በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአዲሱ ሺህ ዓመት ሰላም ይሰፍን ይሆን?

በአዲሱ ሺህ ዓመት ሰላም ይሰፍን ይሆን?

በአዲሱ ሺህ ዓመት ሰላም ይሰፍን ይሆን?

መስከረም 14, 1999 በፓሪስና በኒው ዮርክ ሲቲ ዓለም አቀፍ የሰላም ባሕል የሚሰፍንበት ዓመት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተሰይሟል። ለ2000 ዓመት ይህን ስያሜ የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ነው። የቀድሞው የዩኔስኮ ዋና ዲሬክተር ፌዴሪኮ ማዮር “የሰላምና የስምምነት ባሕል እንዲዳብር የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ እንዲቋቋም” ተማጽነዋል።

ዩኔስኮ “ጦርነት የሚጀምረው በሰዎች አእምሮ ውስጥ ስለሆነ ሰላምን የማስጠበቁ ግንባታም መከናወን ያለበት በሰዎች አእምሮ ውስጥ ነው” የሚል መርሕ አለው። ድርጅቱ ከዚህ መርሕ ጋር በመስማማት “በትምህርት፣ በውይይትና በትብብር” የሰላም ባሕል እንዲስፋፋ የማድረግ ዕቅድ አለው። ሚስተር ማዮር “ሰላማዊ መሆን፣ ሌላው ቀርቶ ፀረ–ጦርነት አቋም መያዝ ብቻ አይበቃም፤ ሰላም ፈጣሪ መሆን ያስፈልጋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሚያሳዝነው ግን 2000 እንደተጠበቀው ሰላም የሰፈነበት ዓመት ሊሆን አልቻለም። የሰው ልጅ የቱንም ያህል ቢፍጨረጨር ጦርነትንና ብጥብጥን ማስቀረት እንደማይችል በ2000 የተፈጸሙ ሁኔታዎችን ጨምሮ ዘመናዊ ታሪክ አረጋግጧል።

ሆኖም ሰላም ከትምህርት ጋር መያያዙ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው። ከ2, 700 ዓመታት ገደማ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 54:​13፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይኸው ነቢይ አሕዛብ መንገዱን ለመማር ወደ ይሖዋ አምላክ ንጹህ አምልኮ የሚጎርፉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም [“ጦርነትም፣” NW ] ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:​2-4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከዚህ ትንቢት ጋር በመስማማት የይሖዋ ምሥክሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጦርነት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን የዘርና የጎሳ ጥላቻን እንዲያሸንፉ ለመርዳት ዓለም አቀፍ የማስተማር ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ለምድር ዘላቂ ሰላምና ደህንነት በሚያመጣው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ጦርነት አይኖርም። (መዝሙር 72:​7፤ ዳንኤል 2:​44) ከዚያም “የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቈርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።​—⁠መዝሙር 46:​8, 9