ዘላለማዊ ደስታ—በሰማይ ወይስ በምድር?
ዘላለማዊ ደስታ—በሰማይ ወይስ በምድር?
ደስተኛ መሆንህ በአንደኛ ደረጃ የተመካው በምትኖርበት ቦታ ላይ ነውን? አብዛኞቹ ሰዎች ደስተኛ መሆናችን ይበልጥ የተመካው ጥሩ ጤንነት ማግኘትን፣ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራትንና ከሌሎች ጋር አስደሳች ዝምድና መመሥረት መቻላችንን በመሳሰሉት ሁኔታዎች ላይ መሆኑን ሳያቅማሙ ይቀበላሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጉዳዩን በዚህ መንገድ ገልጾታል:- “የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።”—ምሳሌ 15:17
የሚያሳዝነው ግን መኖሪያችን የሆነችው ምድር የጥላቻ፣ የዓመፅና የሌሎች የክፋት ዓይነቶች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች። ሆኖም ብዙዎች ከሞቱ በኋላ ለመሄድ ተስፋ የሚያደርጉበትን ሰማይን ወይም መንፈሳዊውን ዓለም በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ሰማይ በአብዛኛው እንደሚታሰበው ምንም ዓይነት ሁከት ተከስቶበት የማያውቅ ምንጊዜም ፍጹም ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት ቦታ ነውን?
አምላክ መላእክት ተብለው ከሚጠሩ በሚልዮን ከሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ጋር በሰማይ እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ማቴዎስ 18:10፤ ራእይ 5:11) መላእክት መንፈሳዊ ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ እንደሆኑ ተገልጿል። (ኢዮብ 38:4, 7) እንደ ሰዎች ሁሉ መላእክትም የመምረጥ ነፃነት ያላቸው ፍጡራን እንጂ ሮቦቶች አይደሉም። ከዚህ የተነሳ እነሱም ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ ነገር ለመሥራት ሊመርጡ ይችላሉ። መላእክት ስህተት ለመሥራት ይመርጣሉን? በእርግጥም አንዳንዶች፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መላእክት ከበርካታ ሺህ ዓመታት በፊት በአምላክ ላይ በማመፅ ኃጢአት መሥራታቸውን ሲያውቁ ይገረሙ ይሆናል!—ይሁዳ 6
በሰማይ የተነሡ ዓመፀኞች
በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ኃጢአት የተሠራው ከጊዜ በኋላ ሰይጣን (ተቃዋሚ) እና ዲያብሎስ (ስም አጥፊ) ተብሎ በተጠራ በአንድ መልአክ ዓመፅ ምክንያት ነው። በአንድ ወቅት ታዛዥ የነበረው ይህ መልአክ በገዛ ፈቃዱ ስህተት ለመሥራት መረጠ። ከዚህ በኋላ ሰይጣን በሌሎች መንፈሳዊ ፍጡራን ላይ በካይ ተጽእኖ በማሳደሩ በኖኅ ዘመን ከውኃ ጥፋት በፊት ብዙ ቁጥር ያላቸው መላእክት በአምላክ ላይ በማመፅ ከእሱ ጋር ተባበሩ።—ዘፍጥረት 6:2 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ 2 ጴጥሮስ 2:4
እነዚህ ኃጢአተኛ መላእክት ወዲያው ከሰማይ አልተባረሩም። ከዚህ ይልቅ ለበርካታ ሺህ ዓመታት ወደ ሰማይ የመግባት መብታቸውን ሳይነፈጉ በትዕግሥት ታልፈዋል። a ይሁን እንጂ አንዳንድ እገዳዎች እንደተጣሉባቸው ግልጽ ነው። ሆኖም አምላክ ለእነዚህ ክፉ አድራጊዎች ያሳየው ትዕግሥት ሲያበቃ በመጨረሻ ለዘላለም እንዲጠፉ ተፈርዶባቸው ከሰማይ ‘ተጣሉ።’ ከዚህ በኋላም በሰማይ “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ” የሚል ድምፅ ተሰምቷል። (ራእይ 12:7-12) በመጨረሻ ሰማይ ከእነዚህ መጥፎ ረብሸኞች በመጽዳቱ ታማኝ መላእክት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ግልጽ ነው!
በሰዎች ዘንድ እምብዛም ከማይታወቁት ከእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች መረዳት እንደሚቻለው የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን ምንጊዜም የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ሲሉ እውነተኛ ሰላም ሊኖር አይችልም። (ኢሳይያስ 57:20, 21፤ ኤርምያስ 14:19, 20) በአንጻሩ ደግሞ ሁሉም ፍጡር የአምላክን ሕግ ሲታዘዝ ሰላምና ፀጥታ ይሰፍናል። (መዝሙር 119:165፤ ኢሳይያስ ) በመሆኑም ሰዎች ሁሉ አምላክን ቢወድዱና ቢታዘዙ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ቢዋደዱ ኖሮ ምድር እውነተኛ ደስታ የሰፈነባት አስደሳች መኖሪያ አትሆንም ነበርን? የመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አዎን፣ የሚል ነው! 48:17, 18
ሆኖም በራስ ወዳድነት ክፉ አካሄዳቸውን ለመለወጥ ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ከልባቸው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ሰላም ለዘላለም ማወካቸውን ይቀጥላሉን? አይቀጥሉም። አምላክ በሰማይ በነበሩ ክፉ መላእክት ላይ እርምጃ እንደወሰደ ሁሉ በዚህ ምድር በሚኖሩ ክፉ ሰዎችም ላይ እርምጃ ይወስዳል።
የጸዳች ምድር
አምላክ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት” ብሏል። (ኢሳይያስ 66:1) አምላክ የቅድስና ቁንጮ እንደመሆኑ መጠን ‘የእግሩ መረገጫ’ ያለ ገደብ በክፋት እንድትቆሽሽ አይፈቅድም። (ኢሳይያስ 6:1-3፤ ራእይ 4:8) ሰማይን ከክፉ መላእክት እንዳጸዳ ሁሉ ቀጥሎ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ምድርንም ሙሉ በሙሉ ከክፉዎች ያጸዳታል:-
“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።”—መዝሙር 37:9
“ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
“ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፣ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ . . . ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።”—2 ተሰሎንቄ 1:6-9
“ዓለሙም [የክፉዎች ዓለም] ምኞቱም ያልፋ[ል]፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17
ምድር ሰላም የሰፈነባት ቦታ ሆና ትቀጥል ይሆን?
ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ክፉዎችን የሚታገሥበት ጊዜ ገደብ እንዳለው በግልጽ የሚናገሩ ቢሆንም ክፋት አንዴ ከተወገደ በኋላ እንደገና እንደማይቀሰቀስ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ደግሞም እኮ፣ ከኖኅ የውኃ ጥፋት በኋላ ወዲያው ክፋት በከፍተኛ መጠን በመንሰራፋቱ አምላክ የሰዎችን መጥፎ ዕቅድ ለማጨናገፍ ቋንቋቸውን ለመደባለቅ ተገድዷል።—ዘፍጥረት 11:1-8
ክፋት እንደገና እንደማያንሰራራ እርግጠኞች የምንሆንበት ዋነኛ ምክንያት ከጥፋት ውኃ በኋላ ወዲያው እንደታየው ሳይሆን በዚህ ጊዜ በምድር ላይ ሰብዓዊ አገዛዝ የሚያከትም መሆኑ ነው። ከዚህ ይልቅ ምድር በአምላክ መንግሥት ትገዛለች። ከሰማይ ሆኖ የሚገዛው ይህ መንግሥት የምድር ብቸኛው መስተዳደር ይሆናል። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) መንግሥቱ ክፋትን እንደገና ለማስጀመር ጥረት በሚያደርግ በማንኛውም ሰው ላይ ፈጣን እርምጃ ይወስዳል። (ኢሳይያስ 65:20) እንዲያውም የክፋት ጠንሳሽ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስንና ግብረ አበሮቹ የሆኑትን ክፉ መላእክት ማለትም አጋንንትን በመጨረሻ አንድ ላይ ያጠፋቸዋል።—ሮሜ 16:20
በተጨማሪም የሰው ልጅ ስለ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሥራ የሚጨነቅበት ምክንያት አይኖርም። በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች በወንጀል ተግባር ለመሠማራት የሚዳረጉት ከእነዚህ ነገሮች እጦት የተነሳ ነው። አዎን፣ መላዋ ምድር ለሁሉም የሚዳረስ የተትረፈረፈ በረከት የምታስገኝ ፍሬያማ ገነት ትሆናለች።—ኢሳይያስ 65:21-23፤ ሉቃስ 23:43
ከሁሉም በላይ የአምላክ መንግሥት ዜጎቹ ሰላማዊ አኗኗር እንዲከተሉ የሚያስተምራቸው ሲሆን ከዚሁ ጋር የሰብዓዊ ፍጽምና የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲደርሱም ይረዳቸዋል። (ዮሐንስ 17:3፤ ሮሜ 8:21) ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ ከጉድለቶቹና ከኃጢአተኝነት ዝንባሌዎቹ ጋር መታገል አያስፈልገውም። ፍጹም ሰው በነበረው በኢየሱስ ሁኔታ እንደታየው ለአምላክ ፍጹም ታዛዥነት ማሳየት የሚቻልና አስደሳች ነገር ይሆናል። (ኢሳይያስ 11:3) እንዲያውም ኢየሱስ ከፍተኛ ፈተናና ሥቃይ ተደቅኖበት እያለም ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። በገነት ውስጥ በሚኖረው ሕይወት ግን ፈተናና ሥቃይ ፈጽሞ የማይታሰቡ ነገሮች ይሆናሉ።—ዕብራውያን 7:26
አንዳንዶች ወደ ሰማይ የሚሄዱበት ምክንያት
ሆኖም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ኢየሱስ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ። . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ” ብሎ መንገሩን ያውቃሉ። (ዮሐንስ 14:2, 3) ይህ ነገር በምድራዊ ገነት ላይ የዘላለም ሕይወት ይኖራል ከሚለው ሐሳብ ጋር አይጋጭምን?
እነዚህ ትምህርቶች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አይደሉም። እንዲያውም አንዱ ሌላውን ይደግፋል። በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ማለትም 144, 000 ሰዎች ብቻ በሰማይ ለመኖር መንፈሳዊ ፍጡር ሆነው እንደሚነሱ ነው። እነዚህ ሰዎች ይህ አስደናቂ ሽልማት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው? ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ “ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ” የተባለለት ቡድን በእነሱ የተዋቀረ ስለሆነ ነው። (ራእይ 14:1, 3፤ 20:4-6) በምድር ላይ ከሚኖሩት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ 144, 000ዎቹ በእርግጥም “ታናሽ መንጋ” ናቸው። (ሉቃስ 12:32) በተጨማሪም የሰዎችን የጋራ ችግሮች የቀመሱ በመሆናቸው የሰው ልጆችንና የምድርን የተኃድሶ ሂደት በበላይነት ሲቆጣጠሩ እንደ ኢየሱስ እነሱም ‘በድካማችን ሊራሩልን’ ይችላሉ።—ዕብራውያን 4:15
ምድር—የሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ
አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በማቅረብ ከዛሬ 2, 000 ዓመት ገደማ በፊት 144, 000ዎቹን መሰብሰብ የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ ቡድን ተሰባስቦ ማለቁን ሁኔታዎች ይጠቁማሉ። (ሥራ 2:1-4፤ ገላትያ 4:4-7) ሆኖም የኢየሱስ መሥዋዕት የተከፈለው “ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” ለ144, 000ዎቹ ብቻ አልነበረም። (1 ዮሐንስ 2:2) በመሆኑም በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ዮሐንስ 3:16) በመቃብር አንቀላፍተው የሚገኙትና በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉት ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በጸዳችው ምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-13, 25፤ ሥራ 24:15) እዚያ ምን ይጠብቃቸዋል?
ራእይ 21:1-4 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እስቲ አስበው፣ ሰዎች ከሞት እስራት ይፈታሉ፤ ሞት የሚያስከትለው ሥቃይና ሐዘንም ለዘላለም ይወገዳል! በመጨረሻ ይሖዋ ለምድርና ለሰው ዘር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ክብራማ ፍጻሜውን ያገኛል።—ዘፍጥረት 1:27, 28
ከፊታችን ያለው ምርጫ —ሕይወት ወይም ሞት
አዳምና ሔዋን ወደ ሰማይ የመሄድ ምርጫ ጭራሽ አልቀረበላቸውም። የቀረበላቸው ምርጫ ቢኖር አምላክን ታዝዘው በምድረ ገነት ላይ ለዘላለም መኖር አሊያም ሳይታዘዙት ቀርተው መሞት ነበር። የሚያሳዝነው፣ አለመታዘዝን በመምረጣቸው ምክንያት ወደ “አፈር” ተመልሰዋል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:2-5, 19) የሰው ልጅ ቤተሰብ ባጠቃላይ እንዲሞትና በመቃብር አልፎ በሰማይ እንዲኖር የአምላክ ዓላማ አልነበረም። አምላክ በሰማይ የሚኖሩ ብዙ ቁጥር ያላቸው መላእክት ፈጥሯል፤ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ሞተው በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች አይደሉም።—መዝሙር 104:1, 4፤ ዳንኤል 7:10
ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን? የመጀመሪያው እርምጃ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል ጸልዮአል።—ዮሐንስ 17:3
በገነት ውስጥ ዘላለማዊ ደስታ ለማግኘት መወሰድ ያለበት ሌላው እርምጃ ያገኘነውን እውቀት በተግባር ማዋል ነው። (ያዕቆብ 1:22-24) በአምላክ ቃል የሚመሩ ሰዎች በኢሳይያስ 11:9 ላይ እንደሚገኘው “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ [የሰው ልጆች] አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” እንደሚለው የመሳሰሉ አስደናቂ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ በዓይናቸው የመመልከት ተስፋ ይጠብቃቸዋል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አምላክ በሰማይም ሆነ በምድር ክፋትን በትዕግሥት ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 70-9 ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29