በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ እንደሚገባ እንዲመላለሱ ሌሎችን እርዱ

ለይሖዋ እንደሚገባ እንዲመላለሱ ሌሎችን እርዱ

ለይሖዋ እንደሚገባ እንዲመላለሱ ሌሎችን እርዱ

“ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ . . . ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።”​—⁠ቆላስይስ 1:​9, 12

1, 2. ከሁሉ ይበልጥ ደስታና እርካታ የሚያስገኘው ነገር ምንድን ነው?

 “የምንኖረው በአንድ እርሻ ቦታ ባለ በመኪና የሚጎተት ተንቀሳቃሽ ቤት ውስጥ ነው። ኑሮአችንን ቀላል ማድረጋችን ምሥራቹን ለሰዎች ለማድረስ ይበልጥ ጊዜ እንዲኖረን አስችሎናል። ብዙዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የመርዳት መብት በማግኘት ብዙ ተባርከናል።”​—⁠በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት

2 ሌሎችን መርዳት ደስታ ያስገኛል ቢባል አትስማማም? አንዳንዶች የታመሙ፣ የተገፉ ወይም በብቸኝነት የተደቆሱ ሰዎችን ለመርዳት ያልተቋረጠ ጥረት ያደርጋሉ። ይህም እርካታ ያስገኝላቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሌሎች መስጠት የሚችሉት ከሁሉ የላቀው እርዳታ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውቀት ማካፈል እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሰዎች የኢየሱስን ቤዛ እንዲቀበሉ፣ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱና ከዚያም የዘላለም ሕይወት በሚያስገኘው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ሊረዳቸው የሚችለው ይህ ብቻ ነው።​—⁠ሥራ 3:​19-21፤ 13:​48

3. ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን የእርዳታ ዓይነት የትኛው ነው?

3 ይሁን እንጂ አምላክን በማገልገል ላይ ማለትም “መንገዱን” በመከተል ላይ ያሉትን ስለ መርዳትስ ምን ለማለት ይቻላል? (ሥራ 19:​9) እነርሱን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለህ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ወይም ቀጣይነት ያለው እርዳታ እንዴት መስጠት እንደምትችል አታውቅ ይሆናል። ወይም ያለህበት ሁኔታ እነርሱን ለመርዳት የሚያስችልህ ሆኖ አይታይህ ይሆናል፤ ይህም ልታገኝ የምትችለውን እርካታ ይገድብብሃል። (ሥራ 20:​35) ሁለቱንም ዘርፍ በተመለከተ ከቆላስይስ መጽሐፍ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።

4. (ሀ) ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በምን ሁኔታ ሥር እያለ ነው? (ለ) ኤጳፍራ በጉዳዩ ውስጥ የገባው እንዴት ነው?

4 ምንም እንኳ ሰዎች የታሰረበት ቦታ ሄደው ሊጠይቁት ይችሉ የነበረ ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በሮም የቁም እስረኛ በነበረበት ጊዜ ነው። ጳውሎስ የነበረውን ውስን ነፃነት የአምላክን መንግሥት ለመስበክ ይጠቀምበታል ብለህ እንደምታስብ የታወቀ ነው። (ሥራ 28:​16-31) ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሊጎበኙት ይችሉ የነበረ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ በተለያየ ጊዜ ከእርሱ ጋር የመታሰር ዕጣ ሳይገጥማቸው አልቀረም። (ቆላስይስ 1:​7, 8፤ 4:​10) ከእነዚህ መካከል በትንሿ እስያ (በአሁኗ ቱርክ) ከኤፌሶን በስተምሥራቅ የምትገኘው በፍርጊያ የቆላስይስ ከተማ ተወላጅ የሆነው ቀናተኛ ወንጌላዊ ኤጳፍራ ይገኝበታል። ኤጳፍራ በቆላስይስ ጉባኤ በማቋቋም ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን በሎዶቂያ እና በኢያራ አቅራቢያ ለሚገኙት ጉባኤዎችም ብዙ ደክሟል። (ቆላስይስ 4:​12, 13) ኤጳፍራ በሮም ወደሚገኘው ወደ ጳውሎስ የተጓዘው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ከሰጠው ምላሽስ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

ለቆላስይስ ሰዎች የተሰጠ ውጤታማ እርዳታ

5. ጳውሎስ ለቆላስይስ ጉባኤ ያደረገውን ነገር የጻፈው ለምንድን ነው?

5 ኤጳፍራ ስለ ቆላስይስ ጉባኤ ጳውሎስን ለማማከር እጅግ አድካሚ ጉዞ በማድረግ ወደ ሮም ሄደ። እነዚህ ክርስቲያኖች በእምነት፣ በፍቅርና በወንጌላዊነቱ ሥራ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ለጳውሎስ ሪፖርት አደረገለት። (ቆላስይስ 1:​3-8) ሆኖም በጣም አሳስበውት ስለነበሩት የቆላስይስ ጉባኤን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ ጥለው ስለነበሩ ጎጂ ተጽዕኖዎችም ነግሮት መሆን አለበት። ጳውሎስ የሃሰት አስተማሪዎች የሚያስፋፏቸውን አንዳንድ አመለካከቶች የሚያፈርስ ሐሳብ የያዘ ደብዳቤ በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ በመጻፍ ምላሽ ሰጠ። በተለይ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚጫወተው ወሳኝ ሚና ላይ አተኩሯል። a እርዳታው ቁልፍ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ ላይ ብቻ የተወሰነ ነበርን? ታዲያ የቆላስይስ ጉባኤን የረዳው እንዴት ነው? ሌሎችን ከመርዳት ጋር በተያያዘ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

6. ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አጽንዖት የሰጠው ለምን ነገር ነበር?

6 ጳውሎስ ደብዳቤውን ገና ሲጀምር ምናልባትም እኛ ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ልናልፍ የምንችለውን እርዳታ መስጠት የሚቻልበት መንገድ አሰፈረ። ጳውሎስ እና ኤጳፍራ የሚገኙት ከቆላስይስ ርቀው ስለነበር ይህ መንገድ ከሩቅ ሆኖ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ እርዳታ መስጠት የሚያስችል ነበር። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ማረጋገጫ ሰጠ:- “ስለ እናንተ ስንጸልይ [“ሁልጊዜ ስንጸልይ” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] . . . የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን።” አዎን፣ ይህ በቀጥታ ስለ ቆላስይስ ክርስቲያኖች የቀረበ ጸሎት ነበር። ጳውሎስ አክሎም እንዲህ አለ:- “ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም።”​—⁠ቆላስይስ 1:​3, 9

7, 8. በግልና በጉባኤ የሚቀርቡ ጸሎቶች ብዙውን ጊዜ የትኞቹን ጉዳዮች የሚጠቅሱ ናቸው?

7 ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ እንደሆነ እናውቃለን፤ ስለሆነም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (መዝሙር 65:​2፤ 86:​6፤ ምሳሌ 15:​8, 29፤ 1 ዮሐንስ 5:​14) ሆኖም ለሌሎች በምንጸልይበት ጊዜ የጸሎታችን ይዘት ምን ዓይነት መሆን አለበት?

8 ብዙውን ጊዜ ስለ ‘ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር’ እናስብና እንጸልይ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 5:​9) ወይም በተፈጥሮ አደጋ ወይም በከፍተኛ መቅሰፍት በተመታ አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖችንና ሌሎች ሰዎችን ጠቅሰን ወደ ይሖዋ እንጸልይ ይሆናል። በሌላ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት በይሁዳ ረሃብ መግባቱን በሰሙ ጊዜ እርዳታ ከመላካቸው በፊት ለወንድሞቻቸው ተደጋጋሚ ጸሎት አቅርበው እንደሚሆን የታወቀ ነው። (ሥራ 11:​27-30) በእኛም ዘመን ብዙዎች ጉዳዩን እንዲያውቁና “አሜን” እንዲሉ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ መላውን የወንድማማች ማኅበር ወይም በርካታ ቁጥር ስላላቸው ወንድሞች የሚገልጹ ጸሎቶች ሲቀርቡ ብዙውን ጊዜ እንሰማለን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:​16

ስትጸልዩ ለይታችሁ ጥቀሱ

9, 10. (ሀ) ግለሰቦችን በስም ጠቅሶ መጸለይ ተገቢ መሆኑን የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ? (ለ) ጳውሎስን በተመለከተ ቀጥተኛ ጸሎት ሊቀርብ የቻለው እንዴት ነው?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዩን ለይተው በመጥቀስ ስለ ሌሎች የቀረቡ ጸሎቶችን ይዟል። በሉቃስ 22:​31, 32 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል። አሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያቱ ከበውታል። ሁሉም ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጡ የአምላክ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ስለ እነርሱ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:​9-14) ሆኖም ኢየሱስ ጴጥሮስን ለይቶ በመጥቀስ በቀጥታ ይህን ደቀ መዝሙር የሚመለከት ልመና አቅርቧል። ሌሎች ምሳሌዎችም አሉን። ኤልሳዕ አንድን ሰው ማለትም አገልጋዩን አምላክ እንዲረዳው ጸልዮአል። (2 ነገሥት 6:​15-17) ሐዋርያው ዮሐንስ ለጋይዮስ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነት ጸልዮአል። (3 ዮሐንስ 1, 2) እንዲሁም አንድን ቡድን በማስመልከት የተለያዩ ጸሎቶች ቀርበዋል።​—⁠ኢዮብ 42:​7, 8፤ ሉቃስ 6:​28፤ ሥራ 7:​60፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​1, 2

10 ጳውሎስ የጻፈው ደብዳቤ ለይቶ ጠቅሶ የመጸለይን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ለእርሱም ወይም ለእርሱና ለሥራ ባልደረቦቹ እንዲጸልዩለት ጠይቋል። ቆላስይስ 4:​2, 3 እንዲህ ይነበባል:- “ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ።” የሚከተሉትን ተጨማሪ ምሳሌዎችም ተመልከት:- ሮሜ 15:​30፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​25፤ 2 ተሰሎንቄ 3:​1፤ ዕብራውያን 13:​18

11. ኤጳፍራ ሮም በነበረበት ጊዜ ለእነማን ጸልዮአል?

11 ከጳውሎስ ጋር በሮም የነበረው ኤጳፍራም ለሌሎች ይጸልይ ነበር። “ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ . . . ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።” (ቆላስይስ 4:​12) “ይጋደላል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በጥንት የስፖርት ግጥሚያ ላይ የሚካፈል አንድ ስፖርተኛ የሚያደርገውን “ትግል” ሊያመለክት ይችላል። ኤጳፍራ ያለ ማቋረጥ ይጸልይ የነበረው እንዲያው በደፈናው በዓለም ዙሪያ ስለነበሩ የአማኞች ቡድን ወይም በትንሿ እስያ ስለሚኖሩ እውነተኛ አምላኪዎች ነበር? ኤጳፍራ ይጸልይ የነበረው ለይቶ በቆላስይስ ስለነበሩ ክርስቲያኖች እንደነበር ጳውሎስ አመልክቷል። ኤጳፍራ የነበሩበትን ሁኔታ ያውቅ ነበር። ሁሉንም በስም ባናውቃቸውም ወይም ምን ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ባናውቅም የሚከተሉት ነገሮች ተፈጥረዋል ብለን እናስብ። ወጣቱ ሊኖስ በጊዜው ተስፋፍተው የነበሩ ፍልስፍናዎች ከሚያሳድሩት ተጽእኖ ጋር እየተዋጋ ነበር። ፉሮን ቀደም ሲል ይከተለው የነበረው የአይሁድ ልማድ የሚያሳድረውን ማባበያ ለመቋቋም ተጨማሪ ጥንካሬ ማግኘት ያስፈልገው ይሆናል። የማያምን ባል የነበራት ጠርሲዳ ልጆቿን በጌታ ማሳደግ ትችል ዘንድ ጽናትና ጥበብ ማግኘት ያስፈልጋት ይሆን? ታሞ ለሞት ተቃርቦ የነበረው አስቀሪጦን ተጨማሪ ማጽናኛ ያስፈልገው ይሆን? አዎን፣ ኤጳፍራ በጉባኤው ያሉትን ሁሉ ያውቃቸዋል፤ ኤጳፍራ እንደነዚህ ያሉት ተወዳጅ ሰዎች ለይሖዋ እንደሚገባ መመላለስ ይችሉ ዘንድ እርሱም ሆነ ጳውሎስ በጥብቅ ጸልየውላቸዋል።

12. በግል የምናቀርበው ጸሎት በተቻለ መጠን ለይቶ የሚጠቅስ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ይህ ምሳሌ እኛም ሌሎችን እንዴት መርዳት እንደምንችል የሚጠቁመው ነገር እንዳለ አስተውለሃል? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ተሰብሳቢዎች ከመኖራቸው አንጻር በክርስቲያን ጉባኤ ላይ የሚቀርቡት ጸሎቶች ጠቅለል ያለ ይዘት ያላቸው ናቸው። ይሁን እንጂ በግል ወይም በቤተሰብ የምናቀርባቸው ጸሎቶች ለይተው የሚጠቅሱ ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ ሁሉንም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም መንፈሳዊ እረኞች እንዲመራቸውና እንዲባርካቸው መጠየቅ ብንችልም አልፎ አልፎ ለይተን መጥቀስ እንችል ይሆን? ለምሳሌ ያህል ጉባኤህን የሚጎበኘውን የወረዳ የበላይ ተመልካች ወይም የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪህ ስም ጠቅሰህ ለምን አትጸልይም? የጢሞቴዎስ እና የአፍሮዲጡ ጤንነት ጳውሎስን በግል ያሳስበው እንደነበር ከ⁠ፊልጵስዩስ 2:​25-28 እና 1 ጢሞቴዎስ 5:​23 መመልከት እንችላለን። እኛም የምናውቃቸውን የታመሙ ሰዎች ስማቸውን ጠቅሰን በመጸለይ ተመሳሳይ የአሳቢነት ስሜት ማሳየት እንችል ይሆን?

13. በግል በምናቀርበው ጸሎት ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ አንዳንድ ተገቢ የሆኑ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

13 በሌሎች የግል ጉዳይ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ እንዳለብን የታወቀ ቢሆንም ጸሎቶቻችን ለምናውቃቸውና ለምናስብላቸው ሰዎች ያለንን ልባዊ አሳቢነት የሚያንጸባርቁ መሆናቸው የተገባ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:​13፤ 1 ጴጥሮስ 4:​15) ከሥራ የተፈናቀለ ወንድም ይኖር ይሆናል፤ ሌላ ሥራ ልንሰጠው ባንችልም በግል በምናቀርበው ጸሎት ስሙን ልንጠቅስና በገጠሙት ችግሮች ላይ ትኩረት ልናደርግ እንችላለን። (መዝሙር 37:​25፤ ምሳሌ 10:​3) ‘በጌታ ብቻ’ ለማግባት ቁርጥ ውሳኔ በማድረጓ ምክንያት ያለ ባልና ያለ ልጅ የቀረችን በእድሜ የገፋች አንዲት ነጠላ እህት እናውቅ ይሆን? (1 ቆሮንቶስ 7:​39) በግልህ በምትጸልይበት ጊዜ ይሖዋ እንዲባርካትና በአገልግሎቷ ታማኝ ሆና እንድትቀጥል እንዲረዳት ለምን አትጠይቅም? ሌላም ምሳሌ ብንወስድ ሁለት ሽማግሌዎች ስህተት ለፈጸመ አንድ ወንድም ምክር ሰጥተው ይሆናል። ሁለቱም በየግላቸው በሚያቀርቡት ጸሎት ለምን አልፎ አልፎ አይጠቅሱትም?

14. ለይቶ በመጥቀስ መጸለይ ሌሎችን ከመርዳት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

14 በግል በምታቀርበው ጸሎት ውስጥ ልትጠቅሳቸው የምትችላቸው የይሖዋ ድጋፍ፣ ማጽናኛ፣ ጥበብና መንፈስ ቅዱስ የሚያስፈልጋቸው የምታውቃቸው በርካታ ግለሰቦች መኖራቸው አይቀርም። በቦታ ርቀት ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በቁሳዊ መርዳት ወይም ቀጥተኛ እርዳታ ማድረግ እንደማትችል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ለወንድሞችህና ለእህቶችህ መጸለይን አትርሳ። ለይሖዋ እንደሚገባ ሆነው መመላለስ እንደሚፈልጉ ታውቃለህ፣ ሆኖም ይህን ለዘለቄታው ማድረግ ይችሉ ዘንድ እርዳታ ማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። እንዲህ ያለውን እርዳታ ለመስጠት የሚያስችለው ቁልፍ ደግሞ የአንተ ጸሎት ነው።​—⁠መዝሙር 18:​2፤ 20:​1, 2፤ 34:​15፤ 46:​1፤ 121:​1-3

ሌሎችን ለማበረታታት ጣር

15. የቆላስይስ የመጨረሻ ክፍል ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባው ለምንድን ነው?

15 እርግጥ ነው፣ ሌሎችን በተለይ ደግሞ በአቅራቢያህ የሚኖሩና የምትወዳቸውን ሰዎች መርዳት የምትችልበት መንገድ ለይቶ የሚጠቅስ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ብቻ ነው ማለት አይደለም። የቆላስይስ መጽሐፍ ይህን ግልጽ ያደርጋል። በርካታ ምሁራን ጳውሎስ መሠረተ ትምህርትን የሚመለከት መመሪያና ተግባራዊ መሆን የሚችል ምክር ካሰፈረ በኋላ ከግል ሰላምታ ያለፈ ነገር አልጻፈም የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ። (ቆላስይስ 4:​7-18) በተቃራኒው የመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል ትኩረት የሚስብ ምክር እንደያዘና ከዚሁ ክፍል ብዙ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል ቀደም ሲል ተመልክተናል።

16, 17. በ⁠ቆላስይስ 4:​10, 11 ላይ ስለተጠቀሱት ወንድሞች ምን ማለት እንችላለን?

16 ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከተገረዙት ወገን ያሉት፣ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ:- ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ተቀበሉት የሚል ትእዛዝ ተቀበላችሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፣ እኔንም አጽናንተውኛል [“የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል፣” NW ]።”​—⁠ቆላስይስ 4:​10, 11

17 እዚህ ላይ ጳውሎስ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የተወሰኑ ወንድሞችን ለይቶ ጠቅሷል። እነዚህ ሰዎች ከተገረዙት ወገን እንደሆኑ ማለትም አይሁዳዊ አስተዳደግ እንዳላቸው ገልጿል። በሮም በርካታ የተገረዙ አይሁዳውያን የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹም ክርስትናን ተቀብለዋል። ያም ሆኖ ግን ጳውሎስን የረዱት በስም የጠቀሳቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከአሕዛብ ከመጡ ክርስቲያኖች ጋር ተባብረው ለመሥራት ፈጽሞ ወደኋላ አላሉም። እንዲሁም ከጳውሎስ ጋር በመሆን ለአሕዛብ በመስበኩ ሥራ በደስታ ተካፍለው መሆን አለበት።​—⁠ሮሜ 11:​13፤ ገላትያ 1:​16፤ 2:​11-14

18. ጳውሎስ አብረውት የነበሩትን አንዳንድ ሰዎች አመስግኖ የተናገረው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ “የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል” በማለት የተናገረውን ልብ በል። ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እዚህ ቦታ ላይ ብቻ የሚገኝ አንድ ግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። ብዙ ተርጓሚዎች ይህን ቃል “ማጽናኛ” ብለው ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ “ማጽናኛ” ተብሎ የሚተረጎመው የተለመደው የግሪክኛ ቃል (ፓራካሊዮ ) የሚለው ቃል ነው። ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ ይህን ቃል የተጠቀመ ቢሆንም ቆላስይስ 4:​11 ላይ የተጠቀመበት ቃል ግን ከዚህ የተለየ ነው።​—⁠ማቴዎስ 5:​4፤ ሥራ 4:​36፤ 9:​31፤ 2 ቆሮንቶስ 1:​4፤ ቆላስይስ 2:​2፤ 4:​8

19, 20. (ሀ) ጳውሎስ በሮም የረዱትን ሰዎች ለመግለጽ የተጠቀመበት መግለጫ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? (ለ) እነዚህ ወንድሞች ጳውሎስን በምን መንገድ ረድተውት ሊሆን ይችላል?

19 ጳውሎስ የጠቀሳቸው እነዚህ ሰዎች በቃል ማጽናኛ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቆላስይስ 4:​11 ላይ የሚገኘው “የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል” የሚለው የግሪክኛው አነጋገር አንዳንድ ጊዜ ሥቃይን ለማስታገስ ተብሎ የሚወሰድን መድኃኒት ለማመልከት በዓለማዊ ጽሑፎች ውስጥ ይሠራበታል። ኒው ላይፍ ቨርሽን እንዲህ ይነበባል:- “በእጅጉ ረድተውኛል!” ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን “ከፍተኛ እርዳታ አድርገውልኛል” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። በአቅራቢያው ይኖሩ የነበሩ እነዚህ ክርስቲያን ወንድሞች ለጳውሎስ ምን እገዛ አድርገውለት ይሆን?

20 ጳውሎስ ሰዎች እየመጡ እንዲጠይቁት ይፈቀድለት የነበረ ቢሆንም ማድረግ የማይችላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል እንደ ምግብና የክረምት ልብስ የመሳሰሉትን የግድ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ሄዶ መግዛት አይችልም ነበር። ለማጥኛ የሚያገለግሉትን ጥቅልሎች ወይም ለመጻፊያ የሚሆኑ መሣሪያዎችን እንዴት ያገኛል? (2 ጢሞቴዎስ 4:​13) እነዚህ ወንድሞች ገበያ ወጥቶ እንደ መግዛት ወይም እንደ መላላክ ያሉ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማድረግ ረድተውታል ብለህ አትገምትም? አንዳንድ ጉባኤዎች ስላሉበት ሁኔታ በቂ መረጃ አግኝቶ ገንቢ የሆነ አንድ ነገር ማድረግ ይፈልግ ይሆናል። እስረኛ እንደመሆኑ መጠን ይህን ማድረግ አይችልም ነበር፤ ስለዚህ እነዚህ ወንድሞች መልእክቶችን ይዘው በመሄድና ከዚያም ሪፖርቶችን ይዘው በመመለስ ለጳውሎስ ጉባኤዎችን ጎብኝተውለት ይሆናል። ምንኛ የብርታት ምንጭ ናቸው!

21, 22. (ሀ) በ⁠ቆላስይስ 4:​11 ላይ ያሉት ቃላት ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው? (ለ) ከጳውሎስ ጋር የነበሩት ወንድሞች የተዉትን ምሳሌ ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

21 ጳውሎስ “የብርታት ምንጭ” መሆንን በተመለከተ የጻፈው መልእክት እኛም ሌሎችን እንዴት መርዳት እንደምንችል ማስተዋል እንድናገኝ ያደርገናል። ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በመጠበቅ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በስብከቱ ሥራ በመካፈል ረገድ ለይሖዋ እንደሚገባ እየተመላለሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም ልናደንቃቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ለጳውሎስ እንደሆኑለት እኛም ‘የብርታት ምንጭ’ ለመሆን ማድረግ የምንችለው ተጨማሪ ነገር ይኖር ይሆን?

22 አንደኛ1 ቆሮንቶስ 7:​37ን በጥበብ እየተከተለች ያለች ሆኖም የቅርብ የቤተሰብ አባል የሌላት አንዲት እህት የምታውቁ ከሆነ ምናልባት ቤታችሁ በመጋበዝ ወይም ከወዳጆቻችሁ ወይም ከዘመዶቻችሁ ጋር ሰብሰብ ብላችሁ በምትጫወቱበት ጊዜ አብራችሁ እንድትገኝ በማድረግ በቤተሰባችሁ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ላይ እንድትካፈል ልታደርጓት ትችሉ ይሆን? የአውራጃ ስብሰባ ወደሚደረግበት ቦታ ወይም ለእረፍት ወጣ ስትሉ ከቤተሰባችሁ ጋር አብራ እንድትሄድ ብትጋብዟትስ? ወይም አስቤዛ ለመግዛት ወደ ገበያ የምትሄዱበትን ሰዓት በማመቻቸት አብራችሁ እንድትሄድ ጠይቋት። መበለት ለሆነች ወይም ሚስቱ ለሞተችበት ሰው ወይም መጓጓዣ ለሚያስፈልገው ተመሳሳይ የሆኑ ግብዣዎችን ማቅረብ ይቻላል። ተሞክሯቸውን ሲናገሩ በመስማት ልትጠቀሙ ወይም ፍራ ፍሬ ወይም የልጆችን ልብስ እንደመምረጥ በመሳሰሉ ነገሮች ረገድ ያላቸውን ጥሩ ችሎታ ልትቀስሙ ትችላላችሁ። (ዘሌዋውያን 19:​32፤ ምሳሌ 16:​31) ይህም ይበልጥ ሊያቀራርባችሁ ይችላል። እንዲህ ከሆነ ከመድኃኒት ቤት መድኃኒት እንድትገዙላቸው ወይም ሌላ ሥራ እንድትፈጽሙላቸው ቢፈልጉ ሳይሸማቀቁ እንዲጠይቋችሁ ያደርጋቸዋል። በሮም የነበሩት ወንድሞች ለጳውሎስ ተግባራዊ ድጋፍ በመስጠት የብርታት ምንጭ ሆነውለት እንደነበረ ሁሉ እናንተም መሆን ትችላላችሁ። እንደዚያን ጊዜ ሁሉ ዛሬም የፍቅር ማሰሪያ ይጠናከራል እንዲሁም ቁርጥ ያለ አቋም ይዘን ይሖዋን አንድ ላይ በታማኝነት እንድናገለግል በማድረግ ተጨማሪ በረከት ያስገኝልናል።

23. እያንዳንዳችን በምን ነገር ላይ ጊዜ ብናሳልፍ ጥሩ ይሆናል?

23 ሁላችንም በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ላይ ልናሰላስል እንችላለን። እነዚህ እንደ ምሳሌ ያህል የቀረቡ ቢሆኑም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን “የብርታት ምንጭ” ልንሆን የምንችልባቸውን ተግባራዊ የሆኑ መንገዶች ሊያስታውሱን ይችላሉ። እዚህ ላይ ለማስገንዘብ የተፈለገው ነጥብ የበጎ አድራጎት ዝንባሌ እንድናዳብር አይደለም። በ⁠ቆላስይስ 4:​10, 11 ላይ የተጠቀሱት ወንድሞች ግብም ይህ አልነበረም። ‘ለአምላክ መንግሥት የሚሠሩ የሥራ ባልደረቦች’ ነበሩ። የብርታት ምንጭ ሆነው የተገኙት በቀጥታ ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ነበር። የእኛም ግብ እንዲሁ መሆን አለበት።

24. ለሌሎች የምንጸልይበትና እነርሱን ለመገንባት የምንፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

24 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘ለይሖዋ እንደሚገባ ሆነው መመላለስ’ እንደሚፈልጉ ስለምናምን በግል በምናቀርበው ጸሎት ስማቸውን ጠቅሰን እንጸልያለን እንዲሁም እነርሱን ለማበረታታት ጥረት እናደርጋለን። (ቆላስይስ 1:​10) ይህ እውነታ “በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁና ምሉዓን ሆናችሁ [ቁሙ]” በማለት ኤጳፍራ ለቆላስይስ ወንድሞች ካቀረበው ጸሎትና ጳውሎስም በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ከገለጸው ሌላ ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ነው። (ቆላስይስ 4:​12 NW ) በግለሰብ ደረጃ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተሙትን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 490-1 እና “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” ገጽ 226-8 ተመልከት።

ልብ ብለሃል?

• በግል በምናቀርበው ጸሎት ከፍተኛ እርዳታ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?

• አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ “የብርታት ምንጭ” የሆኑለት እንዴት ነው?

• እኛም “የብርታት ምንጭ” መሆን የምንችለው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ነው?

• ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የምንጸልይበትና እነርሱን ለማበርታት የምንጥርበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተሰባችሁ ለሽርሽር ወጣ በሚልበት ጊዜ ሌላ ክርስቲያንም አብሯችሁ እንዲሆን ማድረግ ትችላላችሁ?

[ምንጭ]

Courtesy of Green Chimney’s Farm