“ይሖዋንና እርሱ የሚሰጠውን ብርታት ፈልጉ”
“ይሖዋንና እርሱ የሚሰጠውን ብርታት ፈልጉ”
“እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና [“ያበረታ፣” NW ] ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና።”—2 ዜና መዋዕል 16:9
1. ኃይል [ወይም ፓወር ] ምንድን ነው? ሰዎችስ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?
ኃይል ተብሎ የተተረጎመው ፓወር የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መቆጣጠር፣ ሥልጣን መጨበጥ ወይም በሌሎች ላይ መሠልጠን፣ አንድን ነገር የማከናወን ወይም ውጤት የማስገኘት ችሎታ፣ የአካል ጥንካሬ (ብርታት)፣ አለዚያም የአእምሮ ወይም የሞራል ጥንካሬና የመሳሰሉትን ማለት ሊሆን ይችላል። የሰው ልጅ በኃይል አጠቃቀም ረገድ ያስመዘገበው ታሪክ የጎደፈ ነው። ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ሎርድ አክተን በፖለቲከኞች እጅ ስላለ ሥልጣን ሲናገሩ “ሥልጣን ያባልጋል፤ ገደብ የሌለው ሥልጣን ከሆነ ደግሞ ብልግናውም እንደዚያው ገደብ አይኖረውም” ብለዋል። የኋለኛው የሰው ልጅ ታሪክ የሎርድ አክተንን ቃላት እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ናቸው። ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ እንደሆነ’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በ20ኛው መቶ ዘመን በግልጽ ታይቷል። (መክብብ 8:9) ብልሹ የሆኑ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ሥልጣናቸውን ፍጹም አግባብ በሌለው መንገድ በመጠቀም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። በፍቅር፣ በጥበብና በፍትሕ ያልተገራ ኃይል አደገኛ ነው።
2. ይሖዋ ኃይሉን በሚጠቀምበት መንገድ ላይ ሌሎቹ መለኮታዊ ባሕርያት ተጽዕኖ የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ አብራራ።
2 አምላክ ብዙ ሰዎች ከሚያደርጉት በተለየ መንገድ ኃይሉን የሚጠቀመው ለበጎ ተግባር ብቻ ነው። “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና [“ያበረታ፣” NW ] ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት በገደብ ነው። ክፉዎች ንስሐ መግባት የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኙ ዘንድ ትዕግሥት እርምጃ ከመውሰድ እንዲታቀብ ያደርገዋል። ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ማለትም ለጻድቃንም ሆነ ለዓመፀኞች ፀሐይን እንዲያወጣ የሚገፋፋው ፍቅር ነው። በመጨረሻም ለሞት ምክንያት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ከሕልውና ውጭ ለማድረግ ገደብ የሌለው ኃይሉን እንዲጠቀም የሚያነሳሳው ፍትሕ ነው።—ማቴዎስ 5:44, 45፤ ዕብራውያን 2:14፤ 2 ጴጥሮስ 3:9
3. አምላክ ሁሉን ቻይ መሆኑ በእርሱ እንድንታመን ምክንያት የሚሆነን ለምንድን ነው?
3 የሰማዩ አባታችን ያለው አስፈሪ ኃይል ቃል በገባቸው ተስፋዎችና በሚሰጠው ጥበቃ ላይ ለመተማመን የሚያስችል ምክንያት ይሆናል። አንድ ትንሽ ልጅ በማያውቃቸው ሰዎች መሃል በሚሆንበት ጊዜ የአባቱን እጅ ሙጭጭ አድርጎ ከያዘ አባቱ ከክፉ ነገር እንደሚያስጥለው ስለሚያውቅ የመተማመን ስሜት ይኖረዋል። በተመሳሳይም ‘ለማዳን የሚበረታው’ የሰማዩ አባታችን አካሄዳችንን ከእርሱ ጋር ካደረግን ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብን ይጠብቀናል። (ኢሳይያስ 63:1፤ ሚክያስ 6:8) ደግሞም ይሖዋ እንደ አንድ ጥሩ አባት የገባውን ቃል ሁልጊዜ ይፈጽማል። ገደብ የሌለው ኃይሉ ‘የተናገረው ቃል ፍጻሜውን እንደሚያገኝ’ ዋስትና ይሆነናል።—ኢሳይያስ 55:11፤ ቲቶ 1:2
4, 5. (ሀ) ንጉሥ አሳ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ በታመነ ጊዜ ምን ውጤት አገኘ? (ለ) ለችግሮቻችን በሰብዓዊ መፍትሔ ብንታመን ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?
4 የሰማዩ አባታችን ጥበቃ እንደሚያደርግልን ላፍታ እንኳ አለመዘንጋታችን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በገጠሙን ሁኔታዎች ተውጠን ደህንነታችን የተመካው በማን ላይ መሆኑን በቀላሉ ልንዘነጋ ስለምንችል ነው። በጥቅሉ ሲታይ በይሖዋ ይታመን የነበረው የንጉሥ አሳ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆነናል። በአሳ ዘመን አንድ ሚልዮን ብርቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት ይሁዳን ከብቦ ነበር። አሳ ጠላቶቹ ወታደራዊ የበላይነት እንደነበራቸው በመገንዘብ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አቤቱ፣ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፣ በአንተ ታምነናልና፣ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ።” (2 ዜና መዋዕል 14:11) ይሖዋም የአሳን ጥያቄ በመቀበል ወሳኝ የሆነ ድል እንዲቀዳጅ ረዳው።
5 ይሁን እንጂ አሳ ለብዙ ዓመታት የታመነ ሆኖ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ የነበረው ትምክህት ተዳከመ። ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ከሚሰነዝረው ወታደራዊ ጥቃት ለማምለጥ ከሶርያ እርዳታ ጠይቋል። (2 ዜና መዋዕል 16:1-3) ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር የሰጠው ጉቦ በላዩ አጥልቶበት ከነበረው ከእስራኤል መንግሥት ጥቃት ቢያድነውም አሳ ከሶርያውያን ጋር ቃል ኪዳን መግባቱ በይሖዋ ላይ ትምክህት እንደሌለው የሚያሳይ ነበር። በዚህ ጊዜ ነቢዩ አናኒ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቦለታል:- “ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው።” (2 ዜና መዋዕል 16:7, 8) ሆኖም አሳ ይህንን ወቀሳ አልተቀበለም። (2 ዜና መዋዕል 16:9-12) እኛም ችግሮች በሚገጥሙን ጊዜ በሰብዓዊ መፍትሔዎች ላይ አንታመን። ሰዎች ባላቸው ኃይል ላይ መታመን ትርፉ ቁጭትና ብስጭት ስለሆነ በአምላክ ላይ ትምክህት እንዳለን እናሳይ።—መዝሙር 146:3-5
ይሖዋ የሚሰጠውን ኃይል ለማግኘት ጣሩ
6. ‘ይሖዋንና እርሱ የሚሰጠውን ብርታት’ መፈለግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል መስጠትም ሆነ እነርሱን መጠበቅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋንና እርሱ የሚሰጠውን ብርታት ፈልጉ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (መዝሙር 105:4 NW ) ለምን? ምክንያቱም ነገሮችን የምናከናውነው ከአምላክ በምናገኘው ብርታት ከሆነ ኃይላችንን ሌሎችን ለመጥቀም እንጂ ለመጉዳት ብለን አንጠቀምበትም። በዚህ ረገድ ‘በይሖዋ ኃይል’ ብዙ ተዓምራትን ካከናወነው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለ ሌላ ምሳሌ አናገኝም። (ሉቃስ 5:17) ኢየሱስ ሃብታም፣ ታዋቂ ወይም ከሁሉ የላቀ ኃያል ንጉሥ መሆን ይችል ነበር። (ሉቃስ 4:5-7) ይልቁንም አምላክ የሰጠውን ኃይል ሰዎችን ለማሰልጠን፣ ለማስተማር፣ ለመርዳትና ለመፈወስ ተጠቅሞበታል። (ማርቆስ 7:37፤ ዮሐንስ 7:46) ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
7. ነገሮችን በራሳችን ሳይሆን አምላክ በሚሰጠን ብርታት ማከናወናችን ምን በጣም ወሳኝ የሆነ ባሕርይ እንድናዳብር ይረዳናል?
7 ከዚህም በላይ የምንሠራውን ነገር ‘አምላክ በሚሰጠን ብርታት’ ማከናወናችን በትህትና እንድንመላለስ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 4:11) ለራሳቸው ኃይል ለማግኘት የሚጣጣሩ ሰዎች ትዕቢተኞች ይሆናሉ። “እኔ ኃያል ነኝ፣ ኃያል ነኝ፣ ጀግና ነኝ፣ በጣም ትልቅና ግዙፍ ነኝ” ሲል በጉራ የተናገረው የአሦራውያኑ ንጉሥ አስራዶን ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ከዚያ በተቃራኒው ግን ይሖዋ ‘ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር የዓለምን ደካማ ነገር መርጧል።’ በመሆኑም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ያከናወነው ነገር ሁሉ በራሱ ብርታት የተከናወነ እንዳልሆነ ስለሚገነዘብ ቢመካም የሚመካው በይሖዋ ነው። ‘ከኃይለኛው ከይሖዋ እጅ በታች ራሳቸውን ያዋረዱ’ ከፍ ከፍ ይላሉ።—1 ቆሮንቶስ 1:26-31፤ 1 ጴጥሮስ 5:6
8. ይሖዋ የሚሰጠውን ኃይል ለማግኘት በመጀመሪያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
8 ከአምላክ ብርታት የምናገኘው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በጸሎት መጠየቅ ይገባናል። ኢየሱስ አባቱ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። (ሉቃስ 11:10-13) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ መመሥከራቸውን እንዲያቆሙ ካዘዟቸው የሃይማኖት መሪዎች ይልቅ አምላክን ለመታዘዝ በመረጡ ጊዜ ይህ እንዴት ኃይል እንደሰጣቸው ልብ በል። የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡት ልባዊ ጸሎት መልስ ስላገኘ ምሥራቹን በፍጹም ግልጽነት እንዲናገሩ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል።—ሥራ 4:19, 20, 29-31, 33
9. መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት የሚረዳን ሁለተኛው ነገር ምን እንደሆነ ተናገር፤ እንዲሁም ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ጥቀስ።
9 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ብርታት ልናገኝ እንችላለን። (ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን በግልጽ ታይቷል። ይህ አይሁዳዊ ንጉሥ ቀደም ብሎም ቢሆን የጣዖት አምልኮ ምስሎችን ከምድሪቱ አስወግዶ የነበረ ቢሆንም ባልታሰበ አጋጣሚ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የይሖዋ ሕግ መገኘቱ ይህን የማጽዳት ዘመቻ እንዲያጧጡፍ አነሳስቶታል። a ኢዮስያስ ራሱ የሕጉን ቃል ለሕዝቡ ካነበበ በኋላ መላው ብሔር ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ከዚያም በጣዖት አምልኮ ላይ ይበልጥ የተጠናከረ ሁለተኛ ዘመቻ ተደረገ። ኢዮስያስ ያካሄደው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ‘በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ከመከተል እንዳይርቁ’ በማድረግ መልካም ውጤት አስገኝቷል።—2 ዜና መዋዕል 34:33
10. ከይሖዋ ብርታት ለማግኘት የሚያስችለው ሦስተኛው መንገድ ምንድን ነው? በጣም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
10 ከይሖዋ ብርታት የምናገኝበት ሦስተኛው መንገድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ናቸው። ጳውሎስ ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ይነቃቁና’ እርስ በርሳቸው ይበረታቱ ዘንድ አዘውትረው እንዲሰበሰቡ ክርስቲያኖችን አበረታቷል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ጴጥሮስ በተአምራዊ ሁኔታ ከእስር ቤት በተፈታ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር መሆን ፈልጎ ስለነበር በቀጥታ የሄደው ወደ ዮሐንስ ማርቆስ እናት ቤት ነበር። በዚያም ‘እጅግ ሰዎች ተከማችተው ሲጸልዩ’ አግኝቷል። (ሥራ 12:12) እርግጥ ሁሉም በየቤታቸው ሆነው መጸለይ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ አንድ ላይ ተሰብስበው መጸለይንና እርስ በርስ መበረታታትን መርጠዋል። ጳውሎስ ረጅምና አደገኛ የነበረውን የሮም ጉዞውን ወደ ማጠናቀቁ ሲቃረብ በፑቲዮሉስ አንዳንድ ወንድሞችን ያገኘ ሲሆን በኋላም እርሱን ብለው የመጡ ሌሎች ወንድሞችን አግኝቷል። ታዲያ ምን ተሰማው? “ጳውሎስም [የኋለኞቹን] ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።” (ሥራ 28:13-15) እንደገና ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር ለመገናኘት በመቻሉ እጅግ ተበረታቷል። እኛም ብንሆን ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር መሰብሰባችን ብርታት ያስገኝልናል። እርስ በርሳችን ለመገናኘት ነፃነቱ እስካለንና እስከቻልን ድረስ ወደ ሕይወት በሚወስደው በቀጭኑ መንገድ ብቻችንን ለመሄድ መሞከር የለብንም።—ምሳሌ 18:1፤ ማቴዎስ 7:14
11. ‘ከወትሮው የተለየ ኃይል’ ይበልጥ የሚያስፈልግባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ጥቀስ።
11 አዘውትረን በመጸለይ፣ የአምላክን ቃል በማጥናትና ከእምነት አጋሮቻችን ጋር በመሰብሰብ ‘በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን’ እንሆናለን። (ኤፌሶን 6:10) ሁላችንም ‘የጌታ ኃይል’ እንደሚያስፈልገን ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶች በሚያሠቃይ ሕመም፣ ሌሎች ደግሞ በዕድሜ መግፋት ወይም የረጅም ዘመን ወዳጃቸውን በሞት በማጣት ይሠቃዩ ይሆናል። (መዝሙር 41:3) ሌሎች ከማያምን የትዳር ጓደኛ የሚደርስባቸውን ተቃውሞ በጽናት ይቋቋማሉ። ወላጆች በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ነጠላ የሆኑት ወላጆች ቀኑን ሙሉ ተቀጥረው እየሠሩ ቤተሰብ ማስተዳደሩን ከባድ ኃላፊነት ሆኖ ያገኙት ይሆናል። ወጣት ክርስቲያኖች የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋምም ሆነ አደገኛ ዕፆችን እንዲወስዱና የጾታ ብልግና እንዲፈጽሙ የሚቀርብላቸውን ግብዣ እምቢ ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ ያስፈልጋቸዋል። ማንኛችንም ብንሆን እንደነዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት እንችል ዘንድ ይሖዋ ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ እንዲሰጠን ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብንም።—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW
‘ለደከሙት ኃይል ይሰጣል’
12. ይሖዋ በክርስቲያናዊው አገልግሎት የሚደግፈን እንዴት ነው?
12 በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቦቹ አገልግሎታቸውን ማከናወን ይችሉ ዘንድ ኃይል ይሰጣቸዋል። በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ እንዲህ እናነባለን:- “ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። . . . እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙምም።” (ኢሳይያስ 40:29-31) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስችል ኃይል አግኝቷል። ከዚህም የተነሣ አገልግሎቱ ውጤታማ ሆኖለታል። በተሰሎንቄ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ . . . እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና” ሲል ጽፎላቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:5) የስብከትና የማስተማር ሥራው የሚያዳምጡትን ሰዎች ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል ነበረው።
13. ኤርምያስ የገጠመውን ተቃውሞ ተቋቁሞ እንዲጸና የረዳው ነገር ምንድን ነው?
13 ብዙም ምላሽ ሳናገኝ ለብዙ ዓመታት በተደጋጋሚ ሠርተንበት ሊሆን በሚችለው የአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ያለው የሰዎች ግዴለሽነት ተስፋ እንድንቆርጥ ይፈታተነን ይሆናል። በተመሳሳይም ኤርምያስ በገጠመው ተቃውሞ፣ ፌዝና ግዴለሽነት ምክንያት የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮበት ነበር። “የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፣ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” ብሎ ለራሱ ቃል ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ ዝም ማለት አልቻለም። መልእክቱ “በአጥንቶ[ቹ] ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት” ሆኖበታል። (ኤርምያስ 20:9) ይህን ያህል ብዙ መከራ ቢደርስበትም ኃይሉን እንዲያድስ የረዳው ነገር ምንድን ነው? ኤርምያስ ራሱ “እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ ጨካኝ ከእኔ ጋር ነው” ብሏል። (ኤርምያስ 20:11) ኤርምያስ የመልእክቱንና አምላክ የሰጠውን ሥራ ክብደት መገንዘቡ ለይሖዋ ማበረታቻ ምላሽ እንዲሰጥ አስችሎታል።
መጉዳትም መፈወስም የሚችል ኃይል
14. (ሀ) አንደበት ምን ያህል ኃይለኛ መሣሪያ ነው? (ለ) አንደበት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
14 ሁሉንም ኃይል በቀጥታ የምናገኘው ከአምላክ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል አንደበት የማቁሰልም ሆነ የመፈወስ ኃይል አለው። ሰሎሞን “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው” ሲል አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 18:21) ሰይጣን ከሔዋን ጋር ያደረገው ውይይት አጭር ቢሆንም ያስከተለውን መዘዝ ስንመለከት ቃላት ምን ያህል ጥፋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እንገነዘባለን። (ዘፍጥረት 3:1-5፤ ያዕቆብ 3:5) እኛም ብንሆን በአንደበታችን ከባድ ጉዳት ልናስከትል እንችላለን። ስለ አንዲት ወጣት ውፍረት የምንሰነዝራቸው ስሜት የሚነኩ ቃላት ልጅቷ የምግብ ጥላቻ እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል። ሳናስብ በተደጋጋሚ የምንሰነዝረው ነቀፋ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ወዳጅነት ሊያበላሽ ይችላል። አዎን፣ ምላሳችን ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል።
15. አንደበታችንን ለማነጽና ለመፈወስ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
15 ይሁን እንጂ አንደበት ሊያንጽም ሊያፈርስም ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።” (ምሳሌ 12:18) ጥበበኛ ክርስቲያኖች የምላሳቸውን ኃይል የተጨነቁትንና ያዘኑትን ለማጽናናት ይጠቀሙበታል። የርኅራኄ ቃላት ጎጂ ከሆነው የእኩዮች ተጽዕኖ ጋር ለሚታገሉ ወጣቶች የብርታት ምንጭ ሊሆንላቸው ይችላል። አንደበታችንን በአሳቢነት ከተጠቀምንበት አረጋዊ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች አሁንም ቢሆን የሚፈለጉና የሚወደዱ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። በደግነት የተነገሩ ቃላት የታመሙ ሰዎች ብሩህ ቀን እንዲያሳልፉ ሊረዳቸው ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አንደበታችንን ኃይለኛ የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት ለሚያዳምጡን ሰዎች ለማካፈል ልንጠቀምበት እንችላለን። ውስጣዊ ፍላጎቱ ካለን የአምላክን ቃል ማወጅ ከአቅማችን በላይ አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” ይላል።—ምሳሌ 3:27
ኃይልን በአግባቡ መጠቀም
16, 17. ሽማግሌዎች፣ ወላጆች፣ ባሎችና ሚስቶች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን ሲጠቀሙ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ይሖዋ ሁሉን ቻይ ቢሆንም ጉባኤውን የሚገዛው በፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም የአምላክን መንጋ የሚንከባከቡት ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ሳይሆን በፍቅር ነው። የበላይ ተመልካቾች አንዳንድ ጊዜ ‘መገሰጽ፣ መውቀስና፣ አጥብቀው ማሳሰብ’ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርጉት ‘በትዕግሥትና የማስተማር ችሎታቸውን’ በመጠቀም ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) በመሆኑም ሽማግሌዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለነበራቸው ወንዶች በጻፋቸው በሚከተሉት ቃላት ላይ ዘወትር ያሰላስላሉ:- “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ።”—1 ጴጥሮስ 5:2, 3፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7, 8
17 ወላጆችና ባሎችም ከይሖዋ ያገኙት ሥልጣን አላቸው። ይህንን ሥልጣናቸውን ሊጠቀሙበት የሚገባው ለመርዳትና ለመንከባከብ ሊሆን ይገባል። (ኤፌሶን 5:22, 28-30፤ 6:4) ሥልጣንን በፍቅራዊ መንገድ በሚገባ መጠቀም እንደሚቻል የኢየሱስ ምሳሌ ያረጋግጣል። ተግሳጽ ሚዛናዊ ከሆነና ተለዋዋጭ ባልሆነ መንገድ ከተሰጠ የልጆች ልብ አይዝልም። (ቆላስይስ 3:21) ክርስቲያን ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን በፍቅር ሲጠቀሙበት እንዲሁም ሚስቶች አምላክ ከሰጣቸው ገደብ ውጭ ሄደው ባሎቻቸውን ለመጫን ወይም እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር ለማስፈጸም ከመሞከር ይልቅ የባላቸውን ራስነት በጥልቅ ሲያከብሩ ትዳራቸው ይጠነክራል።—ኤፌሶን 5:28, 33፤ 1 ጴጥሮስ 3:7
18. (ሀ) ቁጣችንን በመቆጣጠር በኩል የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የሚገባን እንዴት ነው? (ለ) ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በሥራቸው ባሉት ሰዎች ውስጥ ምን ነገር ለመትከል መጣር ይኖርባቸዋል?
18 በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ቁጣቸውን በመቆጣጠር ረገድ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ቁጣ ፍርሃት እንጂ ፍቅር እንዲሰፍን አያደርግም። ነቢዩ ናሆም እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፣ ኃይሉም ታላቅ ነው።” (ናሆም 1:3፤ ቆላስይስ 3:19) ቁጣችንን መቆጣጠር መቻላችን የጥንካሬ ምልክት ነው። በቁጣ መገንፈል ግን ድክመት ነው። (ምሳሌ 16:32) በጉባኤም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ ዓላማችን ለይሖዋ፣ አንዳችን ለሌላውና ለትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚኖረንን ፍቅር መኮትኮት ነው። ፍቅር ከሁሉ ይበልጥ ጠንካራ ማሠሪያና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለመሥራት የሚያንቀሳቅስ ሞተር ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:8, 13፤ ቆላስይስ 3:14
19. ይሖዋ ምን የሚያጽናና ማረጋገጫ ይሰጣል? የእኛስ ምላሽ ምን መሆን ይገባዋል?
19 ይሖዋን ማወቅ ማለት ያለውን ኃይል መገንዘብ ማለት ነው። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል እንደሚከተለው ብሏል:- “አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ የምድር ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፣ አይታክትም።” (ኢሳይያስ 40:28) የይሖዋ ኃይል አይቀንስም። በራሳችን ሳይሆን በእርሱ የምንታመን ከሆነ አይተወንም። እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።” (ኢሳይያስ 41:10) ለዚህ ፍቅራዊ እንክብካቤው የምንሰጠው ምላሽ ምን መሆን ይኖርበታል? ልክ እንደ ኢየሱስ ይሖዋ የሚሰጠንን ማንኛውንም ኃይል ሌሎችን ለመርዳትና ለማነጽ እንጠቀምበት። ምላሳችን የሚያቆስል ሳይሆን የሚፈውስ ይሆን ዘንድ እንቆጣጠረው። እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንኑር፣ በእምነት ጸንተን እንቁም እንዲሁም ታላቁ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ በሚሰጠን ኃይል እየጎለበትን እንሂድ።—1 ቆሮንቶስ 16:13 NW
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አይሁዳውያኑ ያገኙት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በቤተ መቅደሱ እንዲቀመጥ የተደረገውን የሙሴ ሕግ የመጀመሪያ ቅጂ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ልታብራራ ትችላለህን?
• ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?
• ይሖዋ የሚሰጠውን ኃይል ማግኘት የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
• የአንደበታችንን ኃይል እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?
• አምላክ የሚሰጠን ሥልጣን በረከት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከይሖዋ ያገኘውን ኃይል ሌሎችን ለመርዳት ተጠቅሞበታል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውስጣዊ ፍላጎቱ ካለን የአምላክን ቃል ለሌሎች መናገር ከአቅማችን በላይ አይሆንብንም