሪውን ሕይወቱን ያሳለፈው በስተ ምዕራብ በምትገኘው የግሪክ ቅኝ ግዛት በነበረችው፣ በአሁኗ ጣሊያን ደቡባዊ ክፍል ሳይሆን አይቀርም። በሄደበት ቦታ ሁሉ ሁኔታዎችን በአንክሮ የመመልከትና ሰዎችን የመጠያየቅ ልማድ ነበረው፤ በዚህ መንገድ እምነት ይጣልባቸዋል ብሎ ከሚያስባቸው ሰዎች መረጃ ያሰባስብ ነበር።

የታሪኩ ትክክለኛነት

ዘ ሂስቶሪስ የተባለው ጽሑፍ የፓፒረስ ቁራጭ

ሄሮዶተስ የጻፈው ታሪክ ምን ያህል ትክክለኛ ነው? የጎበኛቸውን ቦታዎችና በገዛ ዓይኑ ያያቸውን ነገሮች በተመለከተ ያሰፈረው መረጃ ትክክለኛ እውቀት እንዳለው ያሳያል። እሱ የገለጻቸው አንዳንድ ልማዶች በግሪክ የማይታወቁ ነበሩ፤ ለምሳሌ በሲቲያ፣ ነገሥታት እንዴት ይቀበሩ እንደነበር ወይም በግብፅ አስከሬን እንዴት ያደርቁ እንደነበር የጻፈው ሐሳብ ከአርኪኦሎጂ ግኝቶች ጋር ይስማማል። በግብፅ ዙሪያ ያጠናቀረው መጠነ ሰፊ መረጃ “በጥንት ዘመን ስለዚህች አገር ከተጻፈው ጽሑፍ ሁሉ እጅግ የላቀ ጠቀሜታ አለው” ተብሎ ተነግሮለታል።

ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ሄሮዶተስ አማራጭ ስላልነበረው አስተማማኝነታቸው አጠራጣሪ የሆኑ መረጃዎችንም ለመጠቀም ተገዷል። በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩ ሰዎች፣ አረማውያን አማልክት በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያምኑ ነበር። በመሆኑም ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል የዘመናችን የታሪክ ምሁራን ያወጧቸውን መሥፈርቶች የሚያሟሉት ሁሉም አይደሉም። ያም ሆነ ይህ ሄሮዶተስ እውነታውን ከአፈ ታሪክ ለመለየት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። የተነገረውን ነገር ሁሉ አምኖ ከመቀበል ይቆጠብ እንደነበር ተናግሯል። መደምደሚያ ላይ የሚደርሰው ማስረጃዎቹን በደንብ ካጣራና ካወዳደረ በኋላ ነበር።

ዘ ሂስቶሪስ የተባለው ጽሑፉ የሄሮዶተስ የሕይወት ዘመን ሥራው ሊባል ይችላል። ሄሮዶተስ ሊያገኛቸው ከሚችላቸው መረጃዎች አንጻር ሲታይ ሥራው እጅግ የተዋጣለት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።