በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ይኑራችሁ!

በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ይኑራችሁ!

በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ይኑራችሁ!

“የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ [“እጠባበቃለሁ፣” የ1980 ትርጉም ]፤ አምላኬም ይሰማኛል።”​—⁠ሚክያስ 7:​7

1, 2. (ሀ) እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ የተሳሳተ አስተሳሰብ መያዛቸው የጎዳቸው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ትክክለኛ አስተሳሰብ ሳያዳብር ቢቀር ምን ሊደርስበት ይችላል?

 በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ በርካታ ነገሮች አዎንታዊ ወይም አሉታዊ በሆነ መንገድ ሊታዩ ይችላሉ። ጉዳዩ የተመካው በአስተሳሰባችን ላይ ነው። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ መና ያገኙ ነበር። በዚያ ጠፍ ምድር ይሖዋ በዚህ መንገድ ይመግባቸው የነበረ መሆኑ በጥልቅ እንዲያመሰግኑት ሊገፋፋቸው ይገባ ነበር። እንዲህ አድርገው ቢሆን ኖሮ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዳላቸው የሚያሳይ ይሆን ነበር። ከዚያ ይልቅ በግብፅ የነበረውን ብዙ ዓይነት ምግብ በማስታወስ መናው የሚሰለች ምግብ እንደሆነ አድርገው በመናገር አማረሩ። ይህ እንዴት ያለ አፍራሽ አስተሳሰብ ነው!​—⁠ዘኁልቁ 11:​4-6

2 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ ክርስቲያን አስተሳሰቡ ለነገሮች ያለውን አመለካከት ብሩህ ሊያደርገው አሊያም ሊያጨልምበት ይችላል። አንድ ክርስቲያን ትክክለኛ አስተሳሰብ ከሌለው በቀላሉ ደስታውን ሊያጣ ይችላል። ይህ ደግሞ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ምክንያቱም ነህምያ እንዳለው “የእግዚአብሔርም ደስታ [ኃይላችን] ነው።” (ነህምያ 8:​10) አዎንታዊና አስደሳች አስተሳሰብ ጠንካራ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል።​—⁠ሮሜ 15:​13፤ ፊልጵስዩስ 1:​25

3. ኤርምያስ በአስቸጋሪ ጊዜያት ትክክለኛ አስተሳሰብ መያዙ የረዳው እንዴት ነው?

3 ኤርምያስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ይኖር የነበረ ቢሆንም አዎንታዊ አስተሳሰብ እንደነበረው አሳይቷል። ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ እንደምትጠፋ የሚገልጸውን አስፈሪ መልእክት በሚመሠክርበት ጊዜ እንኳ አዎንታዊ ገጽታዎችን መመልከት ችሏል። ይሖዋ እስራኤልን አይረሳም፣ ሕዝቡንም ከጥፋት ያድናል። ኤርምያስ በሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ላይ “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው” በማለት ጽፏል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:​22, 23) በታሪክ ዘመናት ሁሉ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች አዎንታዊ አልፎ ተርፎም አስደሳች አስተሳሰብ ይዘው ኖረዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 7:​4፤ 1 ተሰሎንቄ 1:​6፤ ያዕቆብ 1:​2

4. ኢየሱስ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነበረው? ይህስ የረዳው እንዴት ነው?

4 ኤርምያስ ከኖረበት ዘመን ስድስት መቶ ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሱስ የነበረው ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲጸና ረድቶታል። “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና” የሚል እናነባለን። (ዕብራውያን 12:​2) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ መሰቃየትን ጨምሮ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ወይም ስደት ቢደርስበት አእምሮው ያተኮረው ‘በፊቱ ባለው ደስታ’ ላይ ነበር። ይህ ደስታ የይሖዋን ሉዓላዊነት የማረጋገጥና ስሙን የማስቀደስ እንዲሁም ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ወደፊት ታላላቅ በረከቶችን እንዲያገኙ የማድረግ መብት ነው።

በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ይኑራችሁ

5. በትዕግሥት መጠበቅ ለነገሮች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ሊረዳን እንደሚችል የሚያሳየው የትኛው ዓይነተኛ ሁኔታ ነው?

5 ኢየሱስ የነበረውን ዓይነት አስተሳሰብ ካዳበርን ነገሮች እኛ በፈለግነው መንገድና ጊዜ ሳይፈጸሙ ቢቀሩ እንኳ ከይሖዋ የሚገኘውን ደስታ አናጣም። ነቢዩ ሚክያስ “እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፣ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ [“እጠባበቃለሁ፣” የ1980 ትርጉም ]” ብሏል። (ሚክያስ 7:​7፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:​21) እኛም ብንሆን በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ልናሳይ እንችላለን። እንዴት? በብዙ መንገዶች ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ ወንድም ስህተት እንደፈጸመና አፋጣኝ የሆነ እርምት ሊሰጠው እንደሚገባ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ካለን ‘በእርግጥ ግለሰቡ ስህተት ሠርቷል ወይስ የተሳሳትኩት እኔ እሆን? ስህተት ሠርቶም ከሆነ ይሖዋ ሁኔታውን የፈቀደው ግለሰቡ ማሻሻያ ሊያደርግ እንደሚችልና አፋጣኝ የሆነ እርምት መውሰድ እንደማያስፈልግ ስለተሰማው ይሆን?’ ብለን እንድናስብ ይረዳናል።

6. በግል ከደረሰበት ችግር ጋር እየታገለ ያለ አንድ ሰው በትዕግሥት የመጠበቅ ባሕርይ መያዙ የሚረዳው እንዴት ነው?

6 በግል በደረሰብን ችግር የምንጨነቅ ብንሆን ወይም የምንታገለው አንድ ዓይነት ድክመት ቢኖርብን በትዕግሥት የመጠባበቅ ባሕርይ መኮትኮት አስፈላጊ ይሆናል። ይሖዋ እንዲረዳን ጠየቅነው እንበል። ሆኖም ችግሩ አልተወገደም። ታዲያ ምን እናደርጋለን? ችግሩን ለማስወገድ ጠንክረን መሥራታችንን መቀጠልና “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፣ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፍትላችሁማል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ማመን ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:​9) ጸሎትህን ሳታቋርጥ ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባበቅ። ይሖዋ ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው ጊዜና በራሱ መንገድ ለጸሎትህ መልስ ይሰጥሃል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​17

7. በትዕግሥት የመጠበቅ ባሕርይ ቀስ በቀስ እየጠራ ለሚሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እያገኙ በሄዱ መጠን በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ያለን ግንዛቤ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ይሄዳል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አንድ ትምህርት ማብራሪያ ሳይሰጥበት እንደዘገየ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። እኛ በፈለግነው ጊዜ ማብራሪያ ሳይሰጥበት ቢቀር በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች ነን? ይሖዋ “የክርስቶስን ምሥጢር” መግለጥ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ቀስ በቀስ 4, 000 በሚያህሉ ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ አስታውስ። (ኤፌሶን 3:​3-6) ታዲያ ትዕግሥታችን የሚሟጠጥበት ምን ምክንያት አለ? “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለይሖዋ ሕዝብ “ምግባቸውን በጊዜው” እንዲሰጥ የተሾመ መሆኑን እንጠራጠራለን? (ማቴዎስ 24:​45፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሁሉም ነገር ሙሉ በሙሉ ግልጽ አልተደረገም ብለን አምላካዊ ደስታችንን ለምን እናጣለን? “ምሥጢሩ” የሚገለጥበትን ጊዜና መንገድ የሚወስነው ይሖዋ መሆኑን አስታውስ።​—⁠አሞፅ 3:​7

8. የይሖዋ ትዕግሥት ለብዙዎች ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

8 አንዳንዶች ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት ካገለገሉ በኋላ በሕይወት ቆይተው ‘ታላቁንና የሚያስፈራውን የእግዚአብሔር ቀን’ ማየት መቻላቸውን ሊጠራጠሩና ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። (ኢዩኤል 2:​30, 31) ሆኖም ሁኔታውን አዎንታዊ ከሆነ አቅጣጫ የሚመለከቱ ከሆነ ሊበረታቱ ይችላሉ። ጴጥሮስ “የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ” በማለት መክሯል። (2 ጴጥሮስ 3:​15) የይሖዋ ትዕግሥት በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ተጨማሪ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ አስችሏቸዋል። ይህ አያስደስትም? ከዚህም በላይ ይሖዋ ረዘም ላለ ጊዜ በመታገሱ እኛም “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ [የራሳችንን] መዳን” ለመፈጸም ተጨማሪ ጊዜ እናገኛለን።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​12፤ 2 ጴጥሮስ 3:​11, 12

9. በይሖዋ አገልግሎት ልናደርግ የምንችለው ነገር ውስን በሚሆንበት ጊዜ በትዕግሥት የመጠበቅ ባሕርይ ሁኔታውን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

9 በትዕግሥት የምንጠባበቅ ከሆነ በተቃውሞ፣ በህመም፣ በእድሜ መግፋት ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ በመንግሥቱ አገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ ውስን በሚሆንበት ጊዜ ተስፋ አንቆርጥም። ይሖዋ በሙሉ ልብ እንድናገለግለው ይጠብቅብናል። (ሮሜ 12:​1) ይሁን እንጂ ‘ለችግረኛና ለምስኪን የሚራራው’ የአምላክ ልጅም ሆነ ይሖዋ ከአቅማችን በላይ አይጠብቁብንም። (መዝሙር 72:​13) ስለዚህ ሁኔታዎች በዚህ የነገሮች ሥርዓት ወይም በሚመጣው ሥርዓት እስኪስተካከሉ ድረስ በትዕግሥት እየተጠባበቅን የአቅማችንን ያህል እንድንሠራ እንበረታታለን። “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ” እንዳልሆነ አስታውስ።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

10. አንድ ሰው በትዕግሥት የመጠበቅን ባሕርይ በመያዝ የትኛውን አምላካዊ ያልሆነ ጠባይ ማስወገድ ይችላል? አብራራ።

10 በተጨማሪም በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ትዕቢተኞች እንዳንሆን ይረዳናል። አንዳንዶች ከሃዲ የሆኑት በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረታቸው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወይም ድርጅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ የሚያሻቸው ነገሮች እንዳሉ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ መንፈስ ታማኝና ልባም ባሪያ ማስተካከያ እንዲያደርግ የሚያነሳሳው ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እንጂ እኛ አስፈላጊ ሆኖ በተሰማን ጊዜ እንዳልሆነ አልተገነዘቡም። እንዲሁም የሚደረገው ማንኛውም ማስተካከያ ከእኛ የግል አስተሳሰብ ጋር ሳይሆን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። ከሃዲዎች የትዕቢት መንፈስ አስተሳሰባቸውን እንዲያዛባባቸውና እንዲያደናቅፋቸው ፈቅደዋል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የነበረውን አስተሳሰብ ኮርጀው ቢሆን ኖሮ ደስታቸውን እንደጠበቁ ከይሖዋ ሕዝቦች ሳይለዩ መኖር ይችሉ ነበር።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​5-8

11. በትዕግሥት የምንጠብቅበትን ጊዜ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ይህንንስ የምናደርገው የእነማንን ምሳሌ በመከተል ነው?

11 እርግጥ ነው፣ በትዕግሥት መጠባበቅ ሰነፍ ወይም ሥራ ፈት መሆን ማለት አይደለም። የምንሠራቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ታማኞቹ ነቢያትና ሌላው ቀርቶ መላእክት እንኳ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያሳዩትን ዓይነት ከፍተኛ ጉጉት ማሳየት ይኖርብናል። ጴጥሮስ እንዲህ ስላለው መንፈሳዊ ፍላጎት ሲናገር “ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ . . . ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 1:​10-12) የግል ጥናት ማድረግ ብቻ ሳይሆን አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ጸሎት የግድ አስፈላጊ ናቸው። (ያዕቆብ 4:​8) አዘውትረው መንፈሳዊ ምግብ በመመገብና ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር በመሰብሰብ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሁሉ ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው ያሳያሉ።​—⁠ማቴዎስ 5:​3

ትክክለኛ አመለካከት ይኑራችሁ

12. (ሀ) አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ነፃነት ማግኘት ፈልገው ነበር? (ለ) የሰው ልጆች የአዳምንና የሔዋንን ጎዳና መከተላቸው ምን ውጤት አስከተለባቸው?

12 አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በፈጠረ ጊዜ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት አልሰጣቸውም ነበር። (ዘፍጥረት 2:​16, 17) አዳምና ሔዋን ከአምላክ አመራር ነፃ መውጣት ፈለጉ። ይህም በአሁኑ ጊዜ በአካባቢያችን የምናያቸውን ሁኔታዎች አስከትሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 5:​12) ከአዳም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀው የሰው ልጅ የስድስት ሺህ ዓመት ታሪክ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” የሚሉትን የኤርምያስ ቃላት እውነተኝነት አረጋግጧል። (ኤርምያስ 10:​23) የኤርምያስን ቃላት እውነተኝነት ማመን ሐቁን የመቀበል እንጂ ተስፋ ቆርጦ እጅ የመስጠት ጉዳይ አይደለም። በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት የሰው ልጅ ከአምላክ ርቆ ራሱን በማስተዳደሩ ምክንያት ‘ሰው ሰውን ለጉዳቱ እንደገዛው’ ለመረዳት ያስችለናል።​—⁠መክብብ 8:​9 NW

13. የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጆች ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸውን ነገሮች በተመለከተ ያላቸው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?

13 የሰው ዘር ካለበት ሁኔታ አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ማከናወን የሚቻለው ነገር ውስን እንደሆነ ይገነዘባሉ። አዎንታዊ አስተሳሰብ ደስታችንን እንድንጠብቅ ሊረዳን ቢችልም ለሁሉም ችግር መፍትሔ ያስገኛል ማለት አይደለም። በ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አንድ አሜሪካዊ ቄስ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለው ኃይል የተባለ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ አንድ መጽሐፍ አሳትመው ነበር። መጽሐፉ ብዙዎቹን መሰናክሎች አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ማሸነፍ እንደሚቻል ሐሳብ ይሰጣል። በእርግጥም አዎንታዊ አስተሳሰብ የሚደነቅ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ እውቀት፣ ችሎታ፣ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚኖረን አቅምና ሌሎች በርካታ ነገሮች በግለሰብ ደረጃ ልናከናውነው የምንችለውን ነገር ውስን እንደሚያደርጉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ሰዎች ምንም ያህል አዎንታዊ አስተሳሰብ ቢኖራቸው ያሉት ችግሮች ከአቅማቸው በላይ ናቸው!

14. የይሖዋ ምሥክሮች አፍራሽ አመለካከት አላቸውን? አብራራ።

14 የይሖዋ ምሥክሮች በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ አመለካከት በመያዛቸው ምክንያት አንዳንድ ጊዜ አፍራሽ አመለካከት እንዳላቸው ተደርገው ይወነጀላሉ። ከዚያ ይልቅ የሰው ዘሮችን የወደፊት ዕጣ ለዘለቄታው ሊያሻሽል ስለሚችለው ብቸኛ አካል ለሰዎች ለመናገር ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። በዚህም ረገድ ክርስቶስ የነበረውን አስተሳሰብ ይኮርጃሉ። (ሮሜ 15:​2) እንዲሁም ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው በመርዳቱ ሥራ የተጠመዱ ናቸው። ይዋል ይደር እንጂ ይህ ሥራቸው የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ያውቃሉ።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​16

15. የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ የግለሰቦችን ሕይወት የሚያሻሽለው እንዴት ነው?

15 የይሖዋ ምሥክሮች በዙሪያቸው ያሉትን ማኅበራዊ ችግሮች በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ርካሽ ድርጊቶችን ችላ ብለው አያልፉም። ፍላጎት ያሳየ አንድ ግለሰብ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት ለውጥ ያደርጋል። ይህም ብዙውን ጊዜ አምላክን የማያስደስቱ ሱስ የሚያስይዙ መጥፎ ምግባሮችን ማሸነፍ ይጠይቅበታል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9-11) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ከስካር፣ ከአደገኛ ዕፆች ሱሰኝነት፣ ከጾታ ብልግናና ከቁማር ሱሰኝነት እንዲላቀቁ ረድተዋል። እነዚህ ለውጥ ያደረጉ ሰዎች ኃላፊነት ተሰምቷቸው ሐቀኝነት በተሞላበት መንገድ ቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብን ተምረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ግለሰቦችና ቤተሰቦች በዚህ መንገድ እርዳታ ሲያገኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖረው ችግር ይቀንሳል። የዕፅ ሱሰኞች ቁጥር፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸመው የኃይል ድርጊትና የመሳሰሉት ችግሮች ይቀንሳሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው ሕግ አክባሪ ዜጎች በመሆንና ሌሎች ሰዎችም አኗኗራቸውን በተሻለ መንገድ እንዲቀይሩ በመርዳት ከማኅበራዊ ችግሮች ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውኑ ድርጅቶች ያለባቸው ጫና እንዲቃለል ያደርጋሉ።

16. የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

16 የይሖዋ ምሥክሮች የዓለምን የሥነ ምግባር ሁኔታ ቀይረዋል? ባለፉት አሥር ዓመታት 3, 800, 000 ገደማ የነበረው የምሥክሮቹ ቁጥር ወደ 6, 000, 000 ገደማ ከፍ ብሏል። ጭማሪው 2, 200, 000 ያህል ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ክርስቲያን በሆኑበት ጊዜ ቀደም ሲል የነበሩባቸውን መጥፎ ልማዶች አቁመዋል። የብዙዎች ሕይወት ተሻሽሏል! ያም ሆኖ ግን ይህ ቁጥር ባለፉት ተመሳሳይ ዓመታት በ875, 000, 000 እድገት ካሳየው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው! የይሖዋ ምሥክሮች በሕይወት መንገድ ላይ ለመጓዝ የሚመርጡት ሰዎች ቁጥር ጥቂት መሆኑን የሚያውቁ ቢሆንም አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን መርዳት አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል። (ማቴዎስ 7:​13, 14) ምሥክሮቹ አምላክ ብቻ ሊያመጣ የሚችለውን በመላው ዓለም ላይ የተሻለ ለውጥ የሚመጣበትን ጊዜ በትዕግሥት ሲጠባበቁ በአብዛኛው መጀመሪያ ላይ በቅን ልቦና በመነሳሳት በሚካሄዱትና በኋላ ግን እንደ ታሰቡት ሳይሆኑ በሚቀሩት እንዲያውም በብጥብጥ በሚቋጩት የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አይካፈሉም።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

17. ኢየሱስ በዙሪያው የነበሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን አደረገ? ሆኖም ምን አላደረገም?

17 የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጎዳና በሚከተሉበት ጊዜ ኢየሱስ ምድር ሳለ የነበረውን ዓይነት በይሖዋ ላይ የመታመን መንፈስ ያሳያሉ። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎችን በመፈወስ ተዓምራት ፈጽሟል። (ሉቃስ 6:​17-19) የሞቱትን እንኳ ሳይቀር አስነስቷል። (ሉቃስ 7:​11-15፤ 8:​49-56) ሆኖም በሽታን ከናካቴው አላስወገደም ወይም ጠላት የሆነውን ሞትን ድል አላደረገም። ይህን ለማድረግ አምላክ የወሰነው ጊዜ እንዳልደረሰ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን የነበሩትን የላቁ ችሎታዎች በመጠቀም ሥር የሰደዱ በርካታ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለማስወገድ ብዙ ነገር ማድረግ ይችል ነበር። በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ሥልጣን ይዞ በዚህ መንገድ እርምጃ እንዲወስድ የፈለጉ ይመስላል። ሆኖም ኢየሱስ ሐሳባቸውን አልተቀበለውም። እንዲህ እናነባለን:- “ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ:- ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።”​—⁠ዮሐንስ 6:​14, 15

18. (ሀ) ኢየሱስ ሁልጊዜ በትዕግሥት የመጠበቅ መንፈስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ እንቅስቃሴ ከ1914 ጀምሮ የተለወጠው እንዴት ነው?

18 ኢየሱስ የንግሥና ሥልጣኑን የሚቀበልበትና በሁሉም ቦታ ለሚገኙ ሰዎች የፈውስ ሥራ የሚያከናውንበት ጊዜ እንዳልደረሰ ያውቅ ስለነበር በፖለቲካ ጉዳዮችም ሆነ በማኅበራዊ ግልጋሎቶች ውስጥ ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆነም። የማይሞት መንፈሳዊ አካል ይዞ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ እንኳ ሳይቀር እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ይሖዋ የወሰነውን ጊዜ በትዕግሥት ለመጠባበቅ ፈቃደኛ ነበር። (መዝሙር 110:​1፤ ሥራ 2:​34, 35) ይሁን እንጂ በ1914 በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ከጨበጠ ወዲህ ‘ድል እየነሣና ድል ለመንሣት’ ወጥቷል። (ራእይ 6:​2፤ 12:​10) ሌሎች ክርስቲያን ነን ባዮች ስለ መንግሥቱ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ለመቀጠል ቢመርጡም እኛ ግን ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ተገዥ ለመሆን በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

በትዕግሥት መጠበቅ​—⁠ደስታ ያስገኛል ወይስ ለብስጭት ይዳርጋል?

19. በትዕግሥት መጠበቅ ‘ልብን ሊያሳዝን’ የሚችለው መቼ ነው? የደስታ ምንጭ የሚሆነውስ መቼ ነው?

19 ሰሎሞን አንድን ነገር መጠባበቅ ብስጭት ሊያስከትል እንደሚችል ያውቅ ነበር። “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 13:​12) በእርግጥም፣ አንድ ሰው መሠረት በሌለው ነገር ላይ ተስፋውን ቢጥል የጠበቀው ነገር ሳይሆን በመቅረቱ ልቡ በሃዘን ሊዋጥ ይችላል። ይሁን እንጂ የሰርግ ቀንን፣ ልጅ የሚወለድበትን ጊዜ ወይም ከምንወደው ሰው ጋር እንደ ገና የምንገናኝበትን ጊዜ የመሰሉ አስደሳች የሆኑ ወቅቶችን የምንጠባበቀው በደስታ ስሜት ተውጠን ነው። ጊዜውን በጥበብ በመጠቀም ዝግጅት እያደረግን የምንጠባበቅ ከሆነ ደግሞ ደስታችን ይበልጥ ከፍ ያለ ይሆናል።

20. (ሀ) ወደፊት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ሆነን የምንጠብቃቸው አስደናቂ ክንውኖች ምንድን ናቸው? (ለ) የይሖዋ ዓላማ የሚፈጸምበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

20 ተስፋ ያደረግነው ነገር መቼ እንደሚፈጸም በትክክል ባናውቅም እንኳ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት ኖሮን የምንጠባበቅ ከሆነ ‘ልባችን በሐዘን አይዋጥም።’ የአምላክ ታማኝ አምላኪዎች የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በጣም እንደተቃረበ ያውቃሉ። ሞትና በሽታ የሚወገዱበትን ጊዜ እንደሚያዩ እርግጠኞች ናቸው። የሚያፈቅሯቸውን በሞት የተለዩአቸውን ሰዎች ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን የሚነሱበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉትና በደስታ ስሜት ተውጠው ይጠባበቃሉ። (ራእይ 20:​1-3, 6፤ 21:​3, 4) ከፍተኛ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ በደረሰበት በአሁኑ ዘመን ምድር ገነት የምትሆንበትን ጊዜ የማየት የተረጋገጠ ተስፋ አላቸው። (ኢሳይያስ 35:​1, 2, 7) እንግዲያው ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ የበዛልን’ ሆነን ተስፋው እስከሚፈጸም ድረስ የሚኖረውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀማችን ምንኛ ጥበብ ነው! (1 ቆሮንቶስ 15:​58) መንፈሳዊ ምግብ መመገባችሁን ቀጥሉ። ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ይበልጥ አጎልብቱት። ይሖዋን ለማገልገል ልባቸው የሚገፋፋቸውን ሰዎች ለማግኘት ጥረት አድርጉ። የእምነት ባልደረቦቻችሁን አበረታቱ። ይሖዋ ገና ወደፊት የሚፈቅደው ጊዜ የቱንም ያህል ይሁን ጊዜውን በሚገባ ተጠቀሙበት። እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋን በትዕግሥት በመጠበቃችሁ ፈጽሞ ‘ልባችሁ በሐዘን አይሰበርም።’ ከዚያ ይልቅ የደስታ ምንጭ ይሆንላችኋል!

ልታብራራ ትችላለህን?

• ኢየሱስ በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ያሳየው እንዴት ነው?

• ክርስቲያኖች በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ ማሳየት የሚኖርባቸው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ነው?

• የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋን በደስታ የሚጠባበቁት ለምንድን ነው?

• ይሖዋን በትዕግሥት የምንጠብቅበት ጊዜ የደስታ ምንጭ እንዲሆንልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በፊቱ ያለውን ደስታ በመመልከት ጸንቷል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለበርካታ ዓመታት ካገለገልን በኋላም እንኳ ደስታችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ሕይወታቸውን ለውጠዋል