መጽሐፍ ቅዱስ የምሥጢር ጽሕፈት አለውን?
መጽሐፍ ቅዱስ የምሥጢር ጽሕፈት አለውን?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ይስሐቅ ራቢን በ1995 ከተገደሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ አንድ ጋዜጠኛ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥንቱ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ ስለ ግድያው የሚገልጽ ትንቢት አግኝቶ እንደነበር ገልጿል። ጋዜጠኛው ሚካኤል ድሮዝኒን ጠቅላይ ሚንስትሩ ከመገደላቸው ከአንድ ዓመት በፊት ሊያስጠነቅቃቸው ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ጽፏል።
ሌሎች መጻሕፍትና ለንባብ የበቁ ርዕሶች ደግሞ ይህ የምሥጢር ጽሕፈት መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉን የሚያረጋግጥ የማያጠያይቅ ማስረጃ ነው ሲሉ ዘግበዋል። በእርግጥ እንዲህ ያለ የምሥጢር ጽሕፈት አለ? ደግሞስ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው ብሎ ለማመን የሚያበቃው መሠረት የምሥጢር ጽሕፈት ያለው መሆኑ ነውን?
አዲስ ሐሳብ ነውን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የምሥጢር ጽሕፈት አለ የሚለው ሐሳብ ዛሬ የተፈጠረ ነገር አይደለም። በካባላ ወይም በልማዳዊው የአይሁድ ምሥጢራዊ አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ነገር ነው። እንደ ካባላ አስተማሪዎች አባባል ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በቀጥታ የምንረዳው ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱሱ እውነተኛው ትርጉም አይደለም። በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ሆሄያት በሚገባ ከተረዳናቸው አምላክ አንድ ታላቅ እውነት እንደሚገልጡ ምልክቶች አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል የሚል እምነት አላቸው። በእነርሱ አመለካከት በጽሑፉ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ የዕብራይስጥ ሆሄም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የያዘው ቦታ አምላክ አንድን ዓላማ በአእምሮው በመያዝ የወሰነው ነገር ነው።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምሥጢራዊ ጽሕፈት ምርምር የሚያደርጉት ጄፍሪ ሳቲኖቨር እንዳሉት ከሆነ እነዚህ የአይሁድ ምሥጢራዊ እምነት ተከታዮች የፍጥረትን ዘገባ ለመግለጽ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተሠራባቸው የዕብራይስጥ ሆሄያት አስገራሚ የሆነ ምሥጢራዊ ኃይል እንዳላቸው ያምናሉ። እኒሁ ሰው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአጭሩ የዘፍጥረት መጽሐፍ እንዲሁ መግለጫ ብቻ አይደለም። የፍጥረት ሥራን ለማከናወን ጭምር አገልግሏል። ግዑዝ በሆነ መልክ የተቀመጠ በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያለ ንድፍ ነው።”
ባቺያ ቤን አሸር የተባለው በ13ኛው መቶ ዘመን በሳራጎዛ ስፔይን የነበረው የካባላ ረቢ በየ42 ሆሄ ርቀት ያሉትን ፊደላት እያገጣጠመ የተወሰነውን የዘፍጥረት መጽሐፍ ክፍል በማንበብ ስለተገለጠለት የተሰወረ መልእክት ጽፏል። ዛሬም መጽሐፍ ቅዱስ የምሥጢር ጽሕፈት አለው ለሚለው ጽንሰ
ሐሳብ መሠረት የሆነው ይኸው በተወሰነ ርቀት ያሉ ሆሄያትን እያገጣጠሙ የማንበብ ዘዴ ነው።ኮምፒዩተሮች የምሥጢር ጽሑፉን “ይገልጣሉ”
የሰው ልጅ የኮምፒዩተር ዘመን ላይ ከመድረሱ በፊት የመጽሐፍ ቅዱሱን ክፍሎች በዚህ መልክ የመመርመር ችሎታው ውስን ነበር። ይሁን እንጂ በነሐሴ 1994 ስታትስቲካል ሳይንስ የተባለው መጽሔት ኢየሩሳሌም በሚገኘው የዕብራይስጥ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ኤልያሁ ሪፕስና ሌሎች ተመራማሪዎች የሰነዘሩትን አስገራሚ አስተያየት የያዘ ዘገባ አውጥቶ ነበር። በየሆሄያቱ መካከል ያሉትን ክፍት ቦታዎች በማውጣትና ከዕብራይስጡ የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በተወሰነ ርቀት ላይ ያሉትን ሆሄያት ለቅሞ በማውጣት ታዋቂ የሆኑ የ34 ረቢዎችን ስም በምሥጢር ተጽፎ እንዳገኙ እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን ጨምሮ የተወለዱበትንና የሞቱበትን ዕለት ከስሞቻቸው አቅራቢያ ሰፍሮ እንዳገኙ ገልጸዋል። a ተመራማሪዎቹ ተደጋጋሚ የማረጋገጫ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በምሥጢር ተጽፎ የተገኘው መረጃ ከስታትስቲክስ አንጻር ሲታይ ፈጽሞ የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ሆን ተብሎ በምሥጢር እንዲጻፍ የተደረገ በመንፈስ አነሳሽነት የሰፈረ መረጃ ነው ሲሉ የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ አስፍረዋል።
ይህንኑ ዘዴ በመከተል ጋዜጠኛው ድሮዝኒን በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ አምስት መጻሕፍት ውስጥ የተሰወረ መልእክት ለማግኘት የራሱን ሙከራ አድርጓል። ድሮዝኒን እንዳለው ከሆነ በየ4, 772 ሆሄያት ርቀት ላይ የይስሐቅ ራቢን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ ሰፍሮ አግኝቷል። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጽሑፍ እያንዳንዳቸው 4, 772 ሆሄያት ባላቸው መስመሮች ሲደረደሩ (ከላይ ወደ ታች በማንበብ) የራቢንን ስም ያገኘ ሲሆን ወደ ጎን በሚያቋርጠው መስመር ላይ ደግሞ (ዘዳግም 4:42 ነው የሚያቋርጠው) ድሮዝኒን አንደተረጎመው ከሆነ “የሚገድል ገዳይ” የሚል ንባብ አግኝቷል።
በመሠረቱ ዘዳግም 4:42 የሚናገረው ሳያውቅ የሰው ሕይወት ስላጠፋ ነፍሰ ገዳይ ነው። በመሆኑም ብዙ ሰዎች በዚህ ዓይነት ዘዴ በማንኛውም ጽሑፍ ውስጥ ተመሳሳይ መልእክት ማግኘት እንደሚቻል በመግለጽ ከሳይንሳዊ እውነታ የራቀውን የድሮዝኒን የግል አመለካከት ተችተዋል። ይሁን እንጂ ድሮዝኒን “እኔን የተቹኝን ሰዎች የምቀበላቸው ሞቢ ዲክ በተባለው [ልብ ወለድ] መጽሐፍ ውስጥ ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ የሚገልጽ ጽሑፍ ያገኙ እንደሆነ ነው” ብሎ በመገዳደር ተከራክሯል።
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት ለመጻፉ ማስረጃ ይሆናልን?
በአውስትራሊያው ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒዩተር ክፍል የሚሠሩት ፕሮፌሰር በሬንደን ማኬይ ከድሮዝኒን ግድድር በመነሳት በኮምፒዩተር እገዛ በሞቢ ዲክ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ላይ መጠነ ሰፊ ፍለጋ አካሂደዋል። b ማኬይ እንዳሉት ድሮዝኒን የተጠቀመበትን ዘዴ በመጠቀም ኢንድራ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፣ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ አብረሃም ሊንከን እና ሌሎችም እንደሚገደሉ “የሚተነብዩ” ሐሳቦችን አግኝተዋል። እንደ ማኬይ ገለጻ ሞቢ ዲክ ይስሐቅ ራቢንም እንደሚገደሉ “ተንብዮአል።”
ፕሮፌሰር ማኬይ እና ተባባሪዎቻቸው በዕብራይስጡ የዘፍጥረት ጽሑፍ ረገድም ቢሆን የሪፕስና የተባባሪዎቹ የምርምር ውጤት ትክክል አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል። መረጃዎችን ማገጣጠሙ በተመራማሪዎቹ ግምት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ይህ ነገር ተመራማሪዎቹ የተጠቀሙበት ዘዴና የመረጡት አካሄድ ውጤት ነው እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት የሰፈረ ምሥጢራዊ መልእክት ነው የሚያሰኝ ምንም መሠረት የለውም ሲሉ ተችተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በምሁራኑ መካከል የሚደረገው ክርክር አሁንም ቀጥሏል።
እንዲህ ያሉት በምሥጢር የተቀመጡ መልእክቶች “በመደበኛው” ወይም “በመጀመሪያው” የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረገው በዓላማ ነው የሚለው ሐሳብ ሌላ ጥያቄ ያስነሣል። ሪፕስና የምርምር ጓደኞቹ ይህን ፍለጋ ለማካሄድ የተጠቀሙት “በሰፊው ተቀባይነት ካለው ከተለመደው የዘፍጥረት ጽሑፍ” እንደሆነ ይናገራሉ። ድሮዝኒን “ዛሬ በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚገኙት መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ በፊደል እንኳ ሳይቀር ፍጹም ተመሳሳይ ናቸው” ሲል ጽፏል። ይሁንና ይህ እውነት ነውን? በዛሬው ጊዜ የሚሠራበት “መደበኛው” ቅጂ ሳይሆን የተለያዩ ጥንታዊ ቅጂዎችን መሠረት ያደረጉ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱሱ መልእክት የተለያየ ነው ማለት ባይሆንም ጥንታዊ ቅጂዎቹ ግን ፊደል በፊደል ሲተያዩ አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይደለም።
ዛሬ ያሉት ብዙዎቹ ትርጉሞች ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት በተዘጋጀው የሌኒን ግራድ ኮዴክስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይህ ኮዴክስ ዛሬ ካሉት የተሟሉ የማሶራውያን ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅጂዎች መካከል አንዱ ነው። ይሁንና ሪፕስና ድሮዝኒን የተጠቀሙት ኮረን በመባል የሚታወቀውን ሌላ ቅጂ ነው። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ምሁርና የኦርቶዶክስ
ረቢ የሆኑት ሾሎሞ ስተርንበርግ የሌኒንግራድ ኮዴክስ ‘ድሮዝኒን ከተጠቀመበት ኮረን የሚለይ ሲሆን በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ብቻ 41 የሆሄያት ልዩነቶች እንዳሉ’ ገልጸዋል። የሙት ባሕር ጥቅልሎች ከ2, 000 ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በፊት የተገለበጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የሚያካትቱ ናቸው። በእነዚህ ጥቅልሎች ላይ ያሉት ፊደላት ብዙውን ጊዜ በኋላ ከተዘጋጁት የማሶራውያን ጽሑፎች ይለያያሉ። በወቅቱ አናባቢዎችን የሚጠቁሙ ምልክቶች ገና ስላልተፈለሰፉ አንዳንድ ጥቅልሎች ውስጥ የአናባቢ ድምፆችን ለማመልከት ሲባል ብቻ የተጨመሩ ሆሄያት አሉ። በሌሎች ጥቅልሎች ውስጥ ደግሞ የተሠራባቸው ሆሄያት ጥቂት ናቸው። በእጅ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ቅጂዎች ስናወዳድር የመጽሐፍ ቅዱሱ መልእክት ምንም እንዳልተቀየረ እንገነዘባለን። ይሁንና ሥርዓተ ሆሄያቱም ሆነ የሆሄያቱ ብዛት ከቅጂ ቅጂ እንደሚለያይም ማስተዋል እንችላለን።በምሥጢር ተቀምጧል የሚባለው መልእክት መገኘቱ የተመካው ፍጹም ያልተለወጠ ጽሑፍ በመኖሩ ላይ ነው። አንዷ ፊደል ከተለወጠች መላውን ቅደም ተከተልና አለ የሚባለው መልእክት ይዛባል። አምላክ መልእክቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ሊፈጠር የሚችለውን የፊደል ለውጥ የመሰለ እምብዛም ጠቀሜታ የሌለው ጉዳይ ሥራዬ ብሎ ስለማይከታተል እያንዳንዱ ፊደል ተጠብቆ እንዲቆይ አላደረገም። ታዲያ ይህ ብቻውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰወረ መልእክት እንዳላስቀመጠ ማስረጃ አይሆንምን?—ኢሳይያስ 40:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:24, 25
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምሥጢር ጽሑፍ ያስፈልጋልን?
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል በግልጽ ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ግልጽና ቀጥተኛ መልእክት ለመረዳትም ሆነ ሥራ ላይ ለማዋል ከባድ አይደለም። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ይህን መልእክት ችላ ማለትን መርጠዋል። (ዘዳግም 30:11-14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡት ትንቢቶች መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ለማመን የሚያስችሉ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው። c ከምሥጢራዊ ጽሑፍ በተለየ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሰዎች መላምት የሚገኙ ወይም ‘በሰው ፈቃድ የመጡ’ አይደሉም።—2 ጴጥሮስ 1:19-21
ሐዋርያው ጴጥሮስ “በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:16) መጽሐፍ ቅዱስ የምሥጢር ጽሕፈት አለው የሚለው ሐሳብ የመነጨው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ‘በብልሃት በተፈጠረ’ ዘዴ ከሚሰውረውና ከሚያድበሰብሰው የአይሁዳውያን ምሥጢራዊ እምነት ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ራሳቸው እንዲህ ያለውን ምሥጢራዊ አሠራር በግልጽ ያወግዛሉ።—ዘዳግም 13:1-5፤ 18:9-13
እኛ ግን አምላክን ለማወቅ የሚረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መልእክትና መመሪያ በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን! ይህ ደግሞ የግል ትርጓሜና በኮምፒዩተር የታገዘ ሐሳብ በወለደው የምሥጢር ጽሕፈት አማካኝነት ስለ አምላክ ለመማር ከመሞከር እጅግ የተለየ ነው።—ማቴዎስ 7:24, 25
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዕብራይስጥ ቋንቋ ቁጥሮች በፊደላት ጭምር ሊቀመጡ ይችላሉ። በመሆኑም እነዚህ ዘመናት የተሰሉት በቁጥር ሳይሆን በዕብራይስጥ ሆሄያት ነው።
b ዕብራይስጥ አናባቢ ፊደላት የሌሉት ቋንቋ ነው። አናባቢ ፊደላቱን እንደየአገባባቸው የሚጨምረው አንባቢው ራሱ ነው። አገባቡ ግምት ውስጥ ካልገባ በስተቀር ለቃሉ ሌላ አናባቢ ድምፆች በመጨመር ፈጽሞ የተለየ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። እንግሊዝኛ ግን የተወሰኑ አናባቢ ፊደላት ያሉት መሆኑ እንዲህ ያለውን የቃላት ፍለጋ ይበልጥ አስቸጋሪና የማያፈናፍን ያደርገዋል።
c መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለመሆኑ እንዲሁም በውስጡ ስላሉት ትንቢቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።