የነበረብኝን የዓይናፋርነት ስሜት ለማሸነፍ እርዳታ አገኘሁ
የሕይወት ታሪክ
የነበረብኝን የዓይናፋርነት ስሜት ለማሸነፍ እርዳታ አገኘሁ
ሩት ኤል ኦልሪክ እንደተናገረችው
በቄሱ ቤት በር ላይ እንደቆምኩ ክው ብዬ ቀረሁ፤ ከዚያም ልቅሶዬን አስነካሁት። የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በነበረው በቻርልስ ቲ ራስል ላይ የሐሰት ክስ ያዥጎደጎደው ይህ ቄስ ነበር። እስቲ ገና በልጅነቴ በየቤቱ እየሄድኩ ሰዎችን ለማነጋገር የበቃሁት እንዴት እንደሆነ ላጫውታችሁ።
ኔብራስካ ዩ ኤስ ኤ በሚገኝ እርሻ ቦታ በሚኖር በጣም ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ በ1910 ተወለድኩ። በየዕለቱ ጧትና ማታ ምግብ ከበላን በኋላ አንድ ላይ ሆነን መጽሐፍ ቅዱስ እናነብ ነበር። አባቴ ከእርሻ ቦታችን በ6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዊንሳይድ የምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ በሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ኃላፊ ነበር። በጨርቅ የተጋረዱ መስኮቶች ያሉት የፈረስ ሰረገላ ስለነበረን አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ቢኖርም እንኳን እሁድ ጧት ከቤተ ክርስቲያን አንቀርም።
በስምንት ዓመቴ ገደማ ትንሹ ወንድሜ በልጅነት ልምሻ ስለተጠቃ እናቴ እሱን ለማሳከም በኢዮዋ ክፍለ ሃገር ወዳለ የአካል ጉዳተኞች ማረፊያ ወሰደችው። ብዙ የደከመችለት ቢሆንም እንኳን ከሞት ሊድን አልቻለም። ሆኖም እናቴ በኢዮዋ እያለች ከአንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መጠሪያ ነበር) ጋር ተገናኘች። ብዙ ውይይት ያደረጉ ሲሆን እንዲያውም እናቴ ከሴትየዋ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ተገኝታ ነበር።
ወደ ቤት ስትመለስ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በብዙ ጥራዞች ያሳተመውን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ይዛ መጣች። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነትን እንደሚያስተምሩና ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው እንዲሁም ክፉ ሰዎች በዘላለም ቅጣት ይሰቃያሉ የሚሉት ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም።—ዘፍጥረት 2:7 [NW ]፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4
ይሁን እንጂ አባቴ በሁኔታው በጣም ስለተበሳጨ እናቴ
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት ስታደርግ ይቃወማት ነበር። እኔንና ታላቅ ወንድሜ ክላረንስን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዞ ይሄድ ጀመር። ሆኖም አባታችን እቤት በማይኖርበት ጊዜ እናታችን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናን ነበር። ይህ መሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያስተምሩትን ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ከምንማረው ጋር ለማወዳደር መልካም አጋጣሚ ከፍቶልናል።እኔና ክላረንስ በቤተ ክርስቲያን በሚሰጠው የሰንበት ትምህርት ላይ ዘወትር የምንገኝ ሲሆን ክላረንስ አስተማሪያችን ልትመልሳቸው የማትችላቸውን አስቸጋሪ ጥያቄዎች ይጠይቃት ነበር። እቤት ስንመለስ የሆነውን ሁሉ ለእናታችን እንነግራትና በዚያ ርዕስ ላይ ረጅም ውይይት እናደርጋለን። በመጨረሻ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆምኩና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ክላረንስም ተመሳሳይ እርምጃ ወሰደ።
ዓይናፋርነትን ማሸነፍ
መስከረም 1922 እኔና እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ባደረጉት የማይረሳ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በዚያ ወቅት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ከ18, 000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” እያለ በማሳሰብ ላይ ሳለ በረጅም የተዘረጋው እነዚህ ቃላት የተጻፉበት ጨርቅ እስከ አሁን ከፊቴ አይጠፋም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ሰዎች የመናገሩ ጉዳይ ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ በጥልቅ እንዲሰማኝ አድርጓል።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14
ከ1922 እስከ 1928 ድረስ በተከታታይ በተደረጉት ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የአቋም መግለጫዎች የተላለፉ ሲሆን እነዚህ መግለጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በብዙ ሚልዮን ቅጂዎች አባዝተው በሚያሰራጯቸው ትራክቶች ላይ ታትመው ይወጡ ነበር። ረጅምና ቀጭን በመሆኔ ሶለግ ውሻ የሚል ቅጽል ስም ያወጡልኝ ሲሆን በፍጥነት ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት እየሄድኩ እነዚህን ትራክቶች ዝም ብዬ አድል ነበር። ይህን ሥራ መሥራት በጣም ያስደስተኝ ነበር። በየቤቱ እየሄዱ እያንዳንዱን ሰው ፊት ለፊት አግኝቶ ስለ አምላክ መንግሥት ማነጋገር ግን ለእኔ በጣም ፈተና ነበር።
የሚገርማችሁ በጣም ዓይናፋር ከመሆኔ የተነሳ እናቴ በየዓመቱ ዘመዶቻችንን እቤታችን በጋበዘች ቁጥር የምገባበት ይጠፋኝ ነበር። ሮጬ መኝታ ክፍሌ ገብቼ
እደበቃለሁ። አንድ ቀን እናቴ መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ፎቶግራፍ እንዲነሳ ፈለገችና ካለሁበት እንድወጣ ነገረችኝ። እነርሱን ማየት ስላልፈለግሁ ከክፍሌ ለማስወጣት ስትጎትተኝ ጩኸቴን አቀለጥኩት።አይደርስ ነገር የለም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቦርሳዬ ይዤ አገልግሎት የምወጣበት ጊዜ ደረሰ። ደግሜ ደጋግሜ “ይሄንንማ አልሞክረውም” አልኩኝ። በሌላ ጊዜ ግን “ማድረግ አለብኝ” ስል ለራሴ ተናገርኩ። በመጨረሻ ወደ አገልግሎት ወጣሁ። ከዚያ በኋላ አገልግሎት ለመውጣት ድፍረት በማግኘቴ በጣም ደስ አለኝ። ትልቅ እርካታ የማገኘው አገልግሎት ላይ እያለሁ ሳይሆን አገልግሎቴን ከጨረስኩ በኋላ ነው። ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን ቄስ ያገኘሁትና እያለቀስኩ ጥዬው የሄድኩት በዚያ ሰሞን ነበር። ከጊዜ በኋላ በይሖዋ እርዳታ ሰዎችን በየቤታቸው እየሄድኩ ማነጋገር በመቻሌ ደስታዬ እየጨመረ መጣ። ከዚያም በ1925 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር
አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ አንዲት አክስቴ ባወረሰችኝ ገንዘብ መኪና ገዛሁና አቅኚነት ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። በ1930 ከሁለት ዓመት በኋላ የአቅኚ ጓደኛዬና እኔ የአገልግሎት ክልል ተቀበልን። በዚያ ወቅት ክላረንስም አቅኚ ሆኖ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በቤቴል ማለትም በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ እንዲሠራ የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ።
በዚያው ሰሞን ወላጆቻችን ተለያዩ፤ ስለዚህ እናቴና እኔ ተንቀሳቃሽ ቤት አሠራንና በአቅኚነት አንድ ላይ ማገልገል ጀመርን። ይህ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ ድንገት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ በገባችበት በጥቅምት 1929 ነበር። በአቅኚነት መቀጠል በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ላለማቋረጥ ቁርጥ ውሳኔ አደረግን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በዶሮ፣ በእንቁላልና በጓሮ አትክልቶች እንዲሁም በአሮጌ ባትሪዎችና በተጣሉ አሉሚነሞች እንለውጥ ነበር። አሮጌ ባትሪዎችንና አሉሚነሞችን ሸጠን የምናገኘውን ገንዘብ ለመኪናችን ነዳጅ ለመግዛትና ሌሎች ወጪዎቻችንን ለመሸፈን ያግዘን ነበር። እንዲሁም ገንዘብ ለመቆጠብ ስል መኪና ግራሶ ማጠጣትና ዘይት መቀየር ተማርኩ። ይሖዋ የሚገጥሙንን እንቅፋቶች እንድንቋቋም በመርዳት የገባውን ቃል የሚፈጽም መሆኑን ለመመልከት ችለናል።—ማቴዎስ 6:33
የሚስዮናዊነት አገልግሎት
በ1946 በሳውዝ ላንሲንግ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት በሰባተኛው ክፍል እንድማር ተጋበዝኩ። በዚያን ጊዜ ከእናቴ ጋር ከ15 ዓመት በላይ አብረን በአቅኚነት አገልግለናል፤ በመሆኑም በሚስዮናዊነት ሥራ ለመሰልጠን ያገኘሁትን ይህን አጋጣሚ ለማከላከል አልፈለገችም። ከዚህ ይልቅ በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል ያገኘሁትን መብት እንድቀበል አበረታታችኝ። ከተመረቅን በኋላ ከፒኦሪያ ኢሊኖይስ ከመጣችው ከማርታ ሄስ ጋር አብረን ተመደብን። በባሕር ማዶ ሌላ የአገልግሎት ምድብ እስኪሰጠን ድረስ ከሌሎች ሁለት እህቶች ጋር ለአንድ ዓመት በኦሃዮ ክሌቭላንድ እንድናገለግል ተመደብን።
ምድባችን የተነገረን በ1947 ነበር። እኔና ማርታ ሃዋይ ተመደብን። ወደ እነዚህ ደሴቶች መግባት ብዙም አስቸጋሪ ስላልነበረ እናቴም ወደ ሃዋይ መጣችና ሆኖሉሉ ከተማ ውስጥ በአቅራቢያችን ትኖር ጀመር። ጤንነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ስለመጣ የሚስዮናዊነት ሥራዬን እያከናወንኩ እናቴንም መርዳት ነበረብኝ። በ1956 በ77 ዓመቷ በሃዋይ እያለች እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን እንክብካቤ ላደርግላት ችያለሁ። እዚያ በደረስንበት ጊዜ በሃዋይ የነበሩት ምሥክሮች 130 ገደማ ነበሩ። ይሁን እንጂ እናቴ በሞተችበት ወቅት የአስፋፊዎች ቁጥር ከአንድ ሺ በላይ ደርሶ ስለነበር በዚያ ሚስዮናውያን ብዙም አያስፈልጉም ነበር።
ከዚያም እኔና ማርታ ጃፓን እንደተመደብን የሚገልጽ ደብዳቤ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደረሰን። ከሁሉ በላይ ያሳሰበን ነገር በዚህ ዕድሜያችን ጃፓንኛ መማር ከባድ አይሆንብንም ወይ የሚለው ነበር። በዚያ ጊዜ እኔ 48 ዓመት ሲሆነኝ ማርታ ደግሞ በአራት ዓመት ከእኔ ታንሳለች። ጉዳዩን ለይሖዋ ትተን ምድባችንን ተቀበልን።
በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ የተደረገውን የአውራጃ ስብሰባ ከተካፈልን
በኋላ ወዲያውኑ በመርከብ ተሳፍረን ወደ ቶኪዮ ተጓዝን። ዮኮሃማ ወደብ ልንደርስ በተቃረብን ጊዜ ታይፉን የተባለ ከባድ አውሎ ነፋስ አንገላታን። ዮኮሃማ ስንደርስ ከዳንና ማበል ሃስለት፣ ከሎይድና ሜልባ ባሪ እንዲሁም ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር ተገናኘን። በዚያን ጊዜ በጃፓን 1, 124 ምሥክሮች ብቻ ነበሩ።ወዲያውኑ ጃፓንኛ መማር ብቻ ሳይሆን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎትም መካፈል ጀመርን። የጃፓንኛ አቀራረቦችን በእንግሊዝኛ ፊደላት እየጻፍን ለቤት ባለቤቶች እናነብ ነበር። የቤቱ ባለቤቶችም “ዮሮሺ ደሱ” ወይም “ከኮው ደሱ” በማለት መልስ ይሰጣሉ። ትርጉሙ “ጥሩ ነው፣” ወይም “መልካም ነው፣” ማለት እንደሆነ ተማርን። ሆኖም ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ለመግለጽ እነዚሁኑ ቃላት ስለሚጠቀሙ የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ይኑረው አይኑረው መለየት ይቸግረን ነበር። ትርጉሙን መለየት የሚቻለው የሰውዬውን የድምፅ ቃና በመስማት ወይም ስሜቱን ከፊቱ ላይ በማንበብ ነው። እነዚህን ነገሮች መለየት እስክንችል ድረስ ጊዜ ፈጅቶብናል።
አስደሳች ተሞክሮዎች
ገና ቋንቋውን ለመማር በመታገል ላይ እያለሁ በሚትሱቢሺ ኩባንያ የሠራተኞች መኖሪያ ውስጥ ሳንኳኳ የ20 ዓመት ዕድሜ ካላት ሴት ጋር ተገናኘን። በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጥሩ እድገት በማድረግ በ1966 ተጠመቀች። ከአንድ ዓመት በኋላ አቅኚነት ጀመረች፤ ብዙም ሳይቆይ በልዩ አቅኚነት ተሾመች። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አቅኚነትን አላቋረጠችም። ከወጣትነቷ ጀምሮ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ጊዜዋንና ጉልበቷን እንዴት እንደተጠቀመች ስመለከት ሁልጊዜ መንፈሴ ይነቃቃል።
በተለይ ክርስቲያን ባልሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምቶ መኖር ተፈታታኝ ነው። ቢሆንም እኔ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸውን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ፈታኝ ሁኔታ ተቋቁመውታል። በባሕሉ ምክንያት በጃፓናውያን ቤቶች ውስጥ የማይጠፋውን ውድ የቡድሃና ሥራ 19:18-20
የሺንቶ መሠዊያ አስወግደዋል። የቅርብ ዘመዶች ይህን እርምጃ የሞቱ የቀድሞ አባቶችን ማዋረድ እንደሆነ አድርገው ስለሚቆጥሩት አዳዲስ ጥናቶች መሠዊያዎቹን ለማስወገድ ድፍረት ይጠይቅባቸዋል። በድፍረት የወሰዱት ይህ እርምጃ ከሐሰት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቁሳቁሶች ያቃጠሉትን የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ያስታውሰናል።—የቤት እመቤት የሆነች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከቤተሰቧ ጋር ከቶኪዮ ውጪ ለመኖር እቅድ እንደነበራት አስታውሳለሁ። የመኖሪያ አካባቢ መቀየር የፈለገችው ከአረማዊ የአምልኮ ዕቃዎች የጸዳ ቤት ለማግኘት ብላ ነበር። ፍላጎቷን ለባሏ ስታማክረው በፈቃደኛነት ተባበራት። ስለ እቅዷ በደስታ አማከረችኝ፤ በኋላ ግን በቤት ውስጥ ሰላም ያሰፍናል የሚባልለት አንድ በጣም ትልቅና ውድ ከእብነበረድ የተሠራ ጌጥ እንዳላት አስታወሰች። ከሐሰት አምልኮ ጋር ዝምድና ይኖረዋል የሚል ጥርጣሬ ስለነበራት በመዶሻ እንክትክቱን አውጥታ አስወገደችው።
ይህች ሴትና ሌሎች ሰዎች ከሐሰት አምልኮ ጋር ቁርኝት ያላቸውን በጣም ውድ ዕቃዎች በፈቃደኛነት ሲያስወግዱና ይሖዋን በድፍረት በማገልገል አዲስ ሕይወት ሲጀምሩ መመልከት አብዝቶ የሚክስና አርኪ ተሞክሮ ነው። በጃፓን ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በሚስዮናዊነት ላገለግል በመቻሌ ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ።
በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለ “ተአምር”
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ70 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብዬ ስመለከት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ እንዳለ ተአምር ሆኖ ይሰማኛል። ልጅ ሳለሁ ዓይናፋር ስለነበርኩ ብዙዎች ምንም ነገር ሊሰሙት ስለማይፈልጉት ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር ቀዳሚ ሆኜ መላ ሕይወቴን እገፋለሁ ብዬ ለአፍታ እንኳን አስቤው አላውቅም። ይሁንና እኔ ብቻ ሳልሆን በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች እንደዚህ ሲያደርጉ አይቻለሁ። ደግሞም ይህንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ስላደረጉት በ1958 ጃፓን ስደርስ ከአንድ ሺህ ብዙም የማይበልጥ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር አሁን ከ222, 000 በላይ ሊሆን ችሏል!
ማርታና እኔ መጀመሪያ ጃፓን ስንደርስ ቶኪዮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድንኖር ተመደብን። በ1963 እዚያው ቦታ ላይ ባለ ስድስት ፎቅ የቅርንጫፍ
ቢሮ ሕንፃ ስለተገነባ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በዚያ ስንኖር ቆይተናል። የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች የነበረው ሎይድ ባሪ ኅዳር 1963 ሕንፃው ለይሖዋ የሚወሰንበትን ንግግር ሲሰጥ እኛን ጨምሮ 163 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በወቅቱ በጃፓን ያሉት የምሥክሮች ቁጥር 3, 000 ደርሶ ነበር።የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሲያድግ ማየት እጅግ ደስ ያሰኛል። በ1972 ኑማዙ በምትባል ከተማ አዲስና ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የአስፋፊዎች ቁጥር ከ14, 000 በላይ ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ በ1982 በጃፓን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ከ68, 000 በላይ ሲደርስ ከቶኪዮ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኢቢና በምትባል ከተማ ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ግንባታ ተካሄደ።
በዚያው ወቅት በቶኪዮ እምብርት ላይ የሚገኘው የቀድሞው የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ እድሳት ተደረገለት። ከዚያም እኔንና የረጅም ጊዜ የአገልግሎት ጓደኛዬን ማርታ ሄስን ጨምሮ ጃፓን ውስጥ ለ40 ወይም ለ50 ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ያገለገሉ ከ20 በላይ ሚስዮናውያን መኖሪያ ሆነ። እንዲሁም ባልና ሚስት የሆኑ አንድ ዶክተርና አንዲት ነርስ አብረውን ይኖራሉ። በጤናችን ረገድ አስፈላጊውን ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርጉልናል። በቅርቡ ደግሞ አንዲት ሌላ ነርስ ተጨምራለች። እንዲሁም ክርስቲያን እህቶች ቀን ቀን እየመጡ ነርሷን ይረዳሉ። ሁለት የኢቢና ቤቴል ቤተሰብ አባላት ምግባችንን ለማብሰልና ቤታችንን ለማጽዳት በየተራ ይመጣሉ። በእርግጥም ይሖዋ ጥሩ እንደሆነ አይተናል።—መዝሙር 34:8, 10
የረጅም ጊዜ ሚስዮናውያን የሆንነው ብዙዎቻችን አሁን የምንኖርበት ሕንፃ ለይሖዋ አገልግሎት ከተወሰነ ከ36 ዓመታት በኋላ ባለፈው ኅዳር በሚስዮናዊነት ሕይወቴ ውስጥ ጉልህ ቦታ የምሰጠው አንድ ነገር ተከናወነ። ኅዳር 13, 1999 በኢቢና የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የጃፓን ቅርንጫፍ ያሠራቸው ተጨማሪ ሕንፃዎች ለይሖዋ አገልግሎት ሲወሰኑ ከ37 አገሮች የመጡ የረጅም ጊዜ ምሥክሮችን ጨምሮ 4, 486 ሰዎች የተገኙ ሲሆን እኔም ከእነርሱ መካከል ነበርኩ። በአሁኑ ጊዜ 650 የቤቴል ቤተሰብ አባላት በዚያ ይኖራሉ።
በጣም ዓይናፋር ሳለሁ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከቤት ወደ ቤት መስበክ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ይሖዋ ዓይናፋርነቴን እንዳሸንፍ ረድቶኛል። ማንኛውም ሰው በእርሱ ላይ እስከታመነ ድረስ እንደኔ በጣም ዓይናፋር ቢሆንም እንኳን ይሖዋ እንደሚጠቀምበት ጽኑ እምነት አለኝ። ስለ ይሖዋ አምላክ ምንም የማያውቁ ሰዎች እሱን እንዲያውቁ መርዳት እንዴት ያለ አርኪ ሕይወት ነው!
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክላረንስ ከቤቴል መጥቶ በጎበኘን ጊዜ ከእናቴና ከእርሱ ጋር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክፍላችን አባላት ኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ አቅራቢያ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት መስክ ላይ ሲያጠኑ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተግራ :- እኔ፣ ማርታ ሄስና እናቴ በሃዋይ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተቀኝ:- በቶኪዮ የሚስዮናውያን ቤት የምንኖር አባላት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከታች :- ከረጅም ጊዜ የአገልግሎት ጓደኛዬ ከማርታ ሄስ ጋር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢቢና በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የተሠሩት ተጨማሪ ሕንፃዎች ባለፈው ኅዳር ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰኑ