አምላክ ለጸሎት መልስ ይሰጣል
አምላክ ለጸሎት መልስ ይሰጣል
ቆርኔሌዎስ በተደጋጋሚ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የጣረ ሰው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የጦር መኮንን በመሆን የነበረውን ሥልጣን በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞበታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ለችግረኞች ‘እጅግ ምጽዋት አድርጓል።’—ሥራ 10:1, 2
በዚያን ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ የተዋቀረው አማኝ በሆኑ አይሁዶች፣ ወደ ይሁዲነት በተለወጡ ሰዎችና በሳምራውያን ነበር። ቆርኔሌዎስ ያልተገረዘ አሕዛብ ከመሆኑም በላይ የክርስቲያን ጉባኤ አባል አልነበረም። ይህ ማለት ታዲያ ጸሎቱ እንዲያው ከንቱ ነበር ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋ አምላክ ቆርኔሌዎስንና የቆርኔሌዎስን በጸሎት የተደገፈ ተግባር ተመልክቷል።—ሥራ 10:4
በመላእክታዊ አመራር አማካኝነት ቆርኔሌዎስ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል። (ሥራ 10:30-33) ከዚህ የተነሳ እርሱና ቤተሰቡ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተቀባይነት ያገኙ የመጀመሪያዎቹ ያልተገረዙ አሕዛብ የመሆን መብት አግኝተዋል። ይሖዋ አምላክ የቆርኔሌዎስ የግል ተሞክሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ማድረጉን ተገቢ ሆኖ አግኝቶታል። ሕይወቱን ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ለማስማማት ብዙ ለውጦች አድርጎ እንደሚሆን አያጠራጥርም። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 17:16) ዛሬ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ለሚፈልጉ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የቆርኔሌዎስ ተሞክሮ ከፍተኛ ማበረታቻ ሊሆናቸው ይገባል። አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።
ዘመናዊ ምሳሌዎች
በሕንድ የምትኖር አንዲት ወጣት ሴት ከፍተኛ ማጽናኛ ያስፈልጋት ነበር። በ21 ዓመቷ አግብታ ሁለት ልጆች ወልዳለች። ሆኖም ሁለተኛ ልጅዋ ከተወለደች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቷ ሞተ። ድንገት በ24 ዓመቷ የ2 ወር ሴት ልጅና የ22 ወር ወንድ ልጅ ያላት መበለት ሆነች። ማጽናኛ መፈለጓ ምንም አያስገርምም! ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ማን ዘወር ልትል ትችላለች? አንድ ቀን ማታ በጭንቀት ተውጣ እያለ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ እባክህ በቃልህ አማካኝነት አጽናናኝ” ስትል ጸለየች።
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት አንድ ሰው ሊጠይቃት መጣ። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር ነበር። የዚያን ዕለት ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል በራቸውን የከፈቱለት ሰዎች ጥቂት ስለነበሩ አገልግሎቱ አስቸጋሪ ነበር። ደክሞትና ተስፋ ቆርጦ ወደ ቤቱ ሊመለስ ካለ በኋላ በሆነ መንገድ አንድ ተጨማሪ ቤት የማንኳኳት ግፊት አደረበት። ከወጣቷ መበለት ጋር የተገናኘው ይህን ቤት ሲያንኳኳ ነበር። ወደ ቤት እንዲገባ የጋበዘችው ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራራ ጽሑፍ
ለመውሰድም ፈቃደኛ ሆነች። ይህች ሴት ጽሑፉን በማንበብና ከይሖዋ ምሥክሩ ጋር በመወያየት ከፍተኛ ማጽናኛ አገኘች። አምላክ ሙታንን ለማስነሳት ቃል መግባቱንና የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ አወቀች። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለጸሎቷ መልስ የሰጣትን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማወቅና ማፍቀር ቻለች።በደቡብ አፍሪካ ጆርጅ ከተማ የምትኖረው ኖራ በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ የምትሳተፍበት ወር መደበች። አገልግሎቷን ከመጀመሯ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ልባዊ ፍላጎት ያለው ሰው ማግኘት እንድትችል ይሖዋ እንዲረዳት ከልቧ ጸለየች። እንድትሸፍነው የተመደበላት የአገልግሎት ክልል ከዚህ በፊት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ክፉኛ ያመናጨቃት ሰው የሚኖርበትን ቤት ያጠቃልላል። ኖራ በድፍረት ይህን ቤት እንደገና አንኳኳች። በጣም የሚያስገርመው ቤቱን ኖሊን የምትባል አዲስ ተከራይ ገብታበት አገኘች። ከዚህ በተጨማሪ ኖሊን እና እናቷ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ አምላክ እንዲረዳቸው ሲጸልዩ ነበር። “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ሐሳብ ሳቀርብላቸው በጣም ተደሰቱ” በማለት ኖራ ተናግራለች። ኖሊንና እናቷ ፈጣን እድገት አደረጉ። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ከኖራ ጋር በመንፈሳዊ የፈውስ ሥራ መሳተፍ ጀመሩ።
የደቡብ አፍሪካ ከተማ በሆነችው በጆሀንስበርግ የሚኖሩ የአንድ ባልና ሚስት ሁኔታም የጸሎትን ኃይል የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። በ1996 አንድ ቅዳሜ ምሽት ላይ የዴኒስና የካሮል ትዳር ሊፈርስ ተቃርቦ ነበር። የመጨረሻ ሙከራ አድርገው በመውሰድ በጸሎት እርዳታ ለማግኘት ሌሊቱን ደጋግመው ጸለዩ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት 5 ሰዓት ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በራቸውን አንኳኩ። ዴኒስ በሩን ከፈተና ሚስቱን ጠርቶ እስኪመለስ ድረስ እንዲጠብቁት ነገራቸው። ከዚያም ምሥክሮቹን እንዲገቡ ከጋበዘቻቸው ከእነርሱ መላቀቅ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አስጠነቀቃት። እርዳታ ለማግኘት ሲጸልዩ እንደነበረና ይህ አምላክ ለጸሎታቸው የሰጠው መልስ ሊሆን እንደሚችል አስታወሰችው። ስለዚህ ምሥክሮቹ ወደ ቤት እንዲገቡ ተጋበዙና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ዴኒስና ካሮል በተማሩት ነገር በጣም ተደሰቱ። የዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ ተገኙ። ዴኒስና ካሮል ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን እውቀት በሥራ በማዋል በትዳራቸው ውስጥ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አገኙ። በአሁኑ ጊዜ የተጠመቁ የይሖዋ አወዳሾች ሲሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታቸውንም አዘውትረው ለጎረቤቶቻቸው ያካፍላሉ።
ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆንክ ቢሰማህስ?
አንዳንድ ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች በሚከተሉት መጥፎ አኗኗር የተነሳ ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸው ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት ስሜት ስለነበረው ስለ አንድ የተናቀ ቀረጥ ሰብሳቢ ተናግሯል። ይህ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ከገባ በኋላ ጸሎት ወደሚቀርብበት የተለመደ ቦታ ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆነ ተሰማው። “በሩቅ ቆሞ . . . አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” (ሉቃስ 18:13) ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ይህ ሰው ጥሩ ተደማጭነት አግኝቷል። ይህ ታሪክ ይሖዋ አምላክ በእርግጥ መሐሪ እንደሆነና ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን የመርዳት ፍላጎት እንዳለው ያረጋግጣል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖረውን ፖል የሚባል የአንድ ወጣት ሁኔታ ተመልከት። ፖል ልጅ በነበረበት ጊዜ ከእናቱ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ሆኖም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረባቸው ዓመታት የአምላክን መንገድ ከማይከተሉ ወጣቶች ጋር መግጠም ጀመረ። ትምህርቱን
ካጠናቀቀ በኋላ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግሥት ጦር ሠራዊት ውስጥ አገለገለ። ከዚያም ሴት ጓደኛው ከእርሱ ጋር የነበራትን ግንኙነት በድንገት አቋረጠች። ይህ አርኪ ያልሆነ የሕይወት ጎዳና በፖል ላይ ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት አሳደረበት። “ምንም እንኳ ለዓመታት ከልቤ ወደ አምላክ በጸሎት ቀርቤ ባላውቅም አንድ ቀን ማታ ግን ይሖዋ እንዲረዳኝ ጠየቅሁት” ሲል ያስታውሳል።ከጸለየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናቱ በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኝ ጋበዘችው። (ሉቃስ 22:19) ፖል መረን የለቀቀ አኗኗር ስለነበረውና ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ፍላጎት ስላልነበረው እናቱ በበዓሉ እንዲገኝ መጋበዟ እንግዳ ነገር ሆነበት። “ይህ ግብዣ ይሖዋ ለጸሎቴ የሰጠኝ መልስ እንደሆነ በመቁጠር ውለታ መመለስ እንዳለብኝ ተሰማኝ።” ከዚህ ጊዜ አንስቶ ፖል በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ለአራት ወራት መጽሐፍ ቅዱስ ካጠና በኋላ ለመጠመቅ ብቁ ሆነ። ከዚህ በተጨማሪ የምኅንድስና ትምህርቱን አቋርጦ በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ መካፈልን ሙያው ለማድረግ መረጠ። ዛሬ ፖል ስለቀድሞ ሕይወቱ መጨነቁን ትቶ ደስተኛ ሆኗል። ላለፉት 11 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ሲያገለግል ቆይቷል።
በእርግጥም ይሖዋ አምላክ በደግነት ለጸሎት መልስ ይሰጣል፤ ‘ለሚፈልጉትም ዋጋቸውን ይሰጣል።’ (ዕብራውያን 11:6) በቅርቡ የይሖዋ ታላቅ ቀን ይመጣና ክፋትን ሁሉ ጥርግርግ አድርጎ ያስወግዳል። እስከዚያ ድረስ ይሖዋ ሕዝቦቹ ወሳኝ በሆነው የምሥክርነቱ ሥራ በቅንዓት ሲካፈሉ ብርታትና አመራር ለማግኘት ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ እየሰጠ ነው። በመሆኑም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እየመጡ ሲሆን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘትም እየተባረኩ ነው።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቆርኔሌዎስ ያቀረበው ልባዊ ጸሎት ሐዋርያው ጴጥሮስ መጥቶ እንዲያነጋግረው መንገድ ከፍቷል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአስቸጋሪ ጊዜያት ሥር ጸሎት ብዙዎችን ረድቷል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ጠቃሚ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባልና ሚስቶች ትዳራቸው እንዲጠናከር እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ይችላሉ