ራስህን በሌሎች ፊት ብቁ አድርገህ ታቀርባለህን?
ራስህን በሌሎች ፊት ብቁ አድርገህ ታቀርባለህን?
‘ሰዎች ስለ እኔ የፈለገውን ቢሰማቸው ደንታ የለኝም!’ በሆነ ወቅት በንዴት ወይም በብስጭት እንዲህ ብለህ ተናግረህ ይሆናል። ሆኖም ንዴትህ ሲበርድልህ ሰዎች አንተን በተመለከተ ስለሚሰማቸው ስሜት መጨነቅህ እንደማይቀር የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም አብዛኞቻችን ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት ያሳስበናል።
በእርግጥም ሌሎች እኛን በተመለከተ ስላላቸው ስሜት መጨነቅ ይኖርብናል። በተለይ የተሾምን የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ማለትም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት ያሳስበናል። ደግሞም ‘ለዓለም በቲያትር መድረክ ላይ እንደሚታዩ ተዋንያን’ ነን። (1 ቆሮንቶስ 4:9 NW ) በ2 ቆሮንቶስ 6:3, 4 ላይ የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ጠንካራ ምክር እናገኛለን:- “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን [“ብቁ አድርገን እናቀርባለን፣” NW ]።”
ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን ሲባል ምን ማለት ነው? ጉራችንን እንነዛለን ወይም ወደራሳችንና ወደ ችሎታዎቻችን ትኩረት እንስባለን ማለት ነው? በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በ1 ጴጥሮስ 2:12 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት ተግባራዊ ማድረግን የሚጠይቅ ነገር ነው:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ . . . በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።” ክርስቲያኖች ተግባራቸው ራሱ እንዲመሠክር በማድረግ ራሳቸውን ብቁ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ! ይህም በመጨረሻ ለእኛ ሳይሆን ለአምላክ ውዳሴ ያመጣል። ይሁን እንጂ ራሳችንን በሌሎች ዘንድ ብቁ አድርገን ማቅረባችን በግል የሚያስገኝልን ጥቅምም አለ። ይህን ተግባራዊ ልታደርግ የምትችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት።
ወደፊት የትዳር ጓደኛ በመሆን ረገድ
ለምሳሌ ያህል የጋብቻን ጉዳይ እንውሰድ። ጋብቻ “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ እውነተኛ ስሙን ካገኘበት” ከይሖዋ አምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። (ኤፌሶን 3:15 የ1980 ትርጉም ) መቼም አንድ ቀን ማግባቴ አይቀርም ብለህ ታስብ ይሆናል። ከሆነ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመሆን ምን ያክል ብቁ ነኝ ትላለህ? አዎን፣ ነጠላ ክርስቲያን በሆንክበት በአሁኑ ጊዜ ምን ዓይነት ስም እያተረፍክ ነው?
በአንዳንድ አገሮች ይህ ጉዳይ ቤተሰቦችን በጣም የሚያሳስብ ነገር ነው። ለምሳሌ በጋና ባሕል መሠረት ሁለት ሰዎች ለመጋባት ሲያስቡ ሁለቱም የወደፊት ተጋቢዎች ለወላጆቻቸው ያሳውቃሉ። ወላጆቻቸው ደግሞ ለሌሎች የቤተሰብ አባላት ያሳውቃሉ። ከዚያም የወንዱ ቤተሰቦች ልጅቷ በአካባቢው ባሉ ሰዎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም እንዳተረፈች ማጣራት ይጀምራሉ። የወንዱ ወላጆች ልጅቷ ለልጃቸው እንደምትስማማ ሲያረጋግጡ ልጃቸው ልጅቷን ለማግባት ማሰቡን ለእርሷ ቤተሰቦች ያሳውቃሉ። የልጅቷ ቤተሰቦች ደግሞ በበኩላቸው በጋብቻው ሐሳብ ከመስማማታቸው በፊት ልጁ ምን ዓይነት ስም እንዳተረፈ ያጣራሉ። ስለሆነም “ከማግባትህ በፊት የሚያውቁትን ጠይቅ” የሚል አንድ የጋናውያን አባባል አለ።
በአብዛኛው ግለሰቡ ራሱ የትዳር ጓደኛውን በሚመርጥባቸው በምዕራባውያን አገሮች ስላለው ሁኔታስ ምን ለማለት ይቻላል? በእነዚህ አገሮችም ቢሆን የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሊያገቡት ያሰቡትን ሰው በትክክል የሚያውቁትንና ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ እውነቱን የሚነግራቸውን ሰው ቢጠይቁ ጥበብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ወላጆችን ወይም የጎለመሱ ጓደኞችን መጠየቅ ይቻላል። ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ በሚለው መሠረት አንዲት ወጣት እንደሚከተለው ብላ ልትጠይቅ ትችላለች:- “ ‘ይህ ሰው ምን ዓይነት ስም ነው ያለው? ጓደኞቹ እነማን ናቸው? ራሱን ይገዛልን? አረጋውያንን የሚይዘው እንዴት ነው? በምን ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገው? ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ነው? ለገንዘብ ያለው አመለካከት እንዴት ነው? የአልኮል መጠጦችን አለአግባብ ይጠጣልን? ግልፍተኛ፣ አልፎ ተርፎም ጠበኛ ነውን? ምን የጉባኤ ኃላፊነቶች አሉት? እነዚህን ኃላፊነቶቹንስ እንዴት እየተወጣቸው ነው? በጥልቅ ላከብረው እችላለሁን?’—ዘሌዋውያን 19:32፤ ምሳሌ 22:29፤ 31:23፤ ኤፌሶን 5:3-5, 33፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 6:10፤ ቲቶ 2:6, 7” a
አንድ ወንድም ለትዳር የሚያስባትን ክርስቲያን ሴት በተመለከተ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት ሊፈልግ ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚነግረን ቦዔዝ በኋላ ያገባትን ሩትን በተመለከተ አስቀድሞ አጣርቶ ነበር። ሩት “እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን?” ብላ በጠየቀችው ጊዜ ቦዔዝ “ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ” ሲል ነግሯታል። (ሩት 2:10-12) ሩት ታማኝ፣ ለአምላክ ያደረችና ታታሪ ሴት መሆኗን ሊገነዘብ የቻለው እንዲሁ ራሱ በተመለከተው ነገር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችም እሷን በተመለከተ መልካም አስተያየት ሰጥተውታል።
በተመሳሳይም የምታሳየው ምግባር ሌሎች አንተን ለትዳር ጓደኝነት በማሰብ ረገድ በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል። በዚህ ረገድ ራስህን በሌሎች ፊት እንዴት አድርገህ እያቀረብክ ነው?
ተቀጥረህ ስትሠራ
መልካም ምግባር ጥቅም ሊያስገኝልህ የሚችልበት ሌላው አቅጣጫ የሥራ ቦታ ነው። ሥራ ለማግኘት የሚደረገው ውድድር ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በእንቢተኝነታቸው፣ በአርፋጅነታቸው እንዲሁም በእምነት አጉዳይነታቸው
የሚታወቁ ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ የመባረር ዕጣ ይገጥማቸዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ድርጅቶች ወጪ ለመቀነስ ሲሉ የሥራ ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች ከሥራ ሊቀንሱ ይችላሉ። እነዚህ ሥራቸውን ያጡ ሰዎች ሌላ ቦታ ለመቀጠር በሚፈልጉበት ጊዜ ቀጣሪው ድርጅት ይሠሩበት በነበረው ቦታ ምን ዓይነት የሥራ ልማድ፣ ዝንባሌና ተሞክሮ እንደነበራቸው ከቀድሞ አሠሪዎቻቸው ያጣራል። ብዙ ክርስቲያኖች በሰው አክባሪነታቸው፣ በልከኛ አለባበሳቸው፣ ከሌሎች ጋር ተግባብተው በመሥራታቸውና በሌሎች ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያት ራሳቸውን ብቁ አድርገው ለአሠሪዎቻቸው አቅርበዋል።አብዛኞቹ ቀጣሪዎች ከእነዚህ ባሕርያት አንዱ ለሆነው ለሐቀኝነት ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም “በነገር ሁሉ በመልካም [“በሐቀኝነት፣” NW ]” መኖር እንፈልጋለን። (ዕብራውያን 13:18) በጋና የሚገኝ አንድ የማዕድን ማውጫ ኩባንያ ሠራተኞቹ ስርቆት እንደሚፈጽሙ ይደረስበታል። የይሖዋ ምሥክር የሆነው የማዕድን ማጣሪያ ፋብሪካው ዋና ተቆጣጣሪ ብቻ ሲቀር ሌሎች ሠራተኞች በሙሉ ተባረሩ። ለምን? የኩባንያው አስተዳደር ለዓመታት የዚህን ሰው ሐቀኝነት ይከታተል ስለነበረ ነው። በታታሪ ሠራተኝነቱና ለባለ ሥልጣን ባለው አክብሮትም ይታወቃል። አዎን፣ ያሳየው ጥሩ ምግባር ከሥራ ከመባረር አድኖታል!
አንድ ክርስቲያን በሥራው ዓለም በሌሎች ፊት ራሱን ብቁ አድርጎ ማቅረብ የሚችልባቸው ሌሎች መስኮች ምንድን ናቸው? የተሰጠህን ሥራ በጥሩ ችሎታ መሥራትን ተማር። (ምሳሌ 22:29) በትጋትና በጥንቃቄ ሥራ። (ምሳሌ 10:4፤ 13:4) አሠሪህንና የሥራ አለቃህን አክብር። (ኤፌሶን 6:5) ሰዓት አክባሪነት፣ ሐቀኝነት፣ ቅልጥፍናና ታታሪነት ቀጣሪዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጧቸው ባሕርያት ናቸው። እነዚህ ባሕርያት ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ እንኳ ሥራ እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ።
የጉባኤ ኃላፊነቶች
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የጎለመሱ ወንዶች ዛሬ ከምንጊዜውም ይበልጥ ያስፈልጋሉ። ለምን? ኢሳይያስ “የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፣ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ” ሲል ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 54:2) በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ዓለም አቀፉ የይሖዋ ጉባኤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ ነው።
ክርስቲያን ወንድ ከሆንክ በኃላፊነት ቦታ ላይ መሥራት ትችል ዘንድ ራስህን ብቁ አድርገህ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? የወጣቱ ጢሞቴዎስን ሁኔታ ተመልከት። ጢሞቴዎስ ‘በልስጥራንና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች ዘንድ በመልካም የተመሠከረለት’ እንደነበር ሉቃስ ዘግቧል። አዎን፣ ይህ ወጣት ባሳየው ጥሩ ምግባር የተነሳ በሁለት የተለያዩ ከተሞች በሌሎች ፊት ራሱን ብቁ አድርጎ አቅርቧል። ስለሆነም ጳውሎስ በተጓዥነት በሚያከናውነው አገልግሎት አብሮት እንዲሠራ ግብዣ አቅርቦለታል።—ሥራ 16:1-4
በዛሬው ጊዜ አንድ ወንድ ተገቢና አምላካዊ በሆነ መንገድ ‘ለበላይ ተመልካችነት መብት መጣጣር’ የሚችለው እንዴት ነው? የምረጡኝ ቅስቀሳ በማካሄድ ሳይሆን ለዚህ ዓይነት ኃላፊነቶች አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ባሕርያትን በመኮትኮት እንደሆነ ግልጽ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) በተጨማሪም በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ‘መልካምን ሥራ የሚመኝ’ መሆኑን ማሳየት ይችላል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ለክርስቲያናዊ ኃላፊነት ብቁ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወንዶች ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ደህንነት ከልብ ያስባሉ። “ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ይከተላሉ። (ሮሜ 12:13) አንድ ክርስቲያን ወንድ እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮችን በማድረግ በእርግጥ ‘ራሱን ብቁ የአምላክ አገልጋይ አድርጎ ሊያቀርብ’ ይችላል።
በማንኛውም ጊዜ
በሌሎች ፊት ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን ማለት መስለን ለመታየት ወይም ‘ሰውን ደስ ለማሰኘት’ እንሞክራለን ማለት አይደለም። (ኤፌሶን 6:6) ሕጎቹንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በጥንቃቄ በመጠበቅ በፈጣሪያችን በይሖዋ አምላክ ፊት ራሳችንን ብቁ አድርገን ማቅረብ ማለት ነው። መንፈሳዊነትህን ካዳበርክና ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ካጠናከርክ ከቤተሰብህ አባላት፣ ከሥራ ባልደረቦችህ እንዲሁም ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድ ያደረግኸውን መሻሻል ሌሎች ሰዎች ያስተውላሉ። በተጨማሪም ጽኑ አቋም ያለህና ሚዛንህን የምትጠብቅ መሆንህን፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታህን፣ ኃላፊነት ለመሸከም ያለህን ብቃትና ትህትናህን ይመለከታሉ። ይህም የእነሱን ፍቅርና አክብሮት ያተርፍልሃል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሌሎች ፊት ራስህን ብቁ አድርገህ ማቅረብህ የይሖዋን ሞገስ ያስገኝልሃል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስተዋይ የሆኑ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ሊያገቡት ያሰቡት ሰው ምን ዓይነት ስም እንዳተረፈ ያጣራሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ወንድም ለሌሎች አሳቢ በመሆን ለአንዳንድ የአገልግሎት መብቶች ራሱን ብቁ አድርጎ ያቀርባል