በትንቢት እንደተነገረው ሁሉን አዲስ ማድረግ
በትንቢት እንደተነገረው ሁሉን አዲስ ማድረግ
“በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው . . . አለኝ።”—ራእይ 21:5
1, 2. ብዙ ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል የሚለውን ጥያቄ ለመመርመር ማመንታታቸው የማያስገርመው ለምንድን ነው?
‘ነገ የሚያመጣውን ማን ያውቃል?’ ብለህ ተናግረህ ወይም አስበህ ታውቃለህ? ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ ለመገመት ለምን ፈራ ተባ እንደሚሉ ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንተነብያለን በሚሉ ደፋሮች ለምን እንደማይታመኑ መረዳት አያስቸግርህም። የሰው ልጆች በመጪዎቹ ወራት ወይም ዓመታት የሚሆኑትን ነገሮች በትክክል የመተንበይ ችሎታ ፈጽሞ የላቸውም።
2 ፎርብዝ አሳፕ የተባለ አንድ መጽሔት ጊዜን የሚመለከት አንድ እትም ይዞ ወጥቶ ነበር። እዚያም ላይ የቴሌቪዥን ጥናታዊ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት ሮበርት ክሪንግሊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይዋል ይደር እንጂ ጊዜ ሁላችንንም ማሳፈሩ አይቀርም፤ ሆኖም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንተነብያለን የሚሉ ሰዎችን የሚያሳፍረውን ያህል ማንንም አያሳፍርም። የወደፊቱ ጊዜ የሚያመጣውን ለመገመት መሞከር ማናችንም በአሸናፊነት ልንወጣ የማንችለው ጨዋታ ሆኗል ማለት ይቻላል። . . . ቢሆንም ሊቃውንት ነን ባዮች አሁንም መተንበያቸውን አላቆሙም።”
3, 4. (ሀ) አንዳንዶች አዲሱን ሺህ ዓመት በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) ሌሎች ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ምን አመለካከት አላቸው?
3 በርካታ ሰዎች ለአዲሱ ሺህ ዓመት ብዙ ትኩረት እንደሰጡ አስተውለህ ሊሆን ይችላል። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንደሚያስቡ ያሳያል። ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይ ማክሌንስ የተባለ መጽሔት “2000 ዓመት ለአብዛኞቹ ካናዳውያን ከሌሎቹ ዓመታት ያልተለየ ተራ ዓመት ሆኖ ሊታይ ቢችልም የአዲስ ጅምር መባቻ ሊሆን ይችላል” ብሏል። የዮርክ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስ ዱውድኒ የተሻለ ቀን ይመጣል ያሉበትን ምክንያት ሲገልጹ “አዲስ ሺህ ዓመት መጥባቱ በጣም አስከፊ ከነበረው መቶ ዓመት የሚገላግለን መሆኑ ነው” ብለዋል።
4 ይሁን እንጂ ይህ ባዶ ምኞት ሆኖ የሚቀር ነውን? በካናዳ በተደረገ አንድ ጥናት አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል “2000 ዓመት ለዓለም አዲስ ምዕራፍ ከፋች ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው” 22 በመቶዎቹ ብቻ ሆነው ተገኝተዋል። እንዲያውም ግማሽ ያህል የሚሆኑት በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ውስጥ “ሌላ ዓለም አቀፍ ግጭት” ማለትም ሌላ የዓለም ጦርነት ይነሳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። አብዛኞቹ ሰዎች አዲስ ሺህ ዓመት መምጣቱ ብቻ ችግሮቻችንን በሙሉ አስወግዶ ሁሉን ነገር አዲስ ያደርጋል የሚል እምነት የላቸውም። የብሪታንያ ሮያል ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ማይክል አቲያ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጣም ፈጣን በሆነው የለውጥ ሂደት ምክንያት . . . ሃያ አንደኛው መቶ ዘመን መላውን ሥልጣኔ የሚፈታተኑ ከባድ ችግሮች ያመጣል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የተፈጥሮ ሃብቶች መመናመን፣ የአካባቢ መበከልና የድህነት መስፋፋት ባሁኑ ጊዜ እንኳን በእጅጉ የሚፈታተነን ችግር በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል።”
5.ከፊታችን ስለሚጠብቀን ጊዜ አስተማማኝ መረጃ ከየት ልናገኝ እንችላለን?
5 ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ማወቅ እስካልቻሉ ድረስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ መተው የለብንም? ብለህ ታስብ ይሆናል። መልሱ ፈጽሞ መተው የለብንም የሚል ነው። ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል መተንበይ የማይችሉ መሆናቸው የማይካድ ቢሆንም ስለወደፊቱ ጊዜ ሊያውቅ የሚችል ማንም የለም ብለን ማሰብ አይኖርብንም። ታዲያ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማን ሊያውቅ ይችላል? በዚህስ ላይ ብሩሕ ተስፋ ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ከአራት ቀጥተኛ ትንቢቶች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ትችላለህ። ትንቢቶቹ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በብዙ ሰዎች እጅ ውስጥ በገባና በተነበበ፣ ግን ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ ችላ በተባለና ትክክለኛ ግንዛቤ ባላገኘ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለህ አመለካከት ምንም ዓይነት ቢሆን ወይም ምንም ያህል በሚገባ አውቀዋለሁ ብለህ ብታስብ እነዚህን አራት መሠረታዊ ጥቅሶች መመርመርህ ጥቅም ያስገኝልሃል። በጣም ብሩሕ ስለሆነ የወደፊት ጊዜ በትክክል ይተነብያሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ አራት ቁልፍ ትንቢቶች የራስህም ሆነ የምትወዳቸው ሰዎች የወደፊት ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ይገልጻሉ።
6, 7. ኢሳይያስ ትንቢቱን የተናገረው መቼ ነው? ትንቢቱስ አስገራሚ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
6 የመጀመሪያው የሚገኘው በኢሳይያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 65 ላይ ነው። ትንቢቱን ከማንበብህ በፊት መቼቱን ማለትም ትንቢቱ የተጻፈበትን ጊዜና ስለ ምን ነገር እንደሚናገር በግልጽ ተረዳ። እነዚህን ቃላት የጻፈው የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ የኖረው የይሁዳ መንግሥት ከመጥፋቱ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ነበር። የይሁዳ መንግሥት ፍጻሜ የሆነው ይሖዋ ከዳተኞቹን አይሁድ መጠበቁን በማቆሙ ምክንያት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን አውድመው ሕዝቦቿን አግዘው በወሰዱ ጊዜ ነበር። ይህ የተፈጸመው ኢሳይያስ ይሆናል ብሎ ከተነበየ ከመቶ ዓመት በላይ ቆይቶ ነው።—2 ዜና መዋዕል 36:15-21
7 የታሪኩን አፈጻጸም የተሟላ ገጽታ ለመጥቀስ ያህል በአምላክ መሪነት ኢሳይያስ በመጨረሻ ባቢሎንን የሚገለብጠው ፋርሳዊው ቂሮስ እንደሚሆን ንጉሡ ገና ሳይወለድ በፊት መተንበዩን አስታውስ። (ኢሳይያስ 45:1) ቂሮስ አይሁዳውያን በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን አመቻቸ። የሚያስገርመው በምዕራፍ 65 ላይ እንደምናነበው ኢሳይያስ ይህንን የሕዝቡን መመለስ ተንብዮ ነበር። እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሚያገኙት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጓል።
8.ኢሳይያስ ስለ ምን አስደሳች ጊዜ ተንብዮአል? በተለይ ትኩረት የሚስበው የትኛው አነጋገር ነው?
8 ኢሳይያስ 65:17-19 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።” ኢሳይያስ የገለጸው ሁኔታ አይሁዳውያን በባቢሎን ከነበሩበት እጅግ የተሻለ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ደስታና ሐሴት እንደሚሆን ተንብዮአል። አሁን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለውን ሐረግ ተመልከቱ። ይህ ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአራት ቦታዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን ይኸኛው የመጀመሪያው ነው። እነዚህ አራት ጥቅሶች ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን የሚገልጹልን፣ እንዲያውም የሚተነብዩልን ነገር ይኖራል።
9.የኢሳይያስ 65:17-19 ፍጻሜ የጥንት አይሁዳውያንን የሚመለከተው እንዴት ነው?
9 የኢሳይያስ 65:17-19 የመጀመሪያ ፍጻሜ የጥንቱን የአይሁድ ሕዝብ የሚመለከት ሲሆን ኢሳይያስ በትክክል እንደተነበየው ወደ አገራቸው ተመልሰው ንጹሕ አምልኮ አቋቁመዋል። (ዕዝራ 1:1-4፤ 3:1-4) እርግጥ፣ የተመለሱት በዚችው ምድር ላይ ወደምትገኘው ትውልድ አገራቸው እንጂ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ወደሚገኝ ሌላ ቦታ አልነበረም። ይህም ኢሳይያስ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ሲል ምን ማለቱ እንደነበር ለመገንዘብ ይረዳናል። አንዳንድ ሰዎች እንደ ኖስትራደመስ ያሉት ሰብዓውያን ነቢያት ነን ባዮች የተናገሩትን የተምታታ ትንቢት ለመረዳት እንደሚያደርጉት ግምት ውስጥ መግባት አያስፈልገንም። ኢሳይያስ ምን ማለቱ እንደነበረ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርግልናል።
10. ኢሳይያስ የተነበየውን “አዲስ ምድር” ልንረዳው የሚገባው እንዴት ነው?
10 “ምድር” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁልጊዜ ግዑዟን ምድር ብቻ አያመለክትም። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 96:1 ቃል በቃል “ምድር ሁሉ፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ” ይላል። የምንኖርባት ፕላኔታችን ማለትም ደረቁ ምድርም ሆነ ሰፊው ውቅያኖስ ሊዘምሩ እንደማይችሉ እናውቃለን። ሰዎች ግን ይዘምራሉ። አዎን፣ መዝሙር 96:1 የሚናገረው በምድር ላይ ስለሚኖሩ ሰዎች ነው። a ይሁን እንጂ ኢሳይያስ 65:17 ስለ ‘አዲስ ሰማይም’ ይናገራል። ‘አዲሱ ምድር’ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱትን አዲስ የአይሁድ ኅብረተሰብ ካመለከተ “አዲስ ሰማይ” የሚለውስ መግለጫ ምን ያመለክታል?
11. “አዲስ ሰማይ” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው ምንድን ነው?
11 በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክሊስያስቲካል ሊትረቸር እንዲህ ይላል:- “የትንቢታዊ ራእይ ትዕይንት በሚገለጽበት ቦታ ሁሉ ሰማይ የሚያመለክተው . . . ተፈጥሮአዊው ሰማይ ከምድር በላይ ሆኖ ምድርን እንደሚገዛ ሁሉ ከተገዥዎቹ በላይ ሆኖ የሚያስተዳድረውን . . . የገዥ ኃይሎች መደብ በጠቅላላ ነው።” ከዚያም “ሰማይና ምድር” ስለሚለው ጥምር ሐረግ ሳይክለፒዲያው ሲያብራራ ‘በትንቢታዊ ቋንቋ ሐረጉ የሚያመለክተው የተለያየ ማዕረግና ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው። ሰማይ የበላይ ገዥ ሲሆን ምድር ደግሞ ገባሩ ክፍል ማለትም በበላይ ባለ ሥልጣኖች የሚገዙት ሰዎች ክፍል ነው።’
12. የጥንቶቹ አይሁዳውያን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ያገኙት እንዴት ነው?
12 አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ያገኙት አዲስ የነገሮች ሥርዓት ሊባል የሚችል ነገር ነው። አዲስ አገዛዝ ነበር። የንጉሥ ዳዊት ተወላጅ የሆነው ዘሩባቤል ገዥ ሲሆን ኢያሱ ደግሞ ሊቀ ካህናቸው ሆነ። (ሐጌ 1:1, 12፤ 2:21፤ ዘካርያስ 6:11) እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ ተጣምረው “አዲስ ሰማያት” ሆኑ። ገዥ የሆኑት በምን ላይ ነበር? ያ “አዲስ ሰማይ” የተሾመው ኢየሩሳሌምን ለመገንባትና ይሖዋ የሚመለክበትን ቤተ መቅደስ ለማነጽ ወደ አገሩ በተመለሰው የጸዳ ኅብረተሰብ “አዲስ ምድር” ላይ ነበር። ስለዚህ በዚያ ጊዜ ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር በተያያዘ በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር ነበሩ።
13, 14. (ሀ) ልንመረምረው የሚገባን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለው ሐረግ የተጠቀሰበት ሌላው ቦታ የትኛው ነው? (ለ) የጴጥሮስ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ ልዩ ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
13 ይሁን እንጂ የተነሳንበትን ጭብጥ መሳት የለብንም። ዓላማችን በመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ላይ ጥናት ማድረግ ወይም የጥንት ታሪክ መዳሰስ አይደለም። “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለው ሐረግ ወደሚገኝበት ሌላ ቦታ በመሄድ ይህንን ለመገንዘብ ትችላለህ። 2 ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ላይ ይህን ሐረግ ልታገኝና የወደፊቱ ሕይወታችን ከዚህ ትንቢት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ መመልከት ትችላለህ።
14 ሐዋርያው ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ 500 ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ነው። ጴጥሮስ ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ እንደመሆኑ መጠን መልእክቱን የጻፈው በ2 ጴጥሮስ 3:2 ላይ ለተጠቀሰው “ጌታ” ለክርስቶስ ተከታዮች ነው። በ2 ጴጥ 3 ቁጥር 4 ላይ ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ‘መገኘት’ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ይጠቅሳል። ይህ ደግሞ ትንቢቱን ለዘመናችን በጣም ወቅታዊ ያደርገዋል። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ኢየሱስ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ላይ ገዥ ሆኖ በመሾም በሥልጣኑ ላይ ተገኝቷል። (ራእይ 6:1-8፤ 11:15, 18) ይህ ደግሞ ጴጥሮስ በዚህ ምዕራፍ ላይ በተነበየው ትንቢት መሠረት ልዩ ትርጉም ያለው ክንውን ነው።
15. ጴጥሮስ ስለ “አዲስ ሰማይ” የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
15 ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:13 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” ኢየሱስ ‘በአዲሱ ሰማይ’ ላይ ዋነኛ ገዥ መሆኑን ቀደም ብለህ ሳታውቅ አትቀርም። (ሉቃስ 1:32, 33) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን እንዳልሆነ ሌሎች ጥቅሶች ያመለክታሉ። ሐዋርያትና ሐዋርያትን የመሰሉ ሌሎች ሰዎች በሰማይ ቦታ እንደሚኖራቸው ኢየሱስ ቃል ገብቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ እነዚህን ሰዎች ‘የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች’ ሲል ጠርቷቸዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ የዚህ ቡድን አባሎች ከእርሱ ጋር በሰማይ በዙፋን ላይ እንደሚቀመጡ ተናግሯል። (ዕብራውያን 3:1፤ ማቴዎስ 19:28፤ ሉቃስ 22:28-30፤ ዮሐንስ 14:2, 3) ልብ ልንለው የሚገባን ቁም ነገር ሌሎችም የአዲስ ሰማይ ክፍል ሆነው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ መሆኑን ነው። ታዲያ ጴጥሮስ የጠቀሰው “አዲስ ምድር” ምንድን ነው?
16. በአሁኑ ጊዜ ያለው “አዲስ ምድር” ምንድን ነው?
16 የትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ የአይሁዳውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ ሲያመለክት የአሁኑ የ2 ጴጥሮስ 3:13 ፍጻሜም ለአዲሱ ሰማይ አገዛዝ በፈቃደኛነት የሚገዙ ሰዎችን የሚመለከት ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ለዚህ አገዛዝ ራሳቸውን በደስታ ያስገዙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ልታገኝ ትችላለህ። ከሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም በመጠቀም ላይ ከመሆናቸውም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ሕግጋት ለመከተል በመጣር ላይ ናቸው። (ኢሳይያስ 54:13) እነዚህ ከሁሉም ብሔራት፣ ቋንቋዎችና ዘሮች የተውጣጣ ምድር አቀፍ ኅብረተሰብ ስለሚያቋቁሙና ለንጉሡ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመገዛት አንድ ሆነው ስለሚሠሩ “ለአዲሱ ምድር” መሠረቶች ይሆናሉ። አንተም የዚህ አዲስ ምድር ክፍል መሆን የምትችል መሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው!—ሚክያስ 4:1-4
17, 18. በሁለተኛ ጴጥሮስ 3:13 ላይ የሚገኙት ቃላት የወደፊቱን ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንድንመለከት የሚያደርጉን ለምንድን ነው?
17 ይሁን እንጂ ጉዳዩ በዚህ ብቻ እንደሚያበቃና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተጨማሪ እውቀት የምናገኝባቸው ሌሎች ዝርዝር መግለጫዎች እንዳልተሰጡን አድርገህ አታስብ። እንዲያውም በ2 ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ዙሪያ ያለውን ሀሳብ በምትመረምርበት ጊዜ ከፊታችን ታላቅ ለውጥ እንደሚጠብቀን የሚያመለክት ፍንጭ ታገኛለህ። ጴጥሮስ በ2 ጴጥ 3 ቁጥር 5 እና 6 ላይ በኖኅ ዘመን ስለነበረውና በዚያ ዘመን የነበረውን ክፉ ዓለም ስላጠፋው የውኃ መጥለቅለቅ ጽፏል። በ2 ጴጥ 3 ቁጥር 7 ላይ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር” ማለትም ገዥዎቹም ሆኑ ሕዝቦቻቸው “እግዚአብሔርን የማያመልኩት [“አምላካዊ አክብሮት የሌላቸው፣” NW ] ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ” እንደተጠበቁ ይናገራል። ይህ ራሱ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር” የሚለው አገላለጽ ግዑዙን ምድር ሳይሆን ሰዎችንና አገዛዞቻቸውን እንደሚያመለክት ያረጋግጣል።
18 ጴጥሮስ በሚቀጥሉት ቁጥሮች ላይ መጪው የይሖዋ ቀን ትልቅ የጽዳት ሥራ እንደሚያከናውንና በ2 ጴጥ 3 ቁጥር 13 ላይ ለተጠቀሱት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን ያብራራል። “ጽድቅ የሚኖርበትን” የሚለውን የዚህን ጥቅስ ክፍል ልብ በል። ታዲያ ይህ የተሻለ ጊዜ የሚያመጣ አንድ ዓይነት ትልቅ ለውጥ እንደሚኖር አያመለክትም? ሰዎች በእርግጥ አስደሳች የሆኑ ነገሮችን ማለትም በአሁኑ ጊዜ የተሻለ አስደሳች ሕይወት ይመጣል ብለው እንዲጠባበቁ አያደርጋቸውም? እንዲህ የምታስብ ከሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ብዙ ሰዎች ያላገኙትን እውቀትና ማስተዋል እንዳገኘህ መገንዘብ ትችላለህ።
19. ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ እንደሚመጣ የሚያመለክተው የራእይ መጽሐፍ ትንቢት መቼት ምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ ሁኔታውን ጠለቅ ብለን እንመልከት። ይህ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለው ሐረግ የተጠቀሰባቸውን ኢሳይያስ ምዕራፍ 65ንና 2 ጴጥሮስ ምዕራፍ 3ን ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ይህ ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ አንድ ቦታ ላይ የተጠቀሰበትን ራእይ ምዕራፍ 21ን እናውጣ። እዚህም ላይ ቢሆን መቼቱን መረዳታችን ይጠቅመናል። ሁለት ምዕራፎች ቀደም ብሎ ራእይ ምዕራፍ 19 ላይ ሥዕላዊ በሆኑ ምሳሌዎች ስለተገለጸ ጦርነት እናነባለን። ጦርነቱ በጠላትነት በሚፈላለጉ ብሔሮች መካከል የሚካሄድ አይደለም። በዚህ ጦርነት በአንድ ወገን የተሰለፈው “የእግዚአብሔር ቃል” ነው። ይህ የማዕረግ ስም ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ እንደሆነ ሳታስታውስ አትቀርም። (ዮሐንስ 1:1, 14) እርሱ ያለው በሰማይ ሲሆን ራእዩም ከሰማያዊ ጭፍሮቹ ጋር እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። እነዚህ ጭፍሮች የሚዋጉት ከማን ጋር ነው? ምዕራፉ ‘ነገሥታትን፣ ሻለቃዎችን’ እና የተለያየ ደረጃ ያላቸው ‘ታናናሾችና ታላላቆችን’ ይጠቅሳል። ይህ ጦርነት ክፋት የሚወገድበት መጪው የይሖዋ ቀን ነው። (2 ተሰሎንቄ 1:6-10) ቀጥሎም ራእይ ምዕራፍ 20 የሚጀምረው “የቀደመው እባብ ዘንዶው፣ እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን” የሚወገድበትን ሁኔታ በመግለጽ ነው። ይህንን እንያዝና ራእይ ምዕራፍ 21ን እንመርምር።
20. ራእይ 21:1 ከፊታችን ምን ዓይነት ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ያመለክታል?
20 ሐዋርያው ዮሐንስ በሚቀጥሉት አስደሳች ቃላት ይጀምራል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም።” በኢሳይያስ ምዕራፍ 65 እና በ2 ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ላይ የተመለከትነውን መሠረት በማድረግ ይህ ጥቅስ ቃል በቃል ግዑዙ ሰማይ፣ የምንኖርባት ፕላኔትና በላይዋ ላይ የሚገኙት ባሕሮች ይወገዳሉ ማለቱ አይደለም። ቀደም ብለው ያሉት ምዕራፎች እንደሚያመለክቱት በዓይን የማይታየውን ገዥ ሰይጣንን ጨምሮ ክፉ ሰዎችና አገዛዛቸው ይወገዳሉ። አዎን፣ እዚህ ላይ ቃል የተገባልን በምድር ላይ ሰዎች የሚኖሩበት አዲስ የነገሮች ሥርዓት እንደሚመጣ ነው።
21, 22. ዮሐንስ ምን በረከት እንደሚዘንብ ማረጋገጫ ሰጥቷል? እንባዎች ይታበሳሉ የሚለው አነጋገር ትርጉም ምንድን ነው?
21 ይህን አስደናቂ ትንቢት ቀጥለን ስንመለከት ይህ ፈጽሞ ሊታበል የማይችል መሆኑን እናረጋግጣለን። ራእይ 21 ቁጥር 3 አምላክ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኘውን ትኩረቱን ፈቃዱን ወደሚያደርጉ ሰዎች በማዞር ከሰዎች ጋር ስለሚሆንበት ጊዜ ይናገራል። (ሕዝቅኤል 43:7) ዮሐንስ በራእይ 21 ቁጥር 4, 5 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “[ይሖዋ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና . . . በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።” እንዴት ያለ መንፈስን የሚያድስ ትንቢት ነው!
22 እዚህ ላይ ቆም እንበልና መጽሐፍ ቅዱስ የሚተነብይልንን ተስፋ እናጣጥም። ‘እግዚአብሔር እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል።’ ይህ እንባ በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉትን ዓይኖቻችንን የሚያጸዳውን የተለመደ ዓይነት እንባ ወይም የደስታ እንባን ሊያመለክት አይችልም። የለም፣ አምላክ የሚያብስልን እንባ በመከራ፣ በሐዘን፣ በብስጭት፣ በጉዳትና በመቃተት ምክንያት ስናፈስስ የቆየነውን እንባ ነው። እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ይህ አምላክ የሰጠው አስደናቂ ተስፋ ይህን እንባ ‘ከሞት፣ ከሐዘን ከጩኸትና ከሥቃይ ጋር’ አያይዞ እንደገለጸው መመልከት እንችላለን።—ዮሐንስ 11:35
23. በዮሐንስ ትንቢት ውስጥ ምን ነገሮች እንደሚወገዱ ዋስትና ተሰጥቷል?
23 ታዲያ ይህ ካንሰር፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም ሌላው ቀርቶ ሞት ፈጽሞ እንደሚወገዱ አያረጋግጥም? ከመካከላችን በጣም የሚወደውን ዘመዱን በበሽታ፣ በድንገተኛ ወይም በተፈጥሮ አደጋ ያላጣ ሰው ማን አለ? አምላክ ሞት ይቀራል ብሎ ቃል የገባ በመሆኑ በዚያ ጊዜ ሊወለዱ የሚችሉ ልጆች ካደጉ በኋላ የማርጀትና፣ በመጨረሻ በሞት የመሸነፍ ስጋት አይኖርባቸውም ማለት ነው። ከእርጅና ጋር ተግተልትለው የሚመጡት እንደ ኦልዛይመር በሽታ፣ ኦስትዮፖሮሲስ፣ ፋይብሮይድ ቲዩሞር፣ ግላውኮማና ካታራክት ያሉት በሽታዎች ይቀራሉ።
24. ‘አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር’ በረከት የሚሆነው እንዴት ነው? ገና መመርመር የሚኖርብን ነገር ምንድን ነው?
24 ሞት፣ እርጅናና በሽታዎች ሲወገዱ ሐዘንና ጩኸት በእጅጉ መቀነሱ አይቀርም ብላችሁ እንደምትስማሙ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ሰዎችን በመከራ የሚያደቅቀው ድህነት፣ በሕፃናት ላይ የሚደርሰው ወሲባዊ በደልና በእውቀት ደረጃ ወይም በቆዳ ቀለም ምክንያት የሚፈጸመው ጭቆናና አድልዎስ? እነዚህ በዛሬው ጊዜ በያለበት ተስፋፍተው የሚገኙት ሁኔታዎች የሚቀጥሉ ቢሆን ኖሮ ከሐዘንና ከጩኸት ነፃ ልንሆን አንችልም ነበር። ስለዚህ ‘በአዲሱ ሰማይና በአዲሱ ምድር’ የሚኖረው ሕይወት በአሁኑ ጊዜ ባሉ ለሐዘን ምክንያት በሆኑ ነገሮች ሁከት አይደርስበትም። ይህ እንዴት ያለ ለውጥ ነው! ቀደም ሲል እንደጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የሚለውን ሐረግ አራት ጊዜ የተጠቀመበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሦስቱን ተመልክተናል። እስከ አሁን ከመረመርናቸው ጋር ትስስር ያለው አንድ ተጨማሪ ትንቢት ይቀረናል። አምላክ ‘ሁሉን ነገር አዲስ ለማድረግ’ የገባውን ቃል መቼና እንዴት እንደሚፈጽም ለማየት በጉጉት የምንጠባበቅበትን ምክንያት ጎላ አድርጎ ያሳያል። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ስለዚህ ትንቢትና ለእኛ ደስታ ምን ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ማብራሪያ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል መዝሙር 96:1ን “በምድር ላይ የምትኖሩ ሰዎች ሁሉ ለጌታ ዘምሩ” ሲል ተርጉሞታል። ዘ ኮንተምፕረሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን ደግሞ “በዚህ ምድር ላይ የምትኖሩ ሁሉ ለጌታ ውዳሴ ዘምሩ” ይላል። ይህ አባባል ኢሳይያስ ወደ አገራቸው የተመለሱትን የአምላክ ሕዝቦች ለማመልከት “አዲስ ምድር” ብሎ ከተናገረው ጋር የሚስማማ ነው።
ምን ታስታውሳለህ?
• መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ትንቢት የሚናገርባቸው ሦስት ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?
• ‘የአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ትንቢት ፍጻሜ የጥንቶቹን አይሁዳውያን የሚመለከተው እንዴት ነው?
• ጴጥሮስ በጠቀሰው መሠረት ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ትንቢት ፍጻሜ ምን መረዳት ይቻላል?
• ራእይ ምዕራፍ 21 ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ የሚያመለክተው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልክ ይሖዋ እንደተነበየው ቂሮስ በ537 ከዘአበ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን አመቻቸ