በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሙዚቃ

አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሙዚቃ

አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሙዚቃ

ሙዚቃ “ከኪነ ጥበባት ሁሉ እጅግ ጥንታዊና ተፈጥሯዊ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። እንደ ቋንቋ ሁሉ ሰውን ከእንስሳ የሚለይ አስደናቂ ስጦታ ነው። ሙዚቃ ስሜት ይቀሰቅሳል። ለጆሮ የሚጥምና ከአእምሮ የማይጠፋ ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላክን ሊያስደስት ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው እስራኤላውያን ሙዚቃን እጅግ ያፈቅሩ ነበር። ኡንገር የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ሙዚቃ “በጥንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዋነኛው ኪነ ጥበብ ነበር” በማለት ሐሳብ ሰጥቷል። የዕለት ተዕለት የሕይወታቸው ክፍል እንደመሆኑ መጠን በድምፅም ይሁን በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ የአምልኮታቸው ጉልህ ገጽታ ነበር። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የሚዜመው በድምፅ ነበር።

ንጉሥ ዳዊት ልጁ ሰሎሞን ያስገነባው ቤተ መቅደስ ከመመረቁ በፊት ከሌዋውያን መካከል መርጦ በመገናኛው ድንኳን ፊት ‘የሚያዜሙ’ የመዘምራን አለቆችን አቁሞ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 6:​31, 32) የይሖዋን መገኘት የሚወክለው የቃል ኪዳን ታቦት ኢየሩሳሌም ሲደርስ ዳዊት “እግዚአብሔርን ያወድሱት ዘንድ ያመሰግኑትና ያከብሩት ዘንድ” ከሌዋውያን መካከል አንዳንዶችን የመደበ ሲሆን በድምፅ የሚያሰሙት የውዳሴ መዝሙር “በመሰንቆና በበገና . . . በጸናጽል . . . በመለከት” ይታጀብ ነበር። እነዚህ ሰዎች የተመረጡት ‘ፍቅራዊ ደግነቱ ለዘላለም የሆነውን ይሖዋን ለማመስገን’ ነው።​—⁠1 ዜና መዋዕል 16:​4-6, 41፤ 25:​1

“ምሕረቱም ለዘላለም ነውና” የሚለው አዝማች በአብዛኛው ከሙዚቃ ጋር ዝምድና ባለውና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። ለምሳሌ ያክል ይህ አዝማች 26 ቁጥሮች ባሉት በ136ኛ መዝሙር በእያንዳንዱ ቁጥር ሁለተኛ መስመር ላይ ይገኛል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እንዳስቀመጡት “በአጭር በአጭሩ የቀረበው አዝማች ሰዎች በቀላሉ እንዲያዜሙት ያስችላቸዋል። ይህ መዝሙር ሲዘመር የሰማ ማንኛውም ሰው ያለችግር ሊያስታውሰው ይችላል።”

በመዝሙሮቹ አናት ላይ የሚገኙት መግለጫዎች የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች በሰፊው ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይጠቁማሉ። መዝሙር 150 ከመሰንቆ በተጨማሪ መለከት፣ በገና፣ እምቢልታ፣ ዋሽንትና ጸናጽልን ይጠቅሳል። ያም ሆኖ ግን ከእነዚህ ሙዚቃ መሣሪያዎች ይበልጥ ተመራጭ የሚሆነው የሰዎች ድምፅ ነው። ቁጥር 6 “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ” ሲል ማሳሰቢያ ይሰጣል!

ሙዚቃ ስሜታችንን የመግለጽ ባሕሪ ስላለው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ሃዘናቸውን በሙሾ ወይም በእንጉርጉሮ ይገልጹ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የሃዘን መግለጫ እንጉርጉሮ በእስራኤል የሙዚቃ ስልት ብቻ የተወሰነ ነበር። ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ “እንጉርጉሮ ከሙዚቃ ዜማም ይሁን ከድምፅ ቅላጼ የሚመረጠው በሙሾ ወይም በሐዘን እንጉርጉሮ ጊዜ ብቻ ነው” ሲል ይገልጻል። a

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት እሱና ታማኝ ሐዋርያቱ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምረው ነበር። በዚህ ወቅት የሃሌል መዝሙሮችን እንዳዜሙ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 113-118) ይህም ጌታቸውን በሞት የሚያጡትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አበርትቷቸው መሆን አለበት! ከሁሉም በላይ ደግሞ “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና” የሚለውን አዝማች አምስት ጊዜ ሲደጋግሙ የጽንፈ ዓለም የበላይ ጌታ የሆነውን ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ባደረጉት ቁርጥ ውሳኔ እንዲጸኑ ሳያደርጋቸው አልቀረም።​—⁠መዝሙር 118:​1-4, 29

በኤፌሶንና በቆላስይስ ጉባኤዎች ውስጥ የነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “መዝሙርና ዝማሬ” ያቀርቡ ነበር። በተጨማሪም በልባቸው “መንፈሳዊ ቅኔ” ዘምረዋል። (ኤፌሶን 5:​19፤ ቆላስይስ 3:​16) በመዝሙርም ሆነ በንግግር አንደበታቸውን ይሖዋን ለማወደስ ተጠቅመውበታል። ኢየሱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” በማለት አላስታወቀምን?​—⁠ማቴዎስ 12:​34

አምላክ የማይደሰትበት ሙዚቃ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውን ሙዚቃ ሁሉ አምላክ ተደስቶበታል ማለት አይደለም። ሙሴ አሥሩን ትእዛዛት ጨምሮ ሕጉን ለመቀበል ወደ ሲና ተራራ በወጣ ጊዜ ምን ነገር እንደተፈጠረ ልብ በል። ሙሴ ከተራራው ሲወርድ የሰማው የምን ድምፅ ነበር? “የድል ነሺዎች ድምፅ አልነበረም፤” “የድል ተነሺዎች ድምፅም አይደለም፤” ነገር ግን “የዘፈን ድምፅ” ነበር። ይሖዋ ያልተደሰተበት ይህ ዘፈን ወደ 3, 000 የሚጠጉ ሰዎች እንዲጠፉ ምክንያት የሆነ ከጣዖት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው ዘፈን ነበር።​—⁠ዘጸአት 32:​18, 25-28

ምንም እንኳን ሰዎች ብዙ የሙዚቃ ዓይነቶችን መድረስ፣ መጫወትና በእነርሱ መደሰት ቢችሉም ሁሉም የሙዚቃ ዓይነቶች ይሖዋን ያስደስቱታል ማለት አይደለም። ለምን? ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 3:​23) የሙዚቃ ቅንብሮች ርዕስ በአብዛኛው ከአረማዊ የመራባት አምልኮ፣ ነፍስ አትሞትም ከሚለው መሠረተ ትምህርትና ማርያም “የአምላክ እናት” ነች ተብሎ ከሚሰጣት ክብር ጋር የተቆራኘ ነው። ሆኖም እነዚህ እምነቶችና ልማዶች በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስለሚጋጩ ለእውነት አምላክ ክብር አያመጡም።​—⁠ዘዳግም 18:​10-12፤ ሕዝቅኤል 18:​4፤ ሉቃስ 1:​35, 38

ተገቢ የሆነ ሙዚቃ መምረጥ

ሙዚቃ መምረጥ ቀላል አይደለም። የኮምፓክት ዲስኮች ሽፋን የሚዘጋጀው ሰዎች ሳይመርጡ ሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ እንዲገዙ በሚጋብዝ ሁኔታ ነው። ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት የሚፈልግ ሰው ከሐሰት ሃይማኖት እምነቶች የመነጩ ወይም በርኩስ ሥነ ምግባርና በክፉ መናፍስት ላይ ያተኮሩ በድምፅ የሚዜሙም ሆነ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ የሙዚቃ ዓይነቶች እንዳይመርጥ መጠንቀቅ ያስፈልገዋል።

በአንድ ወቅት አፍሪካ ውስጥ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለግል የነበረው አልበርት በዚያ ወቅት ፒያኖ ለመጫወት አጋጣሚ እንዳልነበረው ተናግሯል። ሆኖም ወደ አፍሪካ ሲመጣ ይዟቸው የመጣቸውን ጥቂት ሙዚቃዎች ደግሞ ደጋግሞ ያዳምጥ ነበር። አልበርት አሁን ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ጉባኤዎችን ይጎበኛል። ሙዚቃ ለማዳመጥ ያለው ጊዜ ውስን ነው። “የቤትሆቨንን የሙዚቃ ቅንብሮች በጣም እወዳቸዋለሁ። እሱ ያቀናበራቸው ሲምፎኒ፣ ኮንሴርቶ፣ ሶናታ እና ኳርቴት የተባሉ በርካታ የሙዚቃ ቅጂዎች ባለፉት ዓመታት ስገዛ ቆይቻለሁ።” እነዚህን ሙዚቃዎች ማዳመጥ ታላቅ እርካታ አስገኝቶለታል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ የሙዚቃ ምርጫ አለው። ይሁን እንጂ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ጳውሎስ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ሲል የሰጠውን ምክር ከሐሳባችን ልናወጣው አይገባም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​31

ሙዚቃ እና ራስን ለአምላክ መወሰን

ሱዚ ከምንም ነገር አብልጣ ሙዚቃን ትወድ ነበር። “ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ፒያኖ፣ በ10 ዓመቴ ቫዮሊን በመጨረሻም በ12 ዓመቴ በገና መጫወት ጀመርኩ” ትላለች። ከጊዜ በኋላ ሱዚ በገናን ለማጥናት ለንደን እንግሊዝ በሚገኘው ሮያል የሙዚቃ ኮሌጅ ገባች። ዝነኛዋ ስፔናዊት የበገና ተጫዋች አራት ዓመት አስተማረቻት። ከዚያም በፓሪስ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለተጨማሪ ዓመት ከሰለጠነች በኋላ በሙዚቃ የክብር ዲግሪዋን እንዲሁም በገናን ለመጫወትና የፒያኖ አስተማሪ በመሆን ዲፕሎማዎቿን አገኘች።

ሱዚ ለንደን በሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ላይ መገኘት ጀመረች። እዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ከልብ እንደሚተሳሰቡና እንደሚፋቀሩ ተመለከተች። ቀስ በቀስ ለይሖዋ ያላት ፍቅር እያደገ መጣ፤ እንዲሁም ለአገልግሎቱ ያላት ቅንዓት እርሱን ለማገልገል ሁኔታዋን እንድታስተካክል ገፋፋት። ይህም ራሷን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ አደረሳት። “ሙዚቃን እንደ ሙያ አድርጎ መያዝ ሙሉ በሙሉ ለሙያው ማደርን የሚጠይቅ ስለሆነ ራስን መወሰን ለእኔ እንግዳ የሆነ ነገር አልነበረም” በማለት ተናግራለች። ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ስትጠመድ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት የምታጠፋው ጊዜ እየቀነሰ መጣ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ ማርቆስ 13:​10

በአሁኑ ጊዜ ሙዚቃን ለመጫወት የሚያስችል ብዙ ጊዜ የላትም። ታዲያ ምን ይሰማት ይሆን? “አንዳንድ ጊዜ ሙዚቃ ለመጫወት በቂ ጊዜ የሌለኝ መሆኑ ትንሽ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሙዚቃ መሣሪያዎቼን በመጫወት ሙዚቃን አጣጥማለሁ። ሙዚቃ የይሖዋ ስጦታ ነው። አሁን የእርሱ አገልግሎት በሕይወቴ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ስላደረግሁ በሙዚቃ ይበልጥ እደሰታለሁ።”​—⁠ማቴዎስ 6:​33

አምላክን የሚያወድስ ሙዚቃ

አልበርትና ሱዚ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሌሎች ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ዘወትር ይሖዋ አምላክን በሙዚቃ ያወድሳሉ። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸውን በሚያደርጉባቸው በ234 አገሮች በሚገኙ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ አመቺ ከሆነ ከስብሰባ በፊትና በኋላ መዝሙሮችን በመዘመር ይሖዋን ያወድሳሉ። ይሖዋ አምላክን የሚያወድሱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግጥሞችን በሜጀርና ማይነር ቁልፎች በተቀነባበሩ ጣዕመ ዜማዎች በማጀብ ይዘምራሉ።

በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ይሖዋ አሳቢ አምላክ መሆኑን በመግለጽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይዘምራሉ። (መዝሙር ቁጥር 44) ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ይዘምራሉ። (መዝሙር ቁጥር 190) መዝሙሮቻቸው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታቸው፣ ክርስቲያናዊ አኗኗራቸው እንዲሁም ክርስቲያናዊ ባሕርያቸው የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነቶችና ያስገኘላቸውን ደስታ ለይተው የሚያመለክቱ ናቸው። ከእስያ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እንዲሁም ከሰሜንና ከደቡብ አሜሪካ የተውጣጡት ምሥክሮች ጣዕመ ዜማዎቹን ባቀናበሩበት ወቅት የተለያየ የሙዚቃ ስታይል መጠቀማቸው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎላቸዋል። b

መዝሙራዊው በኖረበት ዘመን የተጻፈው ክብራማ መዝሙር የመክፈቻ ቃላት እንደዚህ ይላሉ:- “ለይሖዋ አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ የምድር ሕዝብ ሁሉ ለይሖዋ ዘምሩ። ለይሖዋ ዘምሩ ስሙንም ባርኩ፤ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ።” (መዝሙር 96:​1-3 NW ) በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እንደዚህ እያደረጉ ሲሆን አንተም አብረሃቸው ሆነህ በዚህ የውዳሴ መዝሙር እንድትካፈል ይጋብዙሃል። ይሖዋን በሚያስደስተው ሙዚቃ እንዴት ማወደስ እንደምትችል ለመማር ወደ መንግሥት አዳራሾቻቸው ብትመጣ በደስታ ይቀበሉሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

b እነዚህ መዝሙሮች የሚገኙት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ባሳተመው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር መዘመር