“ክርስቲያን” የሚለው ቃል ትርጉሙን እያጣ ነውን?
“ክርስቲያን” የሚለው ቃል ትርጉሙን እያጣ ነውን?
ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ምን ብለህ ትመልሳለህ? በተለያዩ አገሮች ለሚኖሩ እንደ አጋጣሚ ለተመረጡ ሰዎች ይኸው ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ከሰጧቸው መልሶች መካከል ለናሙና ያህል ቀጥሎ የቀረቡት ይገኙበታል:-
“ኢየሱስን መከተልና እሱን መምሰል።”
“ጥሩ ሰው መሆን፤ ያለህን ደግሞ ለሌሎች ማካፈል።”
“ክርስቶስን ጌታና አዳኝ አድርጎ መቀበል።”
“ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስ፣ አቡነ ዘበሰማያትን መድገም እንዲሁም ቅዱስ ቁርባን መካፈል።”
“ክርስቲያን ለመሆን የግድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።”
መዝገበ ቃላት እንኳ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ፍቺዎች ይሰጣሉ። እንዲያውም አንድ መዝገበ ቃላት “ክርስቲያን” በሚለው ቃል ሥር አሥር ፍቺዎችን አስፍሯል። “በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ወይም እሱ የመሠረተው ሃይማኖት ክፍል መሆን” ከሚለው አንስቶ “ሥርዓታማ ወይም ጨዋ ሰው” የሚሉ የተለያዩ ፍቺዎችን ይዟል። ብዙዎች ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ መግለጽ የሚከብዳቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም።
ነፃ አስተሳሰብ የመያዝ አዝማሚያ
በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ነን በሚሉ አልፎ ተርፎም የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል በሆኑ ሰዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ስለ መጻፉ፣ ስለ አዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ፣ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ጉዳዮች ስለመግባትዋ እንዲሁም አንድ ሰው እምነቱን ለሌሎች ስለማካፈሉ በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በጣም የተራራቀ አመለካከት እንዳላቸው አንድ ሰው ማስተዋል ይችላል። እንደ ውርጃ፣ ግብረ ሰዶማዊነትና ሳይጋቡ አብሮ መኖር የመሳሰሉ ሥነ ምግባር ነክ ጉዳዮች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳሉ። አዝማሚያው ነፃ አስተሳሰብ የመያዝ አካሄድ እንዳለው ግልጽ ነው።
ለምሳሌ ያህል አንድ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ኮሚቴ “ግብረ ሰዶም ፈጻሚ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ሽማግሌን የአስተዳደር ቦርድ አባል እንዲሆን ለመምረጥ” ቤተ ክርስቲያን ያላትን መብት በመደገፍ በቅርቡ ድምፀ ውሳኔ ማስተላለፉን ክርስቺያን ሴንቸሪ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። ይባስ ብሎም አንዳንድ የቲኦሎጂ ምሁራን ለመዳን በኢየሱስ ማመን የግድ አስፈላጊ አይደለም የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። አይሁዶች፣ ሙስሊሞችም ሆኑ ሌሎች “[እንደ ክርስቲያኖች ሁሉ] ወደ ሰማይ የመግባት አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል” የሚል እምነት እንዳላቸው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ገልጿል።
እስቲ፣ ማርክሲስት ሆኖ ካፒታሊዝምን የሚደግፍ ወይም ዲሞክራት ሆኖ አንባገነን አገዛዝ የሚያራምድ ወይም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተሟጋች ሆኖ ደን ምንጠራን የሚደግፍ ሰው ይኖራል ብለህ ገምት። “ይህ ሰው እውነተኛ ማርክሲስት ወይም ዲሞክራት ወይም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተሟጋች ሊሆን አይችልም” ማለትህ አይቀርም፤ እንዲህ በማለትህም አልተሳሳትክም። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያን ነን ባዮች ያላቸውን የአመለካከት ልዩነት ስትመለከት በጣም የተራራቀና የክርስትና እምነት መስራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው ጋር በአመዛኙ የሚቃረን እምነት እንዳላቸው ትገነዘባለህ። ይህ የአመለካከት ልዩነት ምን ዓይነት የክርስትና ዘርፎች ስለመሆናቸው ምን ይናገራል?—1 ቆሮንቶስ 1:10
ቀጥሎ እንደምንመለከተው ከጊዜው አስተሳሰብ ጋር ተስማምቶ ለመሄድ ሲባል የክርስትና ትምህርቶችን ለመለወጥ የተደረገው ጥረት የቆየ ታሪክ አለው። አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እንደዚህ ዓይነቶቹ ለውጦች ምን ይሰማቸዋል? በክርስቶስ ላይ ያልተመሠረቱ ትምህርቶችን የሚደግፉ አብያተ ክርስቲያናት በትክክል ክርስቲያን ነን ሊሉ ይችላሉን? እነዚህ ጥያቄዎች ቀጥሎ ባለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።