በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታይዋን የሩዝ ማሳዎች ውስጥ ምሥራቹን ማወጅ

በታይዋን የሩዝ ማሳዎች ውስጥ ምሥራቹን ማወጅ

ከሚያምኑት ወገን ነን

በታይዋን የሩዝ ማሳዎች ውስጥ ምሥራቹን ማወጅ

ታይዋን አብዛኛውን ጊዜ የምታገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በዓመት ሁለት ጊዜ ጥሩ የሩዝ ምርት ለመሰብሰብ ያስችላታል። አንዳንድ ጊዜ ግን ዝናቡ መምጣት በሚገባው ወቅት ላይ ስለማይመጣ ቡቃያዎቹ ይደርቃሉ። በዚህ ጊዜ ገበሬው ተስፋ ይቆርጥ ይሆን? የለም፣ ተስፋ አይቆርጥም። ጽናት እንደሚያስፈልግ ስለሚያውቅ አዳዲስ ቡቃያዎች አብቅሎ ማሳው ላይ ይተክላል። ከዚያም ሁኔታዎች ከተሻሻሉ ጥሩ ምርት መሰብሰብ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ ዘር የመዝራቱና መከር የመሰብሰቡ ሥራ ከዚህ ጋር በጣም ይመሳሰላል።

በመንፈሳዊው መከር የመሰብሰብ ሥራ መጽናት

ባለፉት ዓመታት በታይዋን የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ብዙም ምርታማ በማይመስሉት የተወሰኑ ቦታዎች ቅዱስ ጽሑፋዊውን የእውነት ዘር ለመዝራትና መከር ለመሰብሰብ ጠንክረው ሠርተዋል። ለምሳሌ፣ ሚል-ሊ በተባለው ግዛት አልፎ አልፎ ምስክርነት ለመስጠት ጥረት የተደረገ ሲሆን የተገኘው ምላሽ ግን በጣም አነስተኛ ነበር። ስለዚህ በ1973 ልዩ አቅኚ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን በዚያ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በመጀመሪያ ጥቂት ሰዎች ለምሥራቹ ፍላጎት አሳይተው የነበረ ቢሆንም ይህ ፍላጎታቸው ብዙም ሳይቆይ ቀዘቀዘ። በመሆኑም እነዚህ ሁለት ልዩ አቅኚዎች ሌላ ቦታ እንዲያገለግሉ ተመደቡ።

በ1991 ሁለት ልዩ አቅኚ እህቶች በዚህ ቦታ እንዲያገለግሉ ቢመደቡም አካባቢው ለመንፈሳዊ እድገት አመቺ እንዳልሆነ ሁኔታዎች ግልጽ አድርገው ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልዩ አቅኚዎቹ ይበልጥ ፍሬያማ ይሆናሉ ተብለው ወደታሰቡ ክልሎች በመዛወራቸው አካባቢው ለተወሰነ ጊዜ ሳይሠራበት ቆይቷል።

በአዲስ መልክ የተደረጉ ጥረቶች ጥሩ ውጤት አስገኙ

በመስከረም 1998 ታይዋን ውስጥ ለየትኛውም ጉባኤ ካልተመደቡት ሰፋፊ ክልሎች መካከል ይበልጥ ፍሬያማ ሊሆኑ የሚችሉትን ቦታዎች ለማግኘት ጥረት መደረግ እንዳለበት ተወሰነ። ይህንን እንዴት ማከናወን ይቻላል? ወደ 40 የሚጠጉ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎችን ይበልጥ ሕዝብ በሚበዛባቸውና ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ ክልሎች ውስጥ እንዲያገለግሉ በማድረግ ይህን ማከናወን ተችሏል።

ለዚህ ዘመቻ ከተመረጡት ክልሎች መካከል ሚል-ሊ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ተዋሳኝ ከተሞች ይገኙበታል። አራት ነጠላ እህቶች ለሦስት ወራት ያህል ክልሎቹን እንዲሞክሩአቸው የተመደቡ ሲሆን ቦታው ከደረሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዳገኙ የሚገልጽ በአድናቆት የተሞላ ሪፖርት ጽፈው ነበር። የሦስት ወር የአቅኚነት ጊዜያቸውን በጨረሱበት ወቅት ብዙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ከመቻላቸውም በላይ በአቅራቢያው በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ በሚያገለግል አንድ ወንድም ረዳትነት የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ለሟቋቋም በቅተዋል።

ከእነዚህ እህቶች መካከል ሦስቱ እዚያው ቆይተው ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ ያሉትን “ቡቃያዎች” ለመንከባከብ እንደሚፈልጉ ግልጽ በማድረጋቸው ሁለቱ ቋሚ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ሲሾሙ ሦስተኛዋ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገሏን ቀጥላለች። እነዚህን እህቶች ለመርዳት ሲል አንድ ሽማግሌ የሆነ ወንድም በአቅራቢያው ከሚገኝ ጉባኤ ወደ እነርሱ ተዛወረ። ከ60 የሚበልጡ ሰዎች በዚያ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ በቦታው የተገኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህ ጨቅላ ቡድን በርከት ያሉ የመጽሐፍ ጥናት ስብሰባዎችን ጨምሮ እሁድ እሁድ የሚደረጉትን ስብሰባዎች በቋሚነት እንዲካሄድ በአቅራቢያው የሚገኘው ጉባኤ እየረዳው ነው። በቅርቡም በዚህ ቦታ ላይ አንድ አዲስ ጉባኤ ይመሰረት ይሆናል።

ጽናት በሌሎቹ የታይዋን ከተሞች በረከት አስገኘ

ሌሎች ቦታዎችም በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ ሰጥተዋል። ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች በሠሩበት በደሴቲቱ ሰሜናዊ ምሥራቅ በሚገኘው የኢ-ላን ግዛት አንድ አዲስ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ቡድን ተቋቁሟል።

አንዲት ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ እህት በምሽት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አንድ ወጣት አገኘችና የጉባኤ ስብሰባዎችን ዝርዝር የያዘ የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት አሳየችው። ወዲያውኑ “ነገ ማታ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት እችላለሁ? መገኘት ከቻልኩስ መልበስ ያለብኝ ልብስ ምን ዓይነት ነው?” ሲል ጠየቃት። ይህች ልዩ አቅኚ እህት ፍላጎት ላላቸው ስምንት ሰዎች በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ላይ ስትሆን አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም የመጠመቅ ግብ በመያዝ በቅርቡ የምሥራቹ አስፋፊዎች ለመሆን አስበዋል።

በዚሁ ከተማ የምትኖር አንዲት ሴት ለብዙ ዓመታት አዘውትራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ብትሄድም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምራት ሰው አላገኘችም። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ስለሚቻልበት ዝግጅት ስትሰማ አጋጣሚውን ተጠቀመችበት። ትምህርቱን አስቀድማ እንድትዘጋጅ ማበረታቻ ተሰጣት። ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዋ የመጀመሪያውን ጥናት ለመምራት ስትመጣ ሴትዮዋ ደብተር በመግዛትና በምታጠናው ጽሑፍ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ደብተሩ ላይ በመጻፍ “የቤት ሥራዋን” ሠርታ እንደጠበቀቻት ተገነዘበች። የእያንዳንዱን ጥያቄ መልስ እንዲሁም ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሰውን ጥቅሶች በሙሉ ደብተሯ ላይ ከመጻፏም በላይ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ክፍሎች አስቀድማ ተዘጋጅታቸው ነበር!

በመካከለኛው ታይዋን በሚገኘው ዶንግሺ በተባለው ከተማም ተመሳሳይ ውጤቶች ተገኝተዋል። ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎቹ ባገለገሉባቸው ሦስት ወራት ውስጥ ከ2, 000 የሚበልጡ ብሮሹሮች ከማበርከታቸውም በላይ ሦስተኛው ወር ላይ 16 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርተው ነበር። መስከረም 21, 1999 መካከለኛውን ታይዋን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ከተማው በከፍተኛ ሁኔታ ወድሞ ነበር። ያም ሆኖ ግን የተወሰኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በአቅራቢያቸው ያለው ጉባኤ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የአንድ ሰዓት ያህል ጉዞ ማድረግ ቢያስፈልጋቸውም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። አዎን፣ የተሻለ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ምርት ለማግኘት መጽናት ያስፈልጋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቻይና

የታይዋን የባሕር ወሽመጥ

ታይዋን

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.