የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 የታወቀ አንድ መሲሐዊ ትንቢት ይዟል። ቁጥር 10 “እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ” ይላል። ይህ ምን ማለት ነው?
በኢሳይያስ 53:10 ላይ ለምን ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል መረዳት አይከብድም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሩኅሩኅና አዛኝ የሆነው አምላካችን ማንንም ሰው በማድቀቅ ወይም እንዲታመም በማድረግ ይደሰታል የሚል አስተሳሰብ የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ንጹሐን ሰዎችን በማሠቃየት እንደማይደሰት እርግጠኞች እንድንሆን የሚያስችል ማስረጃ ይሰጠናል። (ዘዳግም 32:4፤ ኤርምያስ 7:30, 31) ባለፉት መቶ ዘመናት ይሖዋ ከጥበቡና ከፍቅሩ ጋር በማይቃረኑ ምክንያቶች አንዳንድ ጊዜ መከራ እንዲኖር ፈቅዶ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ውድ ልጁ ኢየሱስ እንዲሠቃይ እንዳላደረገ የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ይህ ጥቅስ በእርግጥ እየተናገረ ያለው ምንድን ነው?
“ፈቃድ” የሚለው ቃል የገባባቸውን ሁለት ቦታዎች በማጤን ሙሉውን ጥቅስ ማንበባችን ፍሬ ነገሩን እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። ኢሳይያስ 53:10 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ። ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።”
በጥቅሱ መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ‘የእግዚአብሔር ፈቃድ’ ይሖዋ ዓላማውን በመንግሥቱ አማካኝነት በመፈጸሙ ላይ ያተኮረ መሆኑን አጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያሳያል። ይሖዋ ይህን ማከናወኑ ልዕልናውን ከማረጋገጡም በላይ የወረስነውን ኃጢአት ታዛዥ ከሆኑ የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ያስችላል። (1 ዜና መዋዕል 29:11፤ መዝሙር 83:18፤ ሥራ 4:24፤ ዕብራውያን 2:14, 15፤ 1 ዮሐንስ 3:8) ለዚህ ሁሉ ቁልፉ የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ መምጣትና ቤዛዊ መሥዋዕቱን ማቅረብ የነበረበት መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ በዚህ ሂደት ላይ ኢየሱስ መከራ ተቀብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን” እንደተማረ ይነግረናል። ስለዚህ ኢየሱስ ከደረሰበት መከራ ጥቅም አግኝቷል።—ዕብራውያን 5:7-9
ኢየሱስ ሊከተለው ያለው በዓይነቱ የላቀ አኗኗር መከራ እንደሚያስከትልበት በቅድሚያ ያውቅ ነበር። ይህም “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፣ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” ብሎ በተናገረበት በዮሐንስ 12:23, 24 ላይ በግልጽ ተመልክቷል። አዎን፣ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ የጸና አቋሙን መጠበቅ እንዳለበት አውቋል። ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አሁን ነፍሴ ታውካለች፣ ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው። ስለዚህም:- አከበርሁት ደግም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።”—ዮሐንስ 12:27, 28፤ ማቴዎስ 26:38, 39
ኢሳይያስ 53:10ን መረዳት ያለብን በዚህ አገባቡ ነው። ይሖዋ ልጁ የሚደርስበት ሥቃይ መድቀቅን እንደሚጨምር በሚገባ ያውቅ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በፍጻሜው የሚገኘውን አስደናቂና ታላቅ ውጤት በአእምሮው በመያዝ ኢየሱስ እንዲሠቃይ ፈቅዷል። ከዚህ አንጻር ይሖዋ የመሲሑን መድቀቅ ወይም ‘ያደቅቀው ዘንድ ፈቅዷል።’ ኢየሱስም ቢሆን ማድረግ የሚችለውን ነገር በፈቃደኝነት አድርጓል። በእርግጥም በኢሳይያስ 53:10 መደምደሚያ ላይ እንደተገለጸው ‘የይሖዋ ፈቃድ በእጁ ተከናውኗል።’