በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልብን አዘጋጅቶ ይሖዋን መፈለግ

ልብን አዘጋጅቶ ይሖዋን መፈለግ

ልብን አዘጋጅቶ ይሖዋን መፈለግ

እስራኤላዊው ካህን ዕዝራ የታወቀ ምሁር፣  ጸሐፊ፣ የሕጉ አስተማሪና ጥልቅ ምርምር የሚያደርግ ሰው ነበር። በተጨማሪም በሙሉ ነፍስ በሚቀርብ አገልግሎት ረገድ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። እንዴት? በሐሰት አማልክትና በአጋንንት አምልኮ ተሞልታ በነበረችው በባቢሎን በሚኖርበት ጊዜም ለአምላክ ያደረ ሆኖ በመቀጠሉ ነው።

ዕዝራ ያሳየው ለአምላክ የማደር ባሕርይ እንዲሁ በአጋጣሚ ያገኘው ነገር አይደለም። ይህን ባሕርይ ለማዳበር ጥሯል። አዎን፣ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ እንደነበር ’ ይነግረናል።​—⁠ዕዝራ 7:​10

እንደ ዕዝራ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ለእውነተኛው አምልኮ ጥላቻ ባለው ዓለም ውስጥ እየኖሩም ይሖዋ የሚጠብቅባቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ይፈልጋሉ። በመሆኑም እኛም ‘የይሖዋን ሕግ ለመፈለግና ለማድረግ’ ልባችንን ማለትም አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንን፣ ምኞታችንንና ግፊታችንን ጨምሮ ውስጣዊ ማንነታችንን ማዘጋጀት የምንችልባቸውን መንገዶች እስቲ እንመርምር።

ልባችንን ማዘጋጀት

“ማዘጋጀት” የሚለው ቃል “ለአንድ ለሆነ ዓላማ አሰናድቶ ማስቀመጥ ማለትም አንድ ዓይነት ጥቅም ወይም አገልግሎት ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸት” የሚል ፍቺ አለው። እርግጥ የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት ካገኘህና ሕይወትህን ለይሖዋ ከወሰንክ ልብህ በተዘጋጀ ሁኔታ እንደሚገኝ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ ከጠቀሰው “መልካም መሬት [“አፈር፣” NW ]” ጋር ሊመሳሰል ይችላል።​—⁠ማቴዎስ 13:​18-23

ያም ሆኖ ግን ልባችን የማያቋርጥ ትኩረትና ክትትል ያሻዋል። ለምን? በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው። አንደኛው ምክንያት ጎጂ የሆኑ ዝንባሌዎች በአትክልት መካከል እንደሚበቅል አረም በቀላሉ ልባችን ውስጥ ሥር ሊሰዱ ስለሚችሉ ነው። በተለይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሥጋዊ አስተሳሰብ በተጠናወተው የሰይጣን ሥርዓት “አየር” ተከበን ባለንበት በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ይህ ነገር እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ኤፌሶን 2:​2) ሁለተኛው ምክንያት በቀጥታ አፈሩን ይመለከታል። አፈር ዝም ብሎ ከተተወ ብዙም ሳይቆይ ደርቆና ደድሮ የማያፈራ ሊሆን ይችላል። ወይም ብዙ ሰዎች በግዴለሽነት በእርሻው ላይ የሚሄዱና የሚረመርሙት ከሆነ መሬቱ ሊጠጥር ይችላል። የምሳሌያዊው ልባችን አፈር ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ችላ ከተባለ ወይም ስለ መንፈሳዊ ደህንነታችን ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች ከረጋገጡት ጭንጫ ሊሆን ይችላል።

ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ሁላችንም “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በተግባር ማዋላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!​—⁠ምሳሌ 4:​23

የልባችንን “አፈር” የሚያዳብሩ ነገሮች

የልባችን “አፈር” ለፍሬ የሚመች እንዲሆን የሚያዳብሩትን አንዳንድ ነገሮች ወይም ባሕርያት እስቲ እንመልከት። እርግጥ የልባችን ሁኔታ እንዲሻሻል የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም እዚህ ላይ ስድስቱን እንመረምራለን። እነዚህም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን መገንዘብ፣ ትሕትና፣ ሐቀኝነት፣ አምላካዊ ፍርሃት፣ እምነትና ፍቅር ናቸው።

ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:​3 NW ) የረሐብ ስሜት መብላት እንዳለብን እንደሚያስታውሰን ሁሉ ለመንፈሳዊ ፍላጎታችን ንቁ መሆናችንም መንፈሳዊ ምግብ እንድንራብ ያደርገናል። ሕይወታቸው ትርጉምና ዓላማ ያለው እንዲሆን ስለሚያደርግ ሰዎች በተፈጥሯቸው ለእንዲህ ዓይነቱ ምግብ ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸው። ከሰይጣን የነገሮች ሥርዓት የሚደርስብን ጫና ወይም ጥናትን በተመለከተ ያለብን ከባድ ስንፍና ለዚህ ፍላጎታችን ንቁዎች እንዳንሆን ሊያደርገን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 4:​4

ቃል በቃል ከወሰድነው ተመጣጣኝና ለጤና የሚስማማ ምግብ አዘውትሮ መመገብ አካላዊ ጤንነት ከማዳበሩም በላይ ሰውነታችን ጊዜው ሲደርስ ቀጥሎ ላለው ምግብ የመብላት ፍላጎት እንዲኖረው ያደርጋል። በመንፈሳዊ ሁኔታም ነገሩ ተመሳሳይ ነው። ምናልባት የማጥናት ፍቅር እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበቡን ልማድ ካደረግከውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘውትረህ የምታጠና ከሆነ የማንበብ ፍላጎትህ እንደሚጨምር ትገነዘባለህ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የምታጠናበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ትጀምራለህ። ስለዚህ በቀላሉ ተስፋ አትቁረጥ፤ ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ የምግብ ፍላጎት ለማዳበር በትጋት ጣር።

ትሕትና ልብን ያለሰልሳል

ትሕትና ለመማር ፈቃደኞች እንድንሆንና ፍቅራዊ ምክርንና እርማትን ሳናንገራግር እንድንቀበል ስለሚረዳን ልብን በማዘጋጀት ረገድ ወሳኝ ነው። ንጉሥ ኢዮስያስ የተወውን ግሩም ምሳሌ ልብ በል። በእሱ የንግሥና ዘመን በሙሴ አማካኝነት የተሰጠውን የአምላክ ሕግ የያዘ አንድ ሰነድ ተገኘ። ኢዮስያስ የሕጉ ቃል ሲነበብ ሰምቶ አባቶቹ ከንጹሕ አምልኮ ምን ያህል እንደራቁ ሲገነዘብ ልብሱን ቀድዶ በይሖዋ ፊት አለቀሰ። የአምላክ ቃል የንጉሡን ልብ ይህን ያህል በጥልቅ የነካው ለምንድን ነው? ዘገባው የይሖዋን ቃል ሲሰማ ራሱን ያዋረደው ልቡ “ገር” ስለነበር መሆኑን ይናገራል። ይሖዋ፣ ኢዮስያስ የነበረውን ትሑትና እሺ ባይ ልብ ተመልክቶ በዚያው መጠን ባርኮታል።​—⁠2 ነገሥት 22:​11, 18-20

ትሕትና “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “እንደ ሰው ጥበብ” ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የሆኑ ሰዎች ያልተገነዘቡትን መንፈሳዊ እውነት እንዲረዱና በሥራ እንዲያውሉ አስችሏቸዋል። (ሥራ 4:​13፤ ሉቃስ 10:​21፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​26) ሌሎቹ ግን ልባቸው በኩራት ደንድኖ ስለነበር የይሖዋን ቃል ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም። ታዲያ ይሖዋ ኩራትን ቢጠላ ምን ያስገርማል?​—⁠ምሳሌ 8:​13፤ ዳንኤል 5:​20

ሐቀኝነትና አምላካዊ ፍርሃት

ነቢዩ ኤርምያስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” ሲል ጽፏል። (ኤርምያስ 17:​9) ይህ የተንኮል ባሕርይ በተለያዩ መንገዶች ይገለጣል። ለምሳሌ ያህል ስህተት ሠርተን ለራሳችን ማመካኛ በምናቀርብበት ጊዜ ይታያል። በተጨማሪም ጉልህ የሆኑ የባሕርይ ድክመቶቻችንን በተመለከተ ሰበብ አስባብ የምንፈልግ ከሆነ ይህ ባሕርይ በግልጽ ይወጣል። ሆኖም ሐቀኝነት መሻሻል እንድንችል ስለ ራሳችን ያለውን እውነታ እንድንጋፈጥ በመርዳት ተንኮለኛ የሆነን ልብ እንድናሸንፍ ይረዳናል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኩላሊቴንና ልቤን ፍተን” ብሎ ሲጸልይ እንዲህ ዓይነቱን ሐቀኝነት አሳይቷል። ምንም እንኳ መዝሙራዊው ደካማ ባሕርያቱን ማሸነፍ እንዲችል እነዚህን አምኖ መቀበል ማለት ቢሆንበትም ይሖዋ እንዲመረምረውና እንዲፈትነው ልቡን አዘጋጅቶ እንደነበር ግልጽ ነው።​—⁠መዝሙር 17:​3፤ 26:​2

‘ክፋትን መጥላት’ የሚጨምረው አምላካዊ ፍርሃት በዚህ የማጥራት ሂደት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። (ምሳሌ 8:​13) ምንም እንኳ አንድ ሰው የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና ጥሩነት ቢያደንቅም ከልቡ ይሖዋን የሚፈራ ሰው ይሖዋ የማይታዘዙ ሰዎችን በሞት እንኳ ሳይቀር የመቅጣት ሥልጣን እንዳለው ፈጽሞ አይዘነጋም። ይሖዋ እስራኤልን በተመለከተ የሚከተለውን ሲናገር እሱን የሚፈሩት ሰዎች እንደሚታዘዙት ጭምር ገልጿል:- “ለእነርሱ ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፣ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!”​—⁠ዘዳግም 5:​29

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላካዊ ፍርሃት ዓላማ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ መገዛት ሳይሆን ሁልጊዜ ለእኛ የሚጠቅመንን ነገር እንደሚያስብ የምናውቀውን አፍቃሪ አባታችንን ለመታዘዝ እንዲያነሳሳን ማድረግ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በሰፊው ያሳየው ይህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት ስሜት የሚያድስ አልፎ ተርፎም ደስታ የሚያስገኝ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 11:​3፤ ሉቃስ 12:​5

የተዘጋጀ ልብ በእምነት የተሞላ ነው

ጠንካራ እምነት ያለው ልብ ይሖዋ የሚጠይቀው ማንኛውም ነገር ወይም በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠው አመራር ምንጊዜም ትክክልና ለእኛ የሚጠቅም እንደሆነ ያውቃል። (ኢሳይያስ 48:​17, 18) እንዲህ ዓይነት ልብ ያለው ሰው “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን የ⁠ምሳሌ 3:​5, 6 ምክር በሥራ በማዋል ጥልቅ ደስታና እርካታ ያገኛል። ሆኖም እምነት የሚጎድለው ልብ፣ በተለይ በመንግሥቱ ጥቅሞች ላይ ለማተኮር ሲባል ኑሮን ቀላል ማድረግን የመሳሰሉ መሥዋዕቶች የሚያካትት ከሆነ በይሖዋ ላይ የመታመን ዝንባሌ ያጣል። (ማቴዎስ 6:​33) ይሖዋ እምነት የለሽ የሆነን ልብ እንደ “ክፉ” መመልከቱ አለምክንያት አይደለም።​—⁠ዕብራውያን 3:​12

በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ቤታችን ሆነን ማንም ሳያየን የምናደርጋቸውን ነገሮች ጨምሮ በብዙ መንገዶች ይንጸባረቃል። ለምሳሌ ያህል ገላትያ 6:​7 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንውሰድ:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።” በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ ያለን እምነት በምንመለከታቸው ፊልሞች፣ በምናነባቸው መጻሕፍት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት መጠን እንዲሁም በጸሎታችን ይንጸባረቃል። አዎን፣ የይሖዋን ቃል ለመቀበልና ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ ልብ ለማግኘት “በመንፈስ” እንድንዘራ የሚያነሳሳን ጠንካራ እምነት ወሳኝ ነው።​—⁠ገላትያ 6:​8

ፍቅር​—⁠ከሁሉ የላቀው ባሕርይ

ከሌሎቹ ባሕርያት ሁሉ ይበልጥ ፍቅር የልባችን አፈር ለይሖዋ ቃል ምላሽ እንዲሰጥ ያደርጋል። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ከእምነትና ከተስፋ ጋር ሲያወዳድረው ፍቅርን “ከእነዚህም የሚበልጠው” ሲል ገልጾታል። (1 ቆሮንቶስ 13:​13) ለአምላክ ባለው ፍቅር የተሞላ ልብ እሱን ከመታዘዝ ከፍተኛ እርካታና ደስታ ያገኛል እንጂ አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች አይበሳጭም። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:​3) በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል።” (ዮሐንስ 14:​23) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ባጸፋው ምላሽ እንደሚያገኝ ልብ በል። አዎን፣ ይሖዋ በፍቅር ተስበው ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች በጥልቅ ይወዳቸዋል።

ይሖዋ ፍጹማን አለመሆናችንንና ዘወትር በእሱ ላይ ኃጢአት እንደምንሠራ ያውቃል። እንደዚያም ሆኖ እንኳ ራሱን ከእኛ አያርቅም። ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚፈልገው ‘በነፍሳችን ፈቃድ’ እንድናገለግለው የሚያነሳሳ “ፍጹም ልብ” እንዲኖረን ነው። (1 ዜና መዋዕል 28:​9) እርግጥ ነው በልባችን ውስጥ ጥሩ ባሕርያትን መኮትኮትና የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅብን ያውቃል። (ገላትያ 5:​22, 23) በመሆኑም ‘ፍጥረታችንን ስለሚያውቅና፤ አፈር እንደ ሆንን ስለሚያስብ’ ይታገሠናል። (መዝሙር 103:​14) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስህተት ሲሰሩ ክፉኛ ወቅሷቸው አያውቅም። ከዚህ ይልቅ በትዕግሥት ረድቷቸዋል እንዲሁም አበረታቷቸዋል። በዚህም ተመሳሳይ ባሕርይ አንጸባርቋል። ይሖዋና ኢየሱስ ያሳዩን ይህ ዓይነቱ ፍቅር፣ ምሕረትና ትዕግሥት ከበፊቱ የበለጠ እንድትወድዳቸው አያነሳሳህምን?​—⁠ሉቃስ 7:​47፤ 2 ጴጥሮስ 3:​9

አንዳንድ ጊዜ ሥር የሰደደ አረም መሰል ልማድን መንቀል ወይም እንደ ዓለት የጠጠረ ባሕርይን ማስወገድ የሚያታግል ሆኖ ካገኘኸው አትዘን ወይም ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ መንፈሱን ለማግኘት ለይሖዋ በተደጋጋሚ ምልጃ ማቅረብን ጨምሮ ‘በጸሎት በመጽናት’ መሻሻል ማድረግህን ቀጥል። (ሮሜ 12:​12) እሱ በፈቃደኝነት በሚሰጥህ እርዳታ እንደ ዕዝራ ‘የይሖዋን ሕግ ለማድረግና ለመፈለግ’ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ የሆነ ልብ በማግኘት ረገድ ይሳካልሃል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዕዝራ በባቢሎን እያለም እንኳ ለአምላክ ያደረ ሆኖ ቀጥሏል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Garo Nalbandian