በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ምክር ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ጥሩ ምክር ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ጥሩ ምክር ከየት ማግኘት ትችላለህ?

በአሁኑ ጊዜ “የምክር አገልግሎት ኢንዱስትሪ” በዓመት በብዙ ቢልዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ንግድ ሆኗል። ሰዎች እርዳታ ይፈልጋሉ። የአእምሮ ጤና ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ሂንትስ ሌይማን እንዲህ ብለዋል:- “[ዛሬ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ] ትምህርት ነክም ሆኑ ማኅበራዊ ጉድለቶች ይታያሉ። ሃይማኖታዊ የሥነ ምግባር ደንቦች ተቀይረዋል። ቤተሰቦች መሠረታቸው ተናግቷል። . . . ከዚህ የተነሳ ሰዎች የሚይዙት ጠፍቷቸው በመደናበር ላይ ናቸው።” ደራሲው ኤሪክ ሚሴል እንዲህ ይላሉ:- “ዱሮ ዱሮ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ለሆኑ ችግሮች እርዳታ ለማግኘት አስማታዊ ኃይል ወዳለው የጎሳ መሪያቸው፣ ቄስ ወይም የቤተሰቡ ሐኪም ይሄዱ የነበሩ ሰዎች አሁን አሁን ለችግሮቻቸው መልስ ለማግኘት ልብ ወለድ ያልሆኑ ራስ አገዝ መጻሕፍትን መመልከት ጀምረዋል።”

የአሜሪካ የሥነ ልቦና ሕክምና ማኅበር እየተስፋፋ ባለው በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ጥናት የሚያካሂድ አንድ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ነበር። ግብረ ኃይሉ፣ ምንም እንኳ “ግለሰቦች ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ሌሎች ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ እገዛ የማድረግ ከፍተኛ አጋጣሚ ቢኖርም . . . ከእነዚህ ፕሮግራሞች ጋር ተያይዘው የሚቀርቡት ማስታወቂያዎችና ስሞች በጣም የተጋነኑና ስሜት ቀስቃሽ ናቸው” ብሏል። አንድ የቶሮንቶ ስታር ጸሐፊ እንዲህ ብሏል:- “በገፍ በሚቀርቡት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ማጭበርበሪያዎች እንዳትታለል ተጠንቀቅ። . . . በተለይ ደግሞ ያለምንም ድካምና መሥዋዕትነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ነገር ማከናወን የምትችልበትን መንገድ ከሚጠቁሙ ራስ አገዝ መጻሕፍት፣ የቴፕ ወይም የቪዲዮ ክሮች ወይም ሴሚናሮች ተጠበቅ።” እርግጥ ነው፣ በችግር ላይ ያሉትን ከልብ መርዳት የሚፈልጉ በጣም በርካታ ሰዎች እንዳሉ አይካድም። የሚያሳዝነው ግን ምንም ዓይነት እውነተኛ እርዳታ ወይም መፍትሔ ሳያቀርቡ ሰዎች ያደረባቸውን የብቸኝነት ስሜትና ስቃይ መጠቀሚያ የሚያደርጉ በርካታ ይሉኝታ ቢስ ሰዎች መኖራቸው ነው።

ከዚህ አንጻር እምነት የሚጣልበት ዋነኛ የእርዳታ ምንጭ ምንድን ነው? ጊዜ የማይሽረው ተግባራዊ ምክር ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

የማይለዋወጥ መመሪያ የሚገኝበት ምንጭ

የ19ኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊ ሰባኪ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር እንዲህ ብለዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስ አቅጣጫህን አቅንተህ መቅዘፍ የሚያስችልህ፣ መርከብህ እንዳይሰጥም የሚረዳህ እንዲሁም ወደቡ የሚገኝበትን ቦታ የሚያመላክትህና ከዐለት ወይም ከተቆለለ አሸዋ ጋር ሳትላተም እንዴት መድረስ እንደምትችል የሚጠቁምህ ከአምላክ የተገኘ ካርታ ነው።” አንድ ሌላ ሰው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሰው የቱንም ያህል በዕድሜ ቢበስል አስተሳሰቡ ከቅዱስ ጽሑፉ የላቀ ሊሆን አይችልም፤ በዕድሜ እየገፋን በሄድን መጠን የመጽሐፉ ስፋትና ጥልቀት እየጨመረ ይሄዳል።” ለዚህ ምንጭ ትኩረት መስጠት ያለብህ ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ መሆኑን ራሱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ የመነጩ ናቸው። (መዝሙር 36:​9) አፈጣጠራችንን ምን ያህል ጠንቅቆ እንደሚያውቅ በመግለጽ መዝሙር 103:​14 እንደሚከተለው በማለት ያስገነዝበናል:- “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ጠቀሜታ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል።

እንዲያውም በየትኛውም ሁኔታ ሥር ብትሆን መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችና መመሪያዎች ይዟል። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንዲህ ይለናል:- “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂ[ዱ]።” (ኢሳይያስ 30:​21) መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችን ፍላጎት በእርግጥ ሊያሟላ ይችላልን? እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ . . . ፍላጎታችንን ያሟላልናል

ጭንቀትን በመቋቋም ረገድ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) ከኢኮኖሚ ችግር፣ ከጾታና በቃል ከሚሰነዘር ጥቃት ወይም ከምንወደው ሰው ሞት ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ስሜታዊ ጭንቀቶች በመቋቋም ረገድ ጸሎት ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷልን? ቀጥሎ የቀረበውን ተሞክሮ ተመልከት።

ጃኪ በሴት ልጅዋ ላይ ስለተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ከሰማች በኋላ እንዲህ ብላለች:- “አንድ ሰው ልጁን ከአደጋ ለማስጣል የሚያስችል አቅም ማጣቱ የሚያሳድርበትን የበደለኛነት ስሜት በቃላት መግለጽ አይቻልም። ካደረብኝ የምሬት፣ የጥላቻና የንዴት ስሜት ጋር መዋጋት ነበረብኝ። እነዚህ ስሜቶች ሕይወቴን ማበላሸት ጀምረው ነበር። ይሖዋ ልቤን እንዲጠብቅልኝ አጥብቄ እፈልግ ነበር።” ፊልጵስዩስ 4:​6, 7ን ደግማ ደጋግማ ካነበበች በኋላ ምክሩን በሥራ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት አደረገች። ጃኪ እንዲህ ትላለች:- “አፍራሽ በሆኑ ስሜቶች ራሴን እንዳልጎዳ ደጋግሜ በመለመን በየቀኑ ጸልያለሁ፤ ይሖዋም የተረጋጋና ደስተኛ ልብ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። በውስጤ እውነተኛ ሰላም እንዳገኘሁ ይሰማኛል።”

አንተም ልትቆጣጠረውም ሆነ መፍትሄ ልታገኝለት ያልቻልከው ጭንቀት የሚያስከትል ሁኔታ ያጋጥምህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንድንጸልይ የሰጠንን ምክር በመከተል ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትቋቋመው ትችላለህ። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ያበረታታናል:- “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል።”​—⁠መዝሙር 37:​5

ማበረታቻ በማግኘት ረገድ። መዝሙራዊው እንደሚከተለው ሲል አድናቆቱን ገልጿል:- “አቤቱ፣ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፣ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።” (መዝሙር 26:​8, 12) ይሖዋን ለማምለክ አዘውትረን አንድ ላይ እንድንሰበሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። በዚህ መልክ አንድ ላይ መሰብሰብ ፍላጎትህን ሊያሟላልህ የሚችለው እንዴት ነው? ሌሎች ምን ያገኙት ነገር አለ?

ቤኪ እንዲህ ትላለች:- “ወላጆቼ ይሖዋን የሚያመልኩ ባለመሆናቸው ለአምላክ ከማቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ በማንኛውም እንቅስቃሴ ስሳተፍ ይቃወሙኛል። በስብሰባዎች መገኘት ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅብኛል።” ቤኪ ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመገኘት ጥረት በማድረጓ ብዙ በረከቶች እንዳገኘች ተሰምቷታል። “ተማሪና በወላጆቼ ሥር ያለሁ እንዲሁም የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኔ መጠን በየዕለቱ የሚደርሱብኝን ጫናዎች መቋቋም እንድችል ስብሰባዎች እምነቴን አጠናክረውልኛል። በመንግሥት አዳራሹ የማገኛቸው ሰዎች በትምህርት ቤት ካሉት ልጆች በጣም ይለያሉ! አሳቢና ሌላውን ለመርዳት የተዘጋጁ ሲሆኑ የምናደርጋቸው ጭውውቶች ደግሞ ምንጊዜም አበረታች ናቸው። እውነተኛ ወዳጆች ናቸው።”

አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወትር አንድ ላይ እንድንሰበሰብ የሚሰጠንን መመሪያ በመከተል ማበረታቻ ለማግኘት ያለንን ፍላጎት ይሖዋ እንዲያሟላልን ማድረግ እንችላለን። የሚከተሉትን የመዝሙራዊው ቃላት እውነተኝነት ማየት የምንችለው እንዲህ ስናደርግ ነው:- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።”​—⁠መዝሙር 46:​1

አርኪና የማያስቆጭ ሥራ በማከናወን ረገድ። መጽሐፍ ቅዱስ “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” ሲል ያሳስባል። (1 ቆሮንቶስ 15:​58) ‘የጌታ ሥራ’ በእርግጥ እርካታ ያስገኛልን? ክርስቲያናዊ አገልግሎት አንድ ዓይነት የማያስቆጭ ውጤት ያስገኛልን?

አሜሊያ የተሰማትን እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ትዳራቸው ሊፈርስ በቋፍ ላይ የነበረ አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቻለሁ። እንዲሁም ሴት ልጅዋ በአሳዛኝ ሁኔታ የተገደለችባትን አንዲት ሴት ረድቻለሁ። ሴትየዋ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እርግጠኛ አለመሆንዋ ከፍተኛ ጭንቀት አስከትሎባት ነበር። በሁለቱም ሁኔታዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋላቸው በሕይወታቸው ውስጥ ሰላምና ተስፋ አስገኝቶላቸዋል። እነሱን የመርዳት ድርሻ በማበርከቴ ከፍተኛ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ።” ስኮት ደግሞ እንዲህ ይላል:- “መስክ አገልግሎት ላይ ጥሩ ተሞክሮ ካጋጠመህ፣ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመርክ ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር አንድ ውጤት ካገኘህ ይህን ነገር ለብዙ ዓመታት ስታወራው ትኖራለህ። ተሞክሮውን ባወራኸው ቁጥር መጀመሪያ የተሰማህ ስሜትና ደስታ ተመልሶ ይመጣልሃል! ከሁሉ የላቀውና ዘላቂ የሆነ ደስታ የሚገኘው ከአገልግሎቱ ነው።”

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ንቁ አገልጋዮች ስለመሆን የሚሰጠውን መመሪያ መከተላቸው አርኪና የማያስቆጭ ሥራ ለማከናወን የነበራቸውን ፍላጎት አሟልቶላቸዋል። አንተም ሌሎችን ስለ አምላክ መንገዶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በማስተማሩ በዚህ ሥራ እንድትካፈል ተጋብዘሃል፤ እንዲህ በማድረግም ራስህን መጥቀም ትችላለህ።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17፤ ማቴዎስ 28:​19, 20

ከአምላክ ቃል ጥቅም ማግኘት

መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎች የያዘ አመኔታ የሚጣልበት ምንጭ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ከመጽሐፉ ጥቅም ለማግኘት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዘወትር ልናነበው፣ ልናጠናውና ልናሰላስልበት ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር።” (1 ጢሞቴዎስ 4:​15፤ ዘዳግም 11:​18-21) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚገኘው መሠረት ምክሩን በሥራ ለማዋል ጥረት ካደረግህ ስኬታማ እንደምትሆን ዋስትና ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በእግዚአብሔር ታመን፣ . . . በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል አርኪና አስደሳች ሕይወት ያስገኛል