የረጅም ዓመታት ፍለጋ በረከት አስገኘ
የረጅም ዓመታት ፍለጋ በረከት አስገኘ
“ይሖዋ? ይሖዋ ማን ነው?” የስምንት ዓመቷ ሲልቪያ አንዲት ትንሽ ልጅ ካሳየቻት ቤተሰቡ እንደ ቅርስ አድርጎ ከሚያየው የአርመን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይህን ስም አነበበች። እሷ በምትኖርበት በአርሜንያ፣ የረቫን ውስጥ ስለዚህ ስም ጠየቀች። ወላጆቿ፣ አስተማሪዎቿ ሌላው ቀርቶ በዚያ አካባቢ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንኳ ይሖዋ ማን እንደሆነ ሊነግሯት አልቻሉም።
ሲልቪያ አድጋ፣ ትምህርት ጨረሰችና ሥራ ያዘች። ሆኖም ይሖዋ ማን እንደሆነ ማወቅ አልቻለችም። ወጣት በነበረችበት ጊዜ አርሜንያን ጥላ ለመሄድ ተገደደች። ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ፖላንድ ገባችና በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ስደተኞች ጋር መኖር ጀመረች። አብረዋት ከሚኖሩት ሴቶች መካከል አንዷን በየጊዜው እየመጡ የሚጠይቋት ሰዎች ነበሩ። ሲልቪያ “እነዚህ ሰዎች ምንድን ናቸው?” ስትል ትጠይቃታለች። ሴትየዋም “የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ እዚህ የሚመጡት መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑኝ ነው” በማለት መለሰችላት።
ሲልቪያ ይሖዋ የሚለውን ስም ስትሰማ ልቧ በደስታ ፈነደቀ። በመጨረሻም ይሖዋ ማን እንደሆነና ምን ያህል አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ መማር ጀመረች። ዳሩ ምን ያደርጋል ብዙም ሳትቆይ ከፖላንድ መውጣት ግድ ሆነባት። ከባልቲክ ባሕር ባሻገር በምትገኘው በዴንማርክ ጥገኝነት ጠየቀች። የያዘችው ጥቂት ነገሮችን ብቻ ሲሆን ከዚያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ይገኝበታል። በዚህ ጽሑፍ የመጨረሻ ገጽ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች አድራሻ ዝርዝር አገኘች። ይህ ጽሑፍ ይሖዋን እንድታገኝ በማድረግ ረገድ በሕይወቷ ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያበረክት በመሆኑ ከያዘችው ማንኛውም ነገር ሁሉ የላቀ ነበር!
ሲልቪያ ዴንማርክ ስትደርስ ወደ ስደተኞች ካምፕ ተወሰደች። እዚያ እንደደረሰች የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመረች። ዴንማርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በሆልቡክ ከተማ እንደሚገኝ ከአድራሻው ዝርዝር ተረዳች። ሆኖም ሆልቡክ የሚገኘው የት ነው? ሲልቪያ በባቡር ወደ ሌላ ካምፕ ስትዛወር ባቡሩ ሆልቡክን አቋርጦ አለፈ! አሁንም ልቧ በደስታ ፈነደቀ።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሲልቪያ በአንድ ፀሐያማ ቀን ባቡር ተሳፍራ ወደ ሆልቡክ ተመለሰችና ከባቡር ጣቢያው እስከ ቅርንጫፍ ቢሮው በእግሯ ተጓዘች። ያንን ጊዜ መለስ ብላ ስታስታውስ “ወደ ግቢው እንደገባሁ በአንድ አግዳሚ ላይ አረፍ አልኩና ‘ይሄማ ገነት ነው!’ ስል አሰብኩ” ብላለች። ቅርንጫፍ ቢሮው ስትደርስ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላት፤ በመጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት።
ሆኖም በየጊዜው ከካምፕ ካምፕ ትዛወር ነበር። በደረሰችባቸው የስደተኛ ካምፖች የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጋ ታገኝና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን ትቀጥል ነበር። በዚህ ሁኔታ ሁለት ዓመታት ካለፉ በኋላ ራሷን ለይሖዋ ለመወሰን የሚያስችል በቂ እውቀት አገኘች። ከዚያም ተጠመቀችና ብዙም ሳይቆይ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረች። በ1998 የዴንማርክ መንግሥት የመኖሪያ ፈቃድ ሰጣት።
ሲልቪያ አሁን 26 ዓመቷ ሲሆን ስለ ገነት እንድታስብ ባደረጋት ቦታ ማለትም ዴንማርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ታገለግላለች። አሁን እንዲህ ትላለች:- “ምን ማለት እችላለሁ? ትንሽ ልጅ ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋን ስፈልግ ነበር። አሁን አግኝቼዋለሁ። ሕይወቴን እሱን በማገልገል ልጠቀምበት እመኝ ነበር። ይኸው አሁን ቤቴል እገኛለሁ። ለመጪዎቹ ዓመታት በዚህ እንድኖር እጸልያለሁ!”