ከዓለም አካባቢ
የዜናው ትኩረት—ቤተሰብ
ቤተሰቦች ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ጊዜ የማይሽረው ምክር እነዚህን ችግሮች በተሳካ መንገድ እንዲወጡ ይረዳቸዋል።
አፍሪካ
የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ እናቶች ከወለዱ በኋላ ባለው አንድ ሰዓት ውስጥ ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት መጀመር ያለባቸው ሲሆን ልጆቹ ስድስት ወር እስኪሞላቸው ድረስ ጡት ብቻ ሊጠቡ ይገባል። ይህ ምክር ጠቃሚ ቢሆንም “በእናት ጡት ምትክ የሚሰጡ የሕፃናት ምግቦች የእናት ጡትን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ” የሚገልጹ የሐሰት ማስታወቂያዎች አሁንም እንደሚቀርቡ በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ አገራት የዩኒሴፍ የሥነ ምግብ አማካሪ ተናግረዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15
ካናዳ
በሞንትሪያል የሚገኙ ተመራማሪዎች እንደገለጹት ከሆነ በፍቅርና በሥርዓት የሚያሳድጉ ወላጆች ካሏቸው ልጆች ይልቅ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ (ድርቅ ያሉ ሕጎችን የሚያወጡና ለልጆቻቸው እምብዛም ፍቅር የማያሳዩ) ወላጆች ያሏቸው ልጆች ከመጠን በላይ የመወፈር አጋጣሚያቸው 30 በመቶ ያህል ከፍ ያለ ነው።
ይህን ያውቁ ኖሯል? ልጆችን በተሻለ መንገድ ለማሳደግ የሚረዳ ጠቃሚ መመሪያ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል።—ቆላስይስ 3:21
ኔዘርላንድስ
በሥራው ዓለም ላይ በተሰማሩ ባልና ሚስቶች ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር፤ ጥናቱ እንዳሳየው ሥራቸውንና የቤተሰብ ኃላፊነታቸውን በአንድነት ለማከናወን ከሚጥሩ ወላጆች ይልቅ እነዚህን ኃላፊነቶቻቸውን በተናጠል የሚወጡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የተሻለ ግንኙነት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ከሥራ ሰዓት በኋላ ከሥራ ጋር የተያያዙ የስልክ ጥሪዎችን በማስተናገድ ሥራንና የቤተሰብን ኃላፊነት በአንድነት ለመወጣት የሚሞክሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን ትኩረት መስጠት አዳጋች ይሆንባቸዋል።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1